የአገሩን ተቃውሞ በአገሩ ቅኔ

የዚህ ዘመን ተቃውሞ መላ-ሰውነቱን ያሳረፈው ሥነ ቀልድ ላይ ነው። ከዚህ ቀደም የነበሩት ዘመናት ተቃውሟቸውን ያስተናግዱ የነበረው በአመዛኙ በቅኔ ነበር ማለት ይቻላል። ቅኔ፤ ምርጊቱ እንደተከፈተ የጋን ጠላ በጊዜ ሂደት ኃይሉን እያጣ የመምጣቱ ምክንያት ግልፅ ነው። የቀድሞቹ ምሁራን መሰረታቸው የቤተክህነት ትምህርት ስለነበር ፖለቲካዊ ቅሬታቸውን የቅኔ ግብአት ለማድረግ አይቸገሩም ነበር። ቀደም ያሉትን ነጋድራስ ተሰማ እሸቴንና ዮፍታሔ ንጉሴን አልፈን የለውጡ ዘመን ወጣቶች ላይ እንረፍ፤
ከ1966 አብዮት አስቀድሞ ተማሪዎች ከአፄ ኃይለሥላሴ አገዛዝ ጋር ቁርሾ መፍጠር ሲጀምሩ ዳርዳርታቸውን ያሳዩት በግጥም ነበር። የኮሌጅ ቀንን ምክንያት በማድረግ የሚቀርቡት የተማሪ ግጥሞች የህዝቡን ጭቆናና በደል የሚያንፀባርቁ ሲሆን አልፎ-አልፎ ደግሞ የቅኔን ልዩ ባህርይ በመንተራስ ሁለት መልክ ያለው መልእክት ይዘው ብቅ ይሉ ነበር። ‹‹አላልንም››፣ ‹‹ብለናል›› በሚል አካፋይ ሰርጥ ውስጥ የተደበቁት ቅኔዎች ዛሬ ወቅታቸው አልፎ ሲነበቡ አንዳንዶቹ ከተልዕኳቸው፣ ከቀስቃሽነት ይልቅ አዝናኝነታቸው ይጐላል። ለምሳሌ ይሄን እንመልከት።
የኃይልዬን ሱሪ ሠፊ አሳጥሮበት፣
ከማይጨው ሲመለስ ጉልበቱ ታየበት።
ቅኔው የፀገየወይን ገብረመድህን ነው። በጥር 1958 ዓ.ም. ‹‹ታጠቅ›› የተሰኘ መጽሔት ላይ ይውጣ እንጂ ቅኔው የተፃፈው ከዚያ በፊት ተማሪዎቹ ከንጉሱ ጋር መደፋፈር እንደጀመሩ ሰሞን ይመስላል። ‹‹ኃይልዬ›› የሚላቸው አፄ ኃይለሥላሴን እንደሆነ ግልፅ ነው። አፄው በማይጨው ጦርነት ሽንፈት የመቅመሳቸውን ታሪካዊ ዳራ ይዞ የተቀኘ ነው።
በነገራችን ላይ ከሱሪ ጋር ተያይዞ ይቀርቡ የነበሩ ብዙ የሽሙጥ ቅኔዎች በወቅቱ ነበሩ። ‹‹ተፈሪ›› የተሰኘ የሱሪ ሞድ ስለነበር ይሆናል ቅኔዎቹ ሁሉ ወደዚያው ሲያመሩ የሚስተዋሉት። ዋለልኝ መኮንን የተቀኘውን ደግሞ እንይ፡-
ከለበሱ አይቀር ሱሪ
የጥንቱን ነበር የተፈሪ
ግን አይመችም ለሥራ
አጥብቆ ይዞ ከቀኝ ከግራ፡፡
እንግዲህ ቅኔዎቹ በአመዛኙ ተመዝግበው የሚገኙት በተማሪዎቹ ነው። ወደ አስተዳደሩ የሚወነጨፉት ቅኔዎች ከወደ ቤተ-መንግሥቱ አካባቢ ምን አይነት አፀፋ እንደሚሰጥ ለማረጋገጥ አዳጋች ይሆናል። አንዳንድ ብቅ ብለው የሚስተዋሉ ቅኔዎች ግን አልጠፉም። ለምሳሌ በነጭ መምህራን ትምህርት የሚያገኙት እነዚህ ወጣቶች ለአመፅ መነሳታቸውን በማየት እንዲህ ተብሎ ቅኔ ተዘርፎ ነበር፡-
