በፍትሕ ጋዜጣ ላይ ለምንጽፍ ሁሉ እየተናገሩ አለማነጋገር፣ እያሰቡ አለማሳሰብ

በፍትሕ ጋዜጣ ላይ ለምንጽፍ ሁሉ እየተናገሩ አለማነጋገር፣ እያሰቡ አለማሳሰብ
ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም

ይህ ጽሑፍ ለእኔም የተጻፈ በመሆኑ አንድ ቀልድ እንደመግቢያ ልናገር፤ አማኑኤል ሆስፒታል ሕመምተኛው ውጭ ይጽፋል፤ ሀኪሙ ይመጣና ‹‹ከበደ፣ እንደምናደርህ?›› ብሎት ሰላምታ ከተለዋወጡ በኋላ፣ ሀኪሙ ምን እየጻፍክ ነው? ይልና ይጠይቃል፤ ህመምተኛው ‹‹ደብዳቤ›› ይላል፤ ሀኪሙ ‹‹ለማን ነው?›› ብሎ ሲጠይቅ፣ ሕመምተኛው ‹‹ለራሴ›› ይላል፤ ሀኪሙ የሕመምተኛውን የውስጥ ስሜት ለማወቅ ጓጉቶ ‹‹ምን ይላል?›› ብሎ ይጠይቃል፤ ሕመምተኛው በመደነቅ ዓይኑን በልጠጥ አድርጎ ‹‹ዶክተር መቼ ተላከና፣ መቼ ደረሰኝና!›› አለው፤ እኔም…

በኢትዮጵያ ውስጥ እያሰቡ ለወደፊት ማቀድ አያዋጣም፤ ለሁሉም ሰው የወደፊቱን የሚወስኑት ወንበሩ ላይ ተቀምጠው ሰይፉን የጨበጡት ብቻ ናቸው፤ ከአንድ ዓመት በኋላ ይህንን አድርጌ፣ ከሁለት ዓመት በኋላ ደግሞ ከዚህ ደረጃ ደርሼ… እያለ በራሱ ሀብት፣ በራሱ ጉልበትና በራሱ እውቀት ሥራውን እያቀነባበረ ከዓመት ወደ ዓመት በእቅድ የሚሄድ የተፈቀደለት ብቻ ነው፤ ፈቃዱም ቢሆን ለአንድ ዓመት የተሰጠው በሌላው ዓመት ይሰረዝ ይሆናል፤ ለባል የተፈቀደው ለሚስት አይሠራም ይሆናል፤ ምክንያቱ ግልጽ ነው፤ አንድ ሰውም ሆነ አንድ ድርጅት እቅድ እያወጣ እየተሳካለት ከአደገ በራሱ የሚተማመንና በራሱ ኃይል እየተራመደ የሚያድግ ሲሆን ላልተደላደለው ሥልጣን አስፈሪ ይሆናል፤ በቋፍ እንዲኖር የሚገደደው ደካማ ሆኖ በልመናና በመለማመጥ እንዲጎብጥ ስለሚፈለግ ነው፤ አንድ ሰው ራሱን ችሎ ብቅ ሲል በኩርኩም አናቱን እያሉ ማኮማተር ባህል ነው፤ አልፎ አልፎ እንዲህ በኩርኩም ልኩን እንዲያውቅ ካላደረጉት ጎበዙ ጎበዝ እየሆነ ጎበዝ ያፈራል፤ ከርሞ ጥጃ ከመሆን ይወጣል! ከርሞ ጥጃነት በሚፈለግበት ሥርዓት እድገት እንዴት ይመጣል?

