ተቀናቃኝ ቡድኖችና ፖለቲካ

ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም
ተመስገን ደሳለኝ በተቀናቃኝ ቡድኖች ላይ አዲስ የመነጋገሪያ ርእስ ከፍቶአል (ግንቦት 3፣ 2004)፤ ጉዳዩ በጣም አንገብጋቢና በጣም ወቅታዊ ነው፤ እንደተለመደው አንብበን ችላ የምንለው ጉዳይ አይደለም፤ ሁላችንም በተቻለን መጠን እውነትን ይዘን ያለ ይሉኝታና ያለፍርሃት በራሳችን ላይ እንዝመትና እውነትን ይዘን እንነሣ።
በ1997 መኢአድ፣ ኢዴፓ፣ ኢዴሊና ቀስተ ደመና የሚባሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች አንድ ሆነው ቅንጅትን ፈጠሩ፤ ነገር ግን የመኢአድን ከአቶ ኃይሉ ሻውል፣ ኢዴፓን ከአቶ ልደቱ ህልውና ለመለየት በፍፁም የማይቻል ሆነ፤ ስለዚህም የቅንጅትን ህልውና ፈተና ውስጥ ከተቱትና ተበታተነ፤ እስካሁን ድረስ ህልውናውን ከሕዝብ ህልውና ጋር አስተሳስሮ የቆየ የፖለቲካ ፓርቲ በኢትዮጵያ ውስጥ የለም፤ በገዢው ወንበር ላይ በጠመንጃ ኃይል ከወጡ በኋላ ጉልበትና ሀብት ሁሉም በጄ ሁሉም በደጄ ብለው ኢሰፓና ወያኔ/ኢሕአዴግ ሎሌዎቻቸውን ሰብስበው ፓርቲ ቢሉ ዋጋ እንደሌለው አይተናል፤ ደርግ በጉልበት ስልጣን በመያዙና ስልጣንን ጉልበት ብቻ በማድረጉ እንደተጠላ ተፍረክርኮ አይዞህ የሚለው ሳያገኝ ወድቆ ተበታተነ፤ ወያኔ/ኢሕአዴግ እንደገና በጉልበት ኢሰፓን ተካ፤ ሥልጣንን ጉልበት ብቻ አድርጎም እየገዛ ነው፤ በኢሰፓ ዘመን ተቀናቃኝ የፖለቲካ ፓርቲዎች በስምም በተግባርም አልነበሩም፤ በወያኔ/ኢህአዴግ ዘመን የፖለቲካ ፓርቲዎች በስም ተፈልፍለው በተግባር ተለጉመው በመኖና ባለመኖር መሀከል እያጣጣሩ አሉ፤ ያውም ምርጫ ቦርድ መልካም ፈቃዱ ሲሆን!
ለይስሙላ የተቋቋሙት ፓርቲዎች በምርጫ ጊዜ ትንሽ የተፈቀደላቸውን ያህል አባላት አስመርጠው በብሔራዊ ምክር ቤት (ፓርላማ) ያስቀምጣሉ፤ የተከበሩት አባላትም ቤትና ደመወዝ ያገኛሉ፤ የመጨረሻው ዓላማቸውም ይኸው ነው፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች በስም ተሰይመው፣ ህልውናቸውን በአንድ ወይ በሁለት ሰዎች ስም ያስከብራሉ።
በወያኔ/ኢሕአዴግ ዘመን አንድ የተለመደ አጉል ፈሊጥ አለ፤ በሆነ ባልሆነው ወያኔ/ኢሕአዴግን መውቀር ያስመሰግናል፤ በአንጻሩ በተቀናቃኝ ቡድኖች ወይ በመሪዎቻቸው ላይ ትችት ማቅረብ እንደክህደትና ከኢትዮጵያዊነት መስመር እንደመውጣት ይታያል፤ ይህ በተደጋጋሚ የታየ ነው፤ በቅንጅት መሪዎች መሀከል የነበረውን የስልጣን ሽኩቻ በአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ ስናገር በመጀመሪያ የራዲዮው ጠያቂ የነበረችው አነጋገሬን አልወደደችውም፤ የግል ስሜትዋን ለመግለጽ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ እንደገና ደውላ ተገቢ ያልሆነ ጥያቄ ጠየቀችኝ፤ ወሬው ከተላለፈ በኋላም ብዙ ሰዎች እየደወሉ ለብቻቸው ብታነጋግራቸውና ብትመክራቸው ይሻል ነበር በማለት የወቀሳ ትችት አቀረቡልኝ፤ እነዚህ ሰዎች የማከብራቸውና ሀሳባቸውን የማልንቅባቸው ናቸው፤ ለሁሉም የመለስሁላቸው እነሱ ለእኔ የሰነዘሩትን ምክር አንደኛ እኛ ሳናስብበትና ተግባራዊ ሳናደርገው ቀረን ብለው መገመታቸው የሚያሳዝን መሆኑን ነበር፤ ሁለተኛ ሁለትና ሶስት ወራት በማይሞላ ጊዜ ውስጥ በተዋናውያኑ በራሳቸው እውነቱ ገሀድ እንደሚወጣ ነግሬአቸው ነበር፤ እኔ የሥልጣን ጥሙን ሽኩቻ በማንሣቴ ለጠብ በር የከፈትሁ የመሰላቸው ሰዎች በቅንጅት ውስጥ የነበረውን ትግል የማያውቁ ናቸው፣ ገና ቀደም ብዬ ሌላው ሁሉ ካቃተኝ በኋላ የስልጣን ሽኩቻው ቅንጅትን እየጎዳው እንደሆነ ስለተረዳሁ ለቅንጅት ሊቀ መንበር ለኃይሉ ሻውል ደብዳቤ ጽፌ ከምክር ቤት መሰናበቴን አሳወቅሁ፤ ከቅንጅት ምክር ቤት ስወጣ በይፋ በአደባባይ ሳልናገር መቅረቴ ስሕተት ነው፤ መናገር ነበረብኝ፤ ግን ያው በኋላ ከብዙ ሰዎች የሰማሁት ወቀሳ በእኔም ውስጥ ስለነበረ ይሉኝታ ይዞኝ ተሳሳትሁ፤ ከቃሊቲ ከወጣን በኋላ በህንድ አገር ሀኪም ቤት ማጅራቴን በመጋዝ ለመተርተር ስዘጋጅ ድንገት ሳልነቃ ብቀር እውነት ተዳፍኖ እንዳይቀር በማለት ምስክርነቴን ሰጠሁ፤ በዚያን ጊዜ እኔ የነበርሁበትን ሁኔታ በትንሹም ቢሆን ለመገመት ከተቻለ ለእውነት በእውነት ከመመስከር ሌላ ዓላማ እንደማይኖረኝ ለመረዳት እንዴት እንዳስቸገረ እስከዛሬ አልገባኝም፤ ጥርጣሬያችንና አለመተማመናችን ድንበር የለውም ማለት ነው።
ከዚያ በኋላ ብዙ መጽሐፎች ተጽፈዋል፤ ገብረ ክርስቶስ ኃይለ ሥላሴ፣ ልደቱ አያሌው፣ ደበበ እሸቱ፣ አንተነህ ሙሉጌታ (የመጽሐፉን ርእስ አበላሽቶት ብዙ ሰዎች አላነበቡትም እንጂ በጣም ጥሩ መጽሐፍ) መስፍን ወልደማርያምም ጽፈዋል፤ አሁን ደግሞ ሲሳይ አጌና (ከውጭ እንደጋዜጠኛ ይሁን ወይስ የውስጥ መስሎ አላውቅም፤ ነገር ግን በራድዮ ሲናገር እንደሰማሁት ብርሃኑ ነጋን ከእውነቱ ሊያርቀው በጣም ሲሞክር እውነቱን ይደፈጥጣል)፤ ለማናቸውም ታዛቢዎች ተናገሩት አልተናገሩት በኃይሉ ሻውል፣ በብርሃኑና በልደቱ መሀከል የነበረውን ግልጽ የሆነ ሥርዓት ያጣ ፉክክር ማንም ሊክደው ወይም ሊያድበሰብሰውና ሊያልፈው አይችልም፤ ለምን ቅንጅት ፈራረሰ? አንዳንዶቻችን ክብራችንን አንጥፈን ለማስታረቅ ሞክረናል፤ አንድ ምሳሌ ለመስጠት በቀጠሮ ሄደን አቶ ገብረጻድቅ፣ አቶ ይልማ ይፍሩና እኔ ከአቶ ኃይሉ ሻውል አጥር ውጭ ለእኩል ሰዓት ያህል መኪና ውስጥ ቆይተን ሳይሆንልን ተመልሰናል፤ በኋላም አሜሪካ ሆኖ በነጭ ወረቀት ከሕግ ውጭ የሆነ የሹም-ሽር ሲያደርግ ሀሳቡን ለማስለወጥ አሜሪካ ስልክ ደውዬ ለማነጋገር ብሞክር እኔንም ባላንጣው አደረገኝ፤ ተፎካካሪዎቹን ለማቀራረብ፣ ለማስታረቅና ወደአብሮ መሰለፍ ለማምጣት በተደረገው ጥረት የተሳተፉትን ሁሉ ተፎካካሪዎቹ በጥላቻ ይመለከቱአቸው ጀመሩ።
