ይድረስ ለሕወሓት ድርጅት
ከጥቂት ሳምንታት ወዲህ ስለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጤንነት የተምታቱና እርስ በርሳቸው የሚጋጩ ዜናዎች የውይይት መድረኮችን አልብሰውት እንደነበረ ታውቃላችሁ። ከተጋጩት ግማሾቹ፥ እንዲያውም ሁሉም፥ ታማኝነት የሌላቸው መስለውኝ ሳለ፥ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለጊዜው በሥራቸው ላይ ሊገኙ አልቻሉም” የሚል መንግሥታዊ መግለጫ ወጥቶ አነበብኩ። ቀጥሎ በሕክምና ላይ መሆናቸውን የሚገልፅ ከቤልጂግ የመጣ የራማ ድምፅ ተሰማ፤ እግዚአብሔር ይማራቸው።
በዚህ በልጅነት እድሜያቸው ካልማራቸው ግን፥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይመሩት የነበረው ወታደራዊ ድርጅት (ሕወሓት) ስለኢትዮጵያ የወደፊት ዕድል አዲስ ፈር ለመትለም አርቆ ለማሰብ ሙሉ ነፃነትና ዕድል ሊሰጠው አስቦ ይሆናል። ባለፉት ሃያ አንድ ዓመታት ድርጅቱና በውድም በግድም የሚደግፋቸው ሕዝብ በአንድ ወገን፥ የቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ በሌላ ወገን፥ ሆነን በቃላት አሎሎ ተደባድበናል። የድርጅቱ ሠራዊት በመሪው ትእዛዝ የሌላውን ወገን መሪዎች አስሯል፤ የረታ ፍትሕ ነፍጓቸዋል፤ ብዙዎችን ለሞት አብቅቷል። በሁለቱ ወገን ያለው ፍጥጫ እስካሁን አንዲት ምናን ያህል አልረገበም። ጋዜጣ ባነበብኩ ቊጥር የማየው እነዚያው የቃላት አሎሎ ሲወናጨፉ ነው። ሕዝቡ ሃያ አንድ ዓመት ሙሉ ውስጣዊ ሰላም ተነፍጎ ነበር ማለት ነው። ከሓዲ ካልሆነ ለዚህ ማስረጃ የሚፈልግ ሰው አይኖርም። ይህን አላስፈላጊ ፍጥጫና ጥላቻ እስከመቸ አንከባክቦ ማኖር ይቻላል? ለምንስ ይጠቅማል? ያለነውኮ በመላው ዓለም ላይ የዲሞክራሲ ጮራ በፈነጠቀበት በሃያ አንደኛው ምእት ዓመት ነው። ጭቆና የሰብአትካት እንጂ የሥልጣኔ መሪዋ የኢትዮጵያ ልጆች ጠባይ ሊሆን አይገባም። ጭቆና ወንጀል ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የወረደባቸው የቃላት አሎሎ ስላቈሰላቸው፥ ቂም ይዘው፥ እልሕ ገብተው ስለነበረ፥ ዕርቅ ለማውረድ ባያስቡበት ሊገርመን አይገባም። ያ ዕድል የዛሬ ሃያ አንድ ዓመት አዲስ አበባን የያዙ ዕለት አምልጧል። በዚያ ጊዜ ያልፈራቸውን ሕዝብ ስለፈሩት ፍጥጫ የሚፈጠርበትን ሁኔታ ማዘጋጀታቸው አይረሳም። የሽግግር መንግሥት ቻርተር እንጻፍ ብለው፥ በሕዝቡ ላይ የስድብ ውርጂብኝ የሚያዥጎደጉዱ ቂመኞች ለቀውበት እንደነበረ ታስታውሳላችሁ።
“አገዛዜን ሕዝብ ይደግፈዋል፤ ሕዝቡ እኔንም ይደግፈኛል” ይሉት የነበረው ከእውነት የራቀ መሆኑን እሳቸውም፥ እናንተም፥ እኛም፥ እንዲያውም መላው ዓለም ያውቀዋል፤ አቶ መለስ እንደ ሙሶሊኒ፥ እንደ ሂትለር እና እንደ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም የተወደዱም የተጠሉም መሪ ነበሩ። ታሪክም የሚያስታውሳቸው እንደዚሁ ከነዚህ ከመሰሎቻቸው ጋር ነው። ታሪካቸውን በዚህ መልክ ያስመዘገቡት ተገድደው ሳይሆን ወደውና ሌሎችን አስገድደው ነው። የሚያነቧቸው መጻሕፍት ሕዝብን እንዴት አፍኖ መግዛት እንደሚቻል የሚያስተምሩ እኩያን የሰፊ ሕዝብ ጠሮዎች የጻፏቸውን ነው። ታዲያ ሕዝብ ምን አይቶባቸው ይደግፋቸዋል? ኢትዮጵያንም ሆነ ሕዝቧን እና ምድሯን እየበደሉ እንዴት ይደግፋቸዋል?