ሀሳብን በጋዜጣ ማውጣት አደባባይ መውጣት ነው፤ አደባባይ የሚወጡበት ጉዳይ የግል ሳይሆን የአገርና የሕዝብ ነው፤ መሆን አለበት፤ አደባባይ በወጣው ጉዳይ ላይ በአገርና በህዝብ ጉዳይ ያገባኛል የሚል ዜጋ ሁሉ ባለቤት ሊሆንበት ይችላል፤ በባለቤትነት ሊተችበት ይችላል፤ በጉዳዩ ላይ የሞቀ ክርክር ቢደረግበት ሁላችንም በብዙ መንገድ ተጠቃሚዎች ልንሆን እንችላለን፤ ነገር ግን እስከዛሬ የሚታየው አዲሱ ልምድ ከላይ ባለስልጣኖች እንደልባቸው ይናገራሉ፤ በግድም ይሁን በውድ አብዛኛው ሰው ይሰማቸዋል፤ ባለሥልጣኖቹን በማስተጋባት ቴሌቪዥኑና ራዲዮው ደጋግመው እስቲሰለች ድረስ ያሰማሉ፤ በግድም ይሁን በውድ የባለሥልጣኖቹ ንግግር ለብዙ ሰዎች ጆሮ ይደርሳል፤ ግን ጆሮ የደረሰ ሁሉ ወደልብ መተላለፉን እርግጠኛ መሆን አይቻልም፤ በአንጻሩ በግል ጋዜጦች ላይ የሚወጡት የተለዩና የተለያዩ ሀሳቦች በተለያዩ ጉዳዮች ላይ አመራሩን የሚተቹ ናቸው፤ እነዚህን ጋዜጦች የሚያነብቡ በጣም ጥቂቶች ናቸው፣ ጋዜጦቹን የሚያገኙዋቸው በገንዘባቸው እየገዙ በመሆኑ የሰዎችን ቀልብ መሳባቸው ይታወቃል፤ እነዚህን ትችቶች ባለሥልጣኖቹ ጉዳያቸው አድርገው የሚያነቡዋቸው አይመስለኝም፤ የእነሱ ንቀት ሚስትህ አረገዘች ወይ ቢሉት፣ ማንን ወንድ ብላ! እንዳለው ነው መሰለኝ፤ ባለሥልጣኖቹ ሁለት ጥቅሞችን ያጣሉ፤ አንደኛ የተቺዎቹን ሀሳብ መረዳትና ከራሳቸው ሀሳብ ጋር የማመዛዘን ዕድሉ ያመልጣቸዋል፤ ሁለተኛው ሕዝቡ በነፃነትና ያለምንም ግዴታ ትችቱን በማንበቡ ብቻ የሚያስተላልፈውን መልእክት ሳያውቁት ይቀራሉ፤ የዚህ ውጤት የአገር ጉዳት ነው፤ እንግዲህ እነሱ የሚናገሩትን ይናገራሉ፤ ሌላውም የሚናገረውን ይናገራል፤ በሁለቱም ወገን የሚነገረው ስለአንድ አገርና ስለአንድ ሕዝብ ነው፤ በሁለቱም በኩል የተያዘው ፈሊጥ ሳያነጋገሩ መናገር ነው፤ ክፉ ሕመም ነው።

የሳያነጋገሩ መናገሩ ፈሊጥ የሚታየው በባለስልጣኖችና በተቺዎቻቸው መሀከል ብቻ አይደለም፤ በተቺዎቹም መሀከል ያው ነው፤ ተቺዎቹም መናገሩን እንጂ እርስበርሳቸው መነጋገሩን ገና የለመዱት አይመስልም፤ እንደታዘብሁት እስካሁን ድረስ በፍትሕ ጋዜጣ ላይ በየሳምንቱ የሚናገሩት ሁሉ እርስበርሳቸው እምብዛም አይነጋገሩም፤ ይህ ሊሆን የሚችለው እያንዳንዱ በሚናገረው ሁሉም ፍጹም ስምምነት ካላቸው ብቻ ነው፤ ወያኔ/ኢህአዴግም እንደዚህ ያለ ፍፁም ስምምነት ያለው አይመስለኝም፤ ወይም በጋዜጣው ላይ የሚናገሩት ሁሉ ይፈራራሉ ማለት ይሆናል፤ ለመፈራራታቸው ብዙ ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል፤ ነገር ግን አንዱም ምክንያት ለአገርም፣ ለወገንም፣ ለራስም ጠቃሚ አይመስለኝም፤ እንዲያውም የባለስልጣኖቹን ባሕርይ ወደመውረሱ የሚያስጠጋ ይመስለኛል፤ ይህ እውነት ከሆነ፣ ማለት በእኩልነት መነጋገር የማንችል ከሆነ መጀመሪያ ማድረግ ያለብን እያንዳንዳችን ለየራሳችን ተገንዝበን ካረጋገጥን ራሳችንን የምናስተካክልበትን መንገድ መከተል ግዴታ ይሆንብናል።