በልደቱ የተጀመረው የቅንጅት መገነጣጠል፣ በብርሃኑ ነጋና በኃይሉ ሻውል ቀጥሎ ብርቱካን የምትመራው አንድነት ብቻውን ቀረ፤ በአንድነትም ውስጥ ገና ከመጀመሪያው ጠቅላላ ጉባኤ ጀምሮ ብርቱካን በመመረጥዋ ቅር ያላቸው አባሎች አኩርፈው ችግር ተፈጥሮ ነበር፤ ብርቱካን ስትታሰር ኤንጂነር ግዛቸው ሽፈራው በጉጉት ሲጠብቀው የነበረውን ወንበር አገኘና የአምባገነንነት አገዛዙን በግምባር ቀደምትነት ከዶር. ኃይሉ አርአያና ከአቶ ዓሥራት ጣሴ ጋር ጀመረ፤ ሁሉም ቢያንስ ከሁለት ሺህ ብር በላይ የወር ደመወዝ ያገኙ ነበር፤ እንዲሁም የጽሕፈት ቤቱ ሠራተኞች ሁሉ በጥሩ ደመወዝ ተሰንገው የተያዙ ነበሩ፤ እነዚህ ናቸው ሎሌዎች አይደለንም የሚሉት፤ ከበስተጀርባቸውም የብሔራዊ ምክር ቤት ገብተው ሌሎቹ ቃሊቲ በነበሩበት ጊዜ ደመወዝ ሲበሉ የነበሩ ናቸው፤ ያንን የደመወዝ ወንበር እንደያዙ ለመቀጠል የተመኙ የአንድነት የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴና የምክር ቤት አባላት ነበሩ፤ ግዛቸው እነዚህን ሁሉ ሎሌዎች አሰልፎ ስሙ ወደምግባሩ መራውና የማይበገር አንባ-ገነን ሆነ፤ ከመጀመሪያዎቹ አወዛጋቢ ጉዳዮች መሀከል አባላት በጽሕፈት ቤቱ አዳራሽ ያለፈቃድ እንዳይሰበሰቡ፣ ግዛቸው፣ ኃይሉ አርአያና ዓሥራት ባልፈቀዱት ጉዳይ መወያየት መከልከሉን፣ በነፃነት አባልነታቸውን ለመወጣት የሚፈልጉትንና ከሎሌነት ያፈነገጡትን ሰዎች ለማስወንጀል ማስፈራራት ነበሩ፤ ከውጭም ድጋፍ ነበራቸው፤ የቅንጅት የድጋፍ ኮሚቴ በአሜሪካ ሊቀመንበር ነኝ የሚል አክሎግ ልመንህ የሚባል የማስፈራሪያ ደብዳቤ ጽፎልን እኔ መልስ ሰጥቸውአለሁ፤ ሌሎች አንገብጋቢ ጉዳዮች ዋና ጸሐፊው አቶ ዓሥራት ጣሴ አንደኛ አንዲት ጸሐፊ የነበረች የአንድነት አባልን ያለማስጠንቀቂያና ካሣ፣ ሁለተኛ አንዲት የጽዳት ሠራተኛን እንዲሁም ያለምንም ማስጠንቀቂያና ካሣ ከሥራ ማስወጣቱ ናቸው፤ በነዚህ ምክንያቶች አንድነት ለሁለት ተከፈለ፤ ግዛቸው መርጠው ወንበሩ ላይ ያስቀመጡትን ሰዎች አባርሮ በዶር. ነጋሶ ጊዳዳ፣ በአቶ ስዬ አብርሃና በአቶ ገብሩ ዓሥራት ድጋፍ መሰላሉን ሊወጣ ተመኘ፤ መሰላሉ ወደቀ።
ዛሬ ቅንጅትን ሰባብረው ግልገል የሥልጣን ፈረሶችን የፈጠሩት ሁሉ በሦስት ምክንያቶች ኮስሰዋል፤ አንደኛ ሰውን መግዣ ገንዘብ እያነሰ ነው፤ ሁለተኛ አባሎችም የተሻለ ንቃትና ትምህርት እያገኙ ሎሌነትን እምቢ እያሉ ነው፤ ሦስተኛ የኢትዮጵያ ሕዝብ የአዲሶቹን መኳንንት የኤንጂነር ግዛቸውን፣ የዶር. ኃይሉ አርአያንና የአቶ ዓሥራት ጣሴን ‹‹በታላላቅ›› ሰዎች ጥላ ስር ሆነው ለመሽሎክ ያቀዱት አልተሳካላቸውም፤ መማር የሚችሉት ሊማሩ ሄዱ፤ የማይችሉት ቀሩ።