የነጯ ላም ጥጃ
ማደጓንም እንጃ
የተማሪዎቹ ቅኔዎች ግን እንደውርጅብኝ የሚቆጠሩ ነበሩ ማለት ይቻላል። ንጉሱን አስመልክቶ ልምዶችንና ወጐችን ጭምር የሚተቹ ቅኔዎች በብዛት ፈልቀዋል። አሁንም ፀገየወይን ገብረመድህን ይቺን ቅኔ ጀባ ይለናል፡-
ዕድሜያችን ሰባ ነው
ቢበዛ ሰማኒያ
ብሎ ነግሮን ነበር
ዳዊት በበገና
ዳሩ ምን ይሆናል ትንቢቱ ቀረና
ዘላለም ይኑሩ ብሎ ያንጋጥጣል
የሰነፍ ልቦና።
ተማሪዎች በአፄ ኃይለሥላሴ ላይ የተቃጣውን የታህሣሥ መፈንቅለ-መንግሥት በግልፅ ደግፈው ሠላማዊ ሰልፍ ወጥተው ነበር። ነገሩ እንደታሰበው ሳይሆን ቀርቶ መፈንቅለ መንግሥቱ ሲከሽፍ ተማሪዎቹ አፄውን ይቅርታ ጠየቁ። ይሁን እንጂ የተማሪዎቹ ይቅርታ ውስጡ ማድፈጥ ኖሮበት በተገኘው አጋጣሚ የመፈንቅለ-መንግሥቱን መክሸፍ በቁጭት ያነሱታል። ለምሳሌ ያህል ይሄን ቅኔ መመልከት ይቻላል።
ቁማር ጨዋታ ተጫውቼ
ገንዘቤን ተበልቼ
ቀረሁ እጄን አጨብጭቤ
ምንኛ ዕድሌ በሰመረ
ዘውዴን ገልብጬ በነበረ።
በዚሁ ጭብጥ ላይ ሌላም ተማሪ አንድ ቅኔ ጣል አድርጓል። የተማሪው ሥም በምህፃረ ቃል ‹‹ኃ.ገ›› ይሰኛል።
የቁልቢውን ገብርኤል
አያሌ ሰዎች ወደውታል
ይሄን አይተው ካህናቱ
እንዲደረጅ በስዕለቱ
እንደታህሳሱ ይሁን ሳይሉ
ሌላም ለማንገስ ያስባሉ።
እዚች ቅኔ ላይ ‹‹እንደታህሣሱ›› የምትለው ቃል መንታ ሃሳብ አርግዛ ነው ግጥሙን ወደ ቅኔነት ያሻገረችው። በጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ኃብተወልድ ጥገናዊ ለውጥ ላይ ተማሪዎቹ ቅሬታ እንደተሰማቸው ለመግለጽ የተቀኘ ሳይሆን አይቀርም ብለን እንጠረጥራለን። ተማሪዎቹ በዚህ ቅኔ ሥርነቀል ለውጥ የመጠየቅ ደረጃ መድረሳቸውን ማረጋገጥ ይቻላል።
የተማሪዎቹ ንቅናቄ ያላረገዘውን ወልዶ የመታቀፍ ዕዳ ከመጣበት በኋላ በቀጣዩ ሥርዓት የአፄውን ያህል እንኳን በአደባባይ የቅሬታ ቅኔ ማሰማት ሳይቻል ቀረ። ዳፋው እስከመላው ሕዝብ ወርዶ መደገፍ እንጂ መንቀፍ ከፍተኛው የአገሪቱ ወንጀል ሆነ። ሌላው ቀርቶ በስማ በለው ፍቺ አንዳንድ ፀሐፊዎችና ድምፃውያን ዘብጥያ ወረዱ። ጥላሁን ገሠሠ፣ ፀጋዬ ደቦጭ፣ ተስፋዬ ለማና የመሳሰሉትን ማንሳት ይቻላል። ይሁንና ‹‹ስርዓት-ጐናጭ›› የሆኑ አንዳንድ ቅኔዎች በሽፍንፍን ብቅ-ብቅ ማለታቸው አልቀረም። ለምሳሌ ያህል የብሔራዊ ቴአትሩ ጌታቸው ደባልቄ ፅፈውት አስናቀች ወርቁ ያቀነቀነችውን ቅኔ እንመልከት።