የፍትሕ ጋዜጣ የተሟላና የተዋጣለት ነው ባይባልም፣ በጣም ተፈላጊና ብዙ ሰውም የሚያነብበው ነው፤ ሆኖም በማስፈራራት የተካኑ ሎሌዎች አቤ ቶኪቾን ለስደት ከዳረጉት ወዲህ ፍትሕ ትንሽ ደረቅ ብሏል! በሀሳብ፣ በአስተያየትና እውቀትን በማስፋት የሚቀርቡት መጣጥፎች አብዛኛውን ጊዜ ፀሐፊው ከራሱ ጋር ብቻ የሚያወራባቸው መስለው ይታያሉ፤ የአንባቢን አእምሮ የመኮርኮር፣ ክርክር እንዲከፍት የማድረግ ኃይል ያላቸው አይመስሉም፤ ይህ የመጣጥፎቹ ጉድለት አይመስለኝም፤ ጠጥቶ ዝም፣ የጋን ወንድም! የሚባለው ዓይነት አንባቢና ፀሐፊ ነው፤ በጋዜጣው ላይ ብዙ ሰዎች መጣጥፎችን ቢያቀርቡም እርስበርሳቸው ሲነጋገሩ ወይም ሲከራከሩ አይታዩም፤ ይህ የሕመም ምልክት ይመስለኛል፤ አንድ ሰሞን ከአቶ ስብሐት ነጋ ጋር፣ አንድ ሰሞን ከፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀኝ ጋር ክርክር ቢጤ ተጀመረና ሁሉም እየሮጠ በየምሽጉ ገብቶ ተቋረጠ፤ በዚያን ጊዜም ቢሆን ክርክሩን ከመሩት ሰዎች ውጭ የገባ አንድ ወይም ሁለት ሰው ብቻ ይመስለኛል።

በተለያዩ መንገዶች ደጋግሜ እንደገለጥሁት በእኩልነት ደረጃ ሆነን ለመነጋገርና ለመከራከር ያቅተናል፤ በየፊናችን ስንናገር ራሳችንን ላይ አውጥተን ሰሚውን ከታች አድርገን መደመጥን እንጂ እኛ በተራችን ሌሎችን ማድመጥ እንዳለብን አናውቅም፤ እኛ ለመናገር የምንደፍረውን ያህል ለተናገርነው መልስ የሚሰጠው ድፍረት እንዲያገኝ አንፈልግም፤ እንዲያውም መልስ ከተሰጠን እናኮርፋለን፤ ከመሳፍንት አገዛዝ የወረስነው ባህል ነው፤ ለዚህ ነው ክርክር የማንጀምረው፣ ቢጀመርም የማይቀጣጠለው።

አሁን ደግሞ ስለኢትዮጵያና ጃፓን፣ ስለአጼ ቴዎድሮስና ስለአንድ የጃፓን ንጉሥ ክርክር እየተካሄደ ነው፤ አዝማሚያው የተለመደውን ባሕርያችንን የያዘ ይመስለኛል፤ አንዱ ስለሁነት ሲናገር አንዱ ስለዓላማ ሉዓላዊነት እየተናገረ፣ አንዱ ስለአጼ ቴዎድሮስ ተግባር ሲናገር፣ ሌላው ስለአጼ ቴዎድሮስ ዓላማ መልስ ቢሰጥ መግባባት አይኖርም፤ ክርክሩን እያሻከረው ነው፤ በበኩሌ ሁለቱ ሰዎች የከፈቱት ክርክር ብዙ ቁም-ነገሮችን የያዘ በመሆኑ ብዙ ሰዎችን ይስባል የሚል እምነት ነበረኝ፤ አሁን እንደሚታየው ግን ሁለቱ ሰዎች እንደተለመደው እየተናገሩ ነው እንጂ እየተነጋገሩ አይደለም፤ ስለዚህም አንዳንዶቻችን ክርክር ውስጥ ገብተን የታሪክን አስተሳሰብና ታሪክን የማጥናትና የማጽዳት ኃላፊነታችንን ብንወጣ ጠቃሚ ይመስለኛል።