Comments

ክቡር ፕሮፌሰር! እንዲህ ዓይነቱ ‹‹አስተያየት ›› የጥላቻ አሉቧልታ እንጂ የሚያግባባና መተማመንን የሚፈጥር ኤመስለኝም፡፡ እንዲህ ዓይነት ቂም ያረገዘ አስተያየትም ለርሰዎ ክብርም ሆነ ለሌሎች/ለተዘለፉት የሚበጅ ኤመስለኝም፡፡ማስተማር እንዲህ በጥላቻ የታጀለ ውርጅብኝ ነው እንዴ? የተመስገንን አስተያየት እኔም ወድጀዋለሁ፣ምክንያቱ ገንቢ ስለሆነ ነው፡፡

ክቡር ፐሮፍ ብለህ መጀመርህ ኢትዮጵያዊነትህ ከውስጥህ ተንጠፍጥፎ ያሳያል እና አመሰግናለሁ፡፡ ግን ፐሮፍ የትላይ ነው የጥላቻ አስተያየት የሰጡጥ እኔ የምለው ሰው ሁሉ ግራ ግራውን ነው እንዴ የሚያነበው የኑሮ ውድነቱ ይን የሚያስቀባጥረን እሳቸው ያሉት ሁሉም ለስልጣን የሚራወጥ ከወያኔ የመይሻል ስግብግብ ሆዳም የአገርን ጥቅም በሶስተኛ እና በአራተኛ ደረጃ የሚያይ ባንዳ ብቻ ነው ያለው ተቃዋሚ በለው ወያኔ ያው ናቸው ለአገር የሚያስቡ ከሆነ በፍቅር በሰላም ተባበሮ መስራት ሲገባቸው ሆድ አምላኩዎች ሆነዋል ነው ያሉት በቃ ይሄ ዛሬ የያዙት እና አሳቸው እወቁኝ ብለው ያሳወቁን ሳይሆን ፐሮፍ የጻዋቸውን መፃህፍት እና መጣጥፎችን ብቻ በማበብ ማወቅ ይቻላል፡፡ ረጅም እድሜ ኢትዮጵያን ለሚያፈቅሩ እና ለንድነቷ ለነጻነትዋ ለለፉ ለሚለፉ ሁሉ ከየፐሮፍን እድሜ እና ፍቅር ይስጥልኝ

This is the fact and you need to accept and take a lesson from it.

