ጠላታችን ማነው?

ዓለማየሁ ገላጋይ

ሮማዊው የታሪክ ሰው Tranquillus suetonius (75-150)ዓ.ም “Lives of the twelve Caesars” የሚል መጽሐፍ አለው። የአሥራ ሁለት ቄሳሮችን ስንክሳር ያካተተበት ሥራው ነው። ከእነዚህ ቄሳሮች መካከል ‹‹እብዱ›› በሚል ተቀጥላ የሚጠራው ካሊጉላን (Caligula) ነው። በእርግጥም አንዳንድ የቄሳሩ ተግባሮች ጤነኞች የሚያከናውኗቸው አይደሉም። ለምሳሌ መኳንንቱና ሹማምንቱ እንዲሁም መሳፍንቱ በተገኙበት አዳራሽ ውስጥ ሚስቱ ቄሶኒያ (Caesonia) እርቃነ-ሥጋዋን እንድትመጣ ያዝዛታል። ልብሷን ጥላ እራቁቷን ስትመጣ የአዳራሹን ሁናቴ ይቃኛል። ከዚህ የሚያገኘውን ትርፍ እራሱ ካሊጉላ ይወቀው። ሌላም