በክርክሩ ውስጥ ብዙ ሰዎች የሚያውቁትን እየያዙ ቢገቡበት ስለቴዎድሮስና ስለዚያ ዘመን ከፍተኛ ትምህርት እናገኝበት ነበር።

Comments

Dear, professor, you are my hero and role model through my life. you have already known my mind. It is so surprising for me because when I have read the debates on weekly newspaper Fete about Emperor Tewodros II of Ethiopia, it has become puzzle for me. As far as I know, you are columnist on Fete which is weekly news paper. Thank you, and God bless you and your family, professor, even if I live abroad, I always read a weekly Fete. Thus, I have the right to say something or to give suggestions and comments.when I have read the articles, I have observed some mistakes about debate or argumentative writing based on Emperor Tewodros II of Ethiopia.
If a debate is a form of argument then it logically follows that there must be something to argue about. This is called the TOPIC. The topic changes from debate to debate. They are often about current issues of public importance or about general philosophies or ideas. All topics begin with the word "That". As in other arguments there are two sides to any topic. The writers that agrees with the topic is called the AFFIRMATIVE (or the `government' in parliamentary debating) and the writers that disagrees with the topic is called the NEGATIVE. When we write an article for debate, it is important to select a topic that is appropriate for the newspaper readers’ age and education and also we have to try to become free from Bias or Stereotype also propaganda techniques. The debaters have to concern for readers’ opinion and knowledge. the topics will cover areas that the debaters have a specific interest in or, in the case of the Fete newspaper article. Dear my role modal professor, you know very well the rule of debaters. In debating like persuasive or argumentative each writer will present points in favor of their case. They will also spend some time criticizing the arguments presented by the other writer. This is called rebuttal. There are a few things to remember about rebuttal.
First, we have to give priority for Logic; to say that the other side is wrong is not enough. We have to show why the other side is wrong. This is best done by taking a main point of the other side's argument and showing that it does not make sense. Hence, a lot of the thinking for this needs to be done quickly, this is one of the most challenging and enjoyable aspects of debating.
Second, we have to pick the important points - try to rebut the most important points of the other side's case. We will find these are easier and easier to spot. One obvious spots to find them, but do not rebut those points until we get reliable facts.
The last one will be Play the ball - do not criticise the individual speakers, criticise what they say or write.
To sum up, please, all Fete news paper columnist keep the following in mind:-fact and opinion, cause and effect, Source reliability, and also be free from bias or Stereotype.
Thank you professor
God bless you and your family