ክቡር ጋሽ መስፍን እንዴት ያሉ ብረት የሆኑ ሰው ይሆኑ ይሆን ምን ይሆን የሚበሉት ምን ይሆን የሚጠጡት ግራ ግብ ይለኛል፡፡ እንደ ርስዎ ያሉ አባቶች ባሉበት አገር እንደዚህ ተዋርደን መቀመጣችን ያሳዝናል ገዠያችንም አቶ መለስ ዜናዊ ዋሽንግቶን ዲሲ ተዋርዶ በአበበ ገላው እና በሌሎች ወንድሞቻችን ተሰድቦ አሰድቦን መጣ የአገራችን መሪ የተከበረ ስራ ቢሰራ ክብሩ ለኛ ነበር ታዲ ምን ያደርጋል መለስ ዜናዊም ደጋፊዎቹን አዘጋጅቶ ኖሮ በዛ ቅሪላ ሰለሞን ተካልኝ አማካኘነት እውነትን ለመደፍጠጥ አስሞክሯል እውነት ግን ያሸንፋል ጋንዲ አሽንፏል ማንዴልም እንዲሁ….
ኢትዬጵያችን ከነሙሉ ክብሯ ለዘላለም ትኑር

All of you have taken us to political Armageddon, of course, which is an event of great destruction. Let me tell you one thing! No one can escape from 'Ethiopians' Judgement Day' Whoever you are whether Mr. Meles and Mr. Bereket or Prof. Mesfin and Ing. Hailu or Dr. Araya or Mr. Lidetu all of you will die tomorrow and we will take you to your final resting place! Be meek to save humanity before anything else then we will give you respect!

እርሶ መረጃ አለኝ ባሉበት ነገርላይ አስተያየት መስጠት እጅግ አላዋቂነት ስለሚሆን ዝምታ ጥሩ ነዉ:: ሆኖም ግን አንዳንዴ ስሜታዊ በመሆን የሚሰጡቸው ግምታዊ አስተያየቶች የሚናገሯቸዉ ትልልቅ ቁምነግሮችን ለመስማት እንቅፍት የሚሆኑ ይመስለኛል:: እርሶ የሚወዱት መጻፍ(መጻሀፍ ቅዱስ ማለቴን ነው) ጥቂት ዝንቦች መልካሙን የወይን ጠጅ ያገሙታል ነዉ የሚለዉ? አቶ ሲሳይ መጻፋቸው ላይ የቅንጅት መፈረካከስ በተመለከት ያነሱት መንም ነገር አላነበብኩም:: የመጽሀፉም ፈይዳ እኔ እስከገባኝ ድረስ ኢትዮጵያ ዉስጥ የነበረዉን የፍርድ ስረአት በዚያን ጊዜ ምን ይመስል እንደነበር ማስገንዘብ እንጂ ቅንጅት ዉስጥ የነበረዉን የፖለቲካ ሽኩቻ ማቅረብ አለመሰለኝም:: እርግጥ ነዉ አቶ ልደቱ ባደባባይ የናገራቸዉ የነበሩ ነገሮች ለፍርድቤት የማስረጃ ግብአትነት መዋላቸዉ በተመለከት ጥቂት ብሏል ያግን እርሶ ነበረ የሚሉትን የስልጣን ሽኩቻ በተመለከተ አይደለም::

Add new comment

Filtered HTML

  • Web page addresses and e-mail addresses turn into links automatically.
  • Allowed HTML tags: <a> <em> <strong> <cite> <blockquote> <code> <ul> <ol> <li> <dl> <dt> <dd>
  • Lines and paragraphs break automatically.

Plain text

  • No HTML tags allowed.
  • Web page addresses and e-mail addresses turn into links automatically.
  • Lines and paragraphs break automatically.