እግዚአብሔር ይመስገን
አልጋው ሥራ አልፈታም
አልተገኘም እንጂ
እንዳንት ያለ መልካም፡፡
የዚህ ቅኔ የሰምና ወርቅ ማደሪያ ቃል ‹‹አልጋው›› የሚለው ነው። ሰሙ ከፆታ ፍቅር ጋር ተያይዞ የሚፈታበት አግባብ ላይ ያርፋል። ወርቁ ደግሞ ከንጉሠ-ነገሥቱ ‹‹አልጋ›› አንፃር ሲታይ ፍንትው ብሎ ይገለፅልናል። አፄ ኃይለሥላሴንና ሊቀመንበር መንግሥቱን አነፃፅሮ በመልካምነትና በመጥፎነት ይፈርጃቸዋል።
ሌላው ሥርዓት የሚጐንጥ ቅኔ የይልማ ገብረአብ ነው። ለድምፃዊ ኤፍሬም ታምሩ ሰጥቶት ተጫውቶታል። እንዲህ ይላል፡-
በይ ስፊልኝ ገሳ
የእኔ እንቦሳ፤
የዚህ ቅኔ ወርቅ ምንጭ የመጀመሪያው ሐረግ አላልቶ ከማንበብ ይመነጫል። ‹‹በይ ስፊልኝ ገሳ›› የሚለው ሲላላና ‹‹ፊ›› በ ‹‹ቪ›› ስትቀየር ‹‹በይ ሲቪል ይንገሣ›› የሚል ትርጉም ይሰጣል። ይሄ ለወታደራዊው መንግሥት የሚያስቆጣ አዝማሚያ ነው። ከማስቆጣትም አልፎ የመጨረሻውን እርምጃ እንዲወስድ የሚገፋፋ ነው። እንዳልነው ነው! ቅኔ ምርጊቱ እንደተከፈተ ጠላ በጊዜ ሂደት ኃይሉን ሲያጣ ባለቅኔን ብቻ ሳይሆን ቅኔን በአግባቡ የመፍታት አቅምን ይነሳል። ስለዚህ ደርግ እነዚህን ጐናጭ ቅኔዎች ሳይረዳቸው በገዛ ሬዲዮኑ በየዕለቱ ሲያዘፍናቸው ቆይቷል።
ወደዚህ ዘመን እንምጣ…
…ይሄን ዘመን በንባብም፣ በእግርም የቻልኩትን ያህል አሰስኩ። ዘመኑ የወለዳቸውን ቅኔዎች ማግኘት አልቻልኩም። የቤተክህነት ትምህርት ወዳላቸው አንድ አዛውንት ሄጄ ነበር። ቅኔ በተላበሰ አኳኋን አተኰሩብኝ። አይንም ይቀኛል እንዴ? ግራ ተጋባሁ።
‹‹እንጃ ልጄ›› አሉኝ። አፋቸው እንጂ አይናቸው ተስፋ አስቆራጭ አልነበረም። እንዳሰብኩትም ‹‹ብቻ›› አሉ ‹‹ብቻ የጐንደር ቀሳውስት ለባለስልጣኖቹ የመወድስ ቅኔ አቅርበው ነበር ሲሉ ሰምቻለሁ››
እኔም ሰምቻለሁ፤ ጥር 11 2003ዓ.ም ጎንደር ከተማ ጥምቀት ሲከበር ፒያሳ አደባባይ ላይ ለአዲሱ ለገሠ፣ ለበረከት ስምዖንና ለአያሌው ጎበዜ ቅኔው ፈስሶላቸው ነበር፡፡