ለበውቀቱ ስዩም
በእዉቀቱ ባለፈው ጥሩ ጽኁፍ ሀተታ አድዋ ብለህ አስነበብከን፡፡ በኋላ ስለ አጼ ቴዎድሮስ ጽፈህ አስከፋኸን፡፡ ይሄኛው ጽኁፍኅ ትልቅ ፋይዳን ይስታል፣ ያኛው ከቴዎድሮስ ታሪክ ወሳኙንና ጠቃሚውን እየለየ ሊያስረዳህ ይሞክራል፣ አንተ በወቅቱ የነበርክ እስኪመስል ድረስ የቴዎድሮስን ሃጥያት እንደሸማኔ እያልክ እንደሸማኔ በአማርኛ ቋንቋህ ተጠበብክበት፤ በእውነት ከንቱ ጥበብ፡፡ ቃላት ሁሉ ለአንድነታችን ማጠናከሪያ እንጅ የአንድነታችንን መሰረት ለማፍረስ ባይሞክሩ መልካም ነበር፤ አንተ ግን የአንድነቱን መሰረት ቴዎድሮስን በጭካኔ ነካኸው፡፡ ጭካኔ ማለት የስለት ብቻ አይደለም ወንድሜ፡፡ ቃላትህን በአግባቡ ተጠቀም፡፡ ታላቅን በመድፈር የሚገኝ ታላቅነትም የለም፡፡ ቴዎድሮስ ለአንድነት እንደታገለ ብዙ ምስክሮች አሉ፡፡ ቴዎድሮስ ከነዚያ ሁሉ መሳፍንት ጋር ጦር ሲማዘዝ የመሞት ስጋት እንዳለበት ያውቅ ነበር፡፡ ሆኖም አላማ ስለነበረው ፈጣሪም ረድቶታል፤ ብለን እናምናለን፡፡ ለማያምኑ ግን ይህ ከንቱ ነው፡፡ ቴዎድሮስ ወደመጨረሻው ዘመኑ ጥፋቶችን መስራቱን አቤ ጉቤኛ በትህትና ገልጧል፤ ይሁን እንጅ የመጨረሻው ጥፋቱ የህይወቱን ታላቅ ቁምነገር አልዋጠበትም፡፡ በዚህም ምክንያት እርሱ ስለቴዎድሮስ ተናግሮ የማይጠግብ ሆነ፡፡ አንተ የዚህን ሰው ድንቅ ጎን ማየት እንዴት ተሳነህ? አሱን ለማብጠልጠልስ ለምን ደፈርክ? “ዘላልነት እጣ ፈንታ እንጅ ክብር እንዳልሆነ አውቃለሁ” ብለሃል አንተ ራስህ በምርጡ ባለብዙ ፋይዳ ጽኁፍህ “ጉባኤው”፡፡ አንተ ለነገሩ እንኳን ቴዎድሮስን አይነት የጦር መሪ( ጦር የታጠቁ ለማለት ነው) መስቀል የያዙትን ጠንካራ መምህር አቡነ ተክለሃይማኖትን እንኳን ለፅሁፍህ ማጠንከሪያ እንዲሆኑ ያላጋባብ ደንጉረሃቸው ብዙ አይነት ግሳጼ ደርሶብሃል፤ ከግሳጼዎቹ ሁሉ ያልደገፍኩት መመታትህን ብቻ ነው፣ እንዲውም የመቱህ፣ በሰበቡ እንደመቱህ እንገምታለን፡፡ ነግ በኔ ባይሆን እንኳን ይህን አልደግፍም፡፡ ነገር ግን አስተውል፤ ከስህተቶችህ ተማር፡፡ በተለይ ታላላቆችህን ከሰማህና ካከበርክ አንተ ብዙ “እንደ ሀተታ አደዋ” ያሉ ድንቅ ጽኁፎችን እንደምትጽፍ ያንተን ያህል ባይሆንም እኔም አልጠራጠርም፡፡ በዚህ ካልተቃኘህ ግን የፋይዳ ቢስ ቃላት ፋብሪካ ብቻ ሆነህ ትቀራለህ፤ ወይ ደግሞ የሞራል ጉዳይ ያልገባህ ከሆነ ስለታሪክ አስተያየት አትስጥ፡፡ በበኩሌ ተሳስተህ እንጅ ትንሽም ቢሆን ሳይገባህ አይቀርም፣ ስለታሪክ ስትጽፍ አጻጻፍን ከፕሮፌሰር ተማር፤ ቃላትን አይደለም፤ በዚህ ብዙም አታንስም፣ሎጅክን፣ፋይዳን፣ ሰውየውን ከሀሳቡ መለየትን ወዘተ፡፡ አለማየሁ ነው ስሙ ስለ ቴዎድሮስና ጃፓን የጻፈው? እሱን ከሃሳቡ መለየት ተስኖህ እኮ ቁም ስቅሉን አሳየኸው… የሙጥኝ አለ… ወዘተ እያልክ በቃላት ዝባዝንኬ አሸማቀቅከው እኮ፤ ያንተን ሞራል በመጠበቅ ረገድ እሱ ካንተ በብዙ ርቋል፡፡ በእውነቱ በዚህ ወቅት አንተ ግሳጼ ሚገባኅ ወጣት ነህ፡፡ እኔም ወጣት ነኝ፡፡ ልጨቅንብህ አልፈልግም ነበር፤ አንተ ግን ጨክነህ እኔንም አስጨከንከኝ፤ በእርግጥ ጭካኔ፣ ሞራል፣ ክብር፣ ፍቅር፣ ጥላቻ ወዘተ የሚባሉ ስሜቶች ባንተም ውስጥ ካሉ? እነዚህ ያሉህ መሆኑን የሚያስጠረጥረኝ ብዙ ምልክቶች ሳላየሁብህ ነው፡፡ ቃላቶች ማንነትን ይገልጣሉ አይደል? እማትታረም አይመስለኝም፡፡ ከላይ የገለጽኩልኅን አስተያየቶች ሁሉ ምናልባት አጋንኘ ሊሆን ስለሚችል በሚገባህ( ገ እና ባ ይጠብቃሉ) መጠን ተቀበላቸው እንጅ እንደ ስድብ ቆጥረህ መልስ አትፈልግላቸው፤ ስተትህን ማመን ካልቻልክ መማር አትችልም፡፡ መማር እንደምትችል ደግሞ አምናለሁ:: ታላቅ ይቅርታ… ስለተናገርኩት ሳይሆን ስለተናገርኩበት ሁኔታ፤ በጠቃሚ ቃላትህ እስካገኝህ ደህና ሁን፡፡