አሁን ግን እንደተነገረው በሥራ ላይ ከሌሉ፥ የሌሉት ለዕርቅ ደንቃራ የሆኑትን ቂማቸውንና እልሓቸውን ይዘው ነው። እሳቸው የያዙትን ይዘው ገለል ስላሉ፥ ብሔራዊ ዕርቅ ለማውረድ ድርጅታቸው ሊታለፍ የማይገባው ዕድል ተሰጥቶታል። የዕርቅ በር ከፍቶ ወደፊት በመገሥገሥ ፈንታ፥ ባለበት ረግቶ፥ ሌላ መለስ ዜናዊ እንዳይሰጠን ድርጅቱን አሳስባለሁ። ሐሳቡን ያቀረበውን ሰው ትታችሁ ሐሳቡን አስቡበት።
አንድ ጨቋኝ ሲያልፍ ግብረ አበሮቹ የተሻለ ዘመን እንደሚያመጡ የብዙ አገሮች ታሪክ አሳይቶናል። በሀገራችን ዕርቅ በፈቃድ የማምጫው ጊዜ አሁን ነው። በኃይል የተገለበጠና በፈቃዱ ዕርቅ ያመጣ ባለሥልጣን ዕድላቸው የተለያየ እንደሆነ ግልጽ ነው። ይኸንን ለማየት የሕወሓት ሰዎች ሊያቅታችሁ አይገባም። ዕርቅ፥ ዲሞክራሲ እና ነፃነት ጥቅማቸው ለሕዝብ ብቻ ሳይሆን ለገዢውም አካል ነው። እስቲ እንሞክራቸውና የሚሆነውን እንይ።
የሚሆነውን ለመገመት ግን አያስቸግርም፤ ሰብአዊ መብት ከተከበረ፥ ላምና አንበሳ፥ አህያና ጅብ፥ ምጥማጥና ዶሮ፥ አብረው ይውላሉ፤ አብረው ያድራሉ። የጨቆኑና የተጨቆኑ ያለፈውን ረስተው ሳይፈራሩ በሀገር ልጅነት፥ በወንድማማችነት አብረው ያመሻሉ። ባላንጣዎች አብረው ይዘምታሉ። ሊቃውንቱ፥ ምሁራኑ፥ መምህራኑ ችሎታቸውን ለነፃነት ከመታገል ላይ ቀንሰው ድኽነትና ድንቁርና ከሚጠፉበት ላይ ያውላሉ፤ ልዩነቶች ከጉዳት ወደ ጥቅም የሚለወጡበትን ዘዴ ለመፈለግ የተረጋጋ መንፈስ ያገኛሉ። ኢትዮጵያ የሚቀርቧት እንጂ የሚርቋት ሀገር መሆኗ ይቀራል። ሀገሪቱ ያስተማረቻቸው ልጆቿ በስደት ሌላ ሀገር ከማገልገልና ሀገራቸውን ከመናፈቅ ይድናሉ። በትምርት አንጻ ያሳደገቻቸው ልጆቿ ሌላ ሀገር እንዴት እንደሚያገለግሉና የተሰደዱበትን ሀገር እንደሚያዳብሩ በሰፊው ተነግሯል። ብዙዎች በምርምር ያገኙት ለእድገት የሚጠቅም ግኝት በስማቸው ተመዝግቦላቸዋል። አሁን በቅርቡ እንኳን የአሜሪካ ላዕላይ ፍርድ ቤት የፕሬዚዴንት ኦባማን የሕዝብ ጤና ጥበቃ እቅድ ደግፎ ሲፈርድ የኢኮኖሚ ጥቅሙን ያሳየው የዶክተር ብርሃኑ ዓለማየሁን ምርምር ጠቅሶ መሆኑ በፍርድቤቱ አፍ ተነግሯል።
በጎሳ፥ በቤት የከፋፈላችሁን የቤቶችን መብት ለማስከበር እንደሆነ ታምናላችሁ። ቤቶቹ ካላመኑበት የናንተ እምነት አዲስ ሃይማኖት እንደማስተማር ይቆጠራል። ጥቂት ጥቅመኞች ለይምሰል ያህል የተቀበሉ ቢመስሉ አትታለሉ። ሕዝቡ ለመቀበሉ ማስረጃ አይሆኑም። እንዲያውም፥ ልብ አላላችሁትም እንጂ፥ ልብ ብትሉት፥ በጎሳ በዘር መከለል ከመጣ፥ ሀገሪቷ ብቻ ሳትሆን፥ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ብዙ ክልሎች ይወጣዋል።
ሕወሓቶች አስቡበት፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲሄዱ፥ “ቂሜን፥ እልሔን አደራ” ብለዋችሁም እንደሆነ፥ እሳቸውን በሌሉበት ከመታዘዝ ከአገር ልጆች ጋር በሰላምና በጤና አብሮ መኖር ይብስብናል ብትሉ፥ ዓለም በጀግንነትና በአርቆ አስተዋይነት ይመዘግባችኋል እንጂ፥ ማንም በአደራ በላነት አያማችሁም። ዕድል አምልጧችሁ የሚተገትገን፥ የምንተገትገው ሌላ ተጠልቶ የሚያስጠላችሁ መሪ አታምጡብን። የብዙዎችን ጎባጣ መንገድ ያቀና የወንድሞቻችሁ የእኅቶቻችሁ አምላክ፥ የሰላም ጌታ ቀናውን ይምራችሁ።

Add new comment