‹‹ተገቢ ነው፣ ይላሉ?›› ስል ጠየኳቸው፡፡
‹‹እሱስ ነባር ወግ ነው። እበላ ባይ ቄስ በየባላባቱ ደጃፍ ለውዳሴ ከንቱ ይቀኛል። ቅኔውም ያለው እዚህ ላይ ነው። ያሁኖቹን ባለስልጣናት እንደተላላ ባላባት ቆጥረዋቸዋል ማለት ነው።›› በዚያው በቅኔ አኳኋናቸው ጥርሳቸውን ሳያሳዩ ሳቁ።
የአዛውንቱ ንግግር ወደነዚያ ተማሪዎች መልሶ ወሰደኝ። ቅኔያቸውን በእዝነ ልቦናዬ ደገምኩት።
ቤተክርስቲያን እናት
ታላቅ መልእክት አላት
ምን ይሆናል የጐደላት
አንዳንድ ቅን-ቅን ካህናት።
ቅኔው የደምረው ሱራፌል ነው። በወቅቱ ሢሦ መንግሥት የነበራት ቤተክርስቲያን ለአገዛዙ ያላትን ጥብቅና በመመልከት አንጀታቸው ከሚያረው ተማሪዎች ብዙ ቅኔ ወደካህናቱ ይወነጨፍ ነበር። አንዱን እንድገምና መለስ እንበል። ቅኔው የአክሊሉ ወልደአማኑኤል ነው።
አባቶቻችን ካህናት
ሲጠመጥሙ ከጥንት
ለሥልጣናቸው ለክህነት
መለያ ነበር ምልክት
አሁንማ ጠምጣሞቹ
ሹሞቹና ጠበቆቹ።
ለዚህ ዘመን የቅኔ ድርቅ ወደ አጐራባች ዘመን ቃርሚያ መማተር ይመስላል። ደግሞም ነው። ይሄንን ዘዴ ተጠቅሞ አንድ ጥሩ አልበም ያቀረበ ድምፃዊ አውቃለሁ። አንጋፋው አርቲስት ተሾመ ምትኩ። ተሾመ የጥንቶቹን ቅኔዎች ለዚህ ዘመንና ብጤት እንዲስማማ አድርጐ ቀድዶ በመስፋት ‹‹ሺራሮ›› በሚል ርዕስ አቅርቦልን ነበር። አጠቃላይ ሥራውን ወደፊት እመለስበታለሁ። አሁን እጅግ ያስደነቀችኝን አንድ የዚህ ዘመን ቅኔውን ጀባ ልበላችሁ።
እባቡን የእባብ ዘር እባብ በላውና፣
መዳህኒቱ ጠፋ እርስ በእርስ ሆነና፡፡

Add new comment

Filtered HTML

  • Web page addresses and e-mail addresses turn into links automatically.
  • Allowed HTML tags: <a> <em> <strong> <cite> <blockquote> <code> <ul> <ol> <li> <dl> <dt> <dd>
  • Lines and paragraphs break automatically.

Plain text

  • No HTML tags allowed.
  • Web page addresses and e-mail addresses turn into links automatically.
  • Lines and paragraphs break automatically.