ፕ/ሮ መስፍን አከብርዎታለሁኝ ብቻ ሳይሆን አርዓያ ምልክት ነዎት ለአገራችን ኢትዮጵያ።
¨በፍትሕ ጋዜጣ ላይ ለምንጽፍ ሁሉ እየተናገሩ አለማነጋገር፣ እያሰቡ አለማሳሰብ¨
ይህን አስተያየትዎትን ግን ወዳጅዎ በዕውቀቱ ስዩምን ለመመከት ዐምዱን ሰለባ አድርገውታል።ሁሉም ነገር ሙያ ይጠይቃል ካለ ብቃት የሚሰራ ስራ ውጤቱ
አመርቂ አይሆንም።ታሪክ አንድ የሙያ ዘርፍ እንጂ ከሰው የሰማውን አሊያም በጨረፍታ ያነበበውን አንድ አመለካከት ይዞ የሚወረውሩት፣መፃፍ የቻለ ሁሉ ባሰኘው መንገድ የሚተርከው እንዳልሆነ ለእርስዎ መንገር ለቀባሪው ማርዳት ነው የሚሆነው።በተረዱት መጠን የሚገለፅ ስሜት ከሆነማ አቶ ስብሃት ነጋ የአክሱም ስርዎመንግስት አጋሜና ጋምቤላን አይደርስም ያሉትም ትክክል ነው ማለት ነው? ሰው አጋጣሚውን አግኝቶ የሚናገረውና የሚፅፈው ታሪክ ከተባለ የበረከት ስምዖን መፅሃፍም የታሪክ ማጣቀሻ ይባላል ማለት ነው? አንባቢም የእራሱ ግንዛቤ አለው የሰጠናችሁን ብቻ ዋጡ አግባብ አይመስለኝም።
አሁን የተያዘው ብሔራዊ ምልክቶቻችንን ማጥፋት፣ማንቋሸሽ ዘመቻ ላይ ነው ዘመኑ ትልቅን በማጣጣል ትልቅነት ግን አይገኝም።ስለ ቢሮክራሲ ለመቀለድ አጠገባችን ብዙ ቢሮክራቶች ሞልተውልንየቀበሌ መታወቂያ ለማውጣት አበሳችንን በምናይበት ምድር ዘመናት ተሻግሮ በዐፄ ቴዎድሮስ ላይ ማላገጥ፣በአቡነ ተክልዬ ላይ ማሽሟጠጥ አግባብ ነው የሚል ካለ ንፁሃን ወንድሞቻችን የሞቱበትን ምርጫ97 ትክክል ነው የሚሉትን ነፍሰገዳዮችም አግባብ ናቸው ከሚሉት በምን ይለያል?ታሪክ እንደተመልካቹና ፀሃፊው ዐይን ብቻ የሚታይ ከሆነ።

Add new comment

Filtered HTML

  • Web page addresses and e-mail addresses turn into links automatically.
  • Allowed HTML tags: <a> <em> <strong> <cite> <blockquote> <code> <ul> <ol> <li> <dl> <dt> <dd>
  • Lines and paragraphs break automatically.

Plain text

  • No HTML tags allowed.
  • Web page addresses and e-mail addresses turn into links automatically.
  • Lines and paragraphs break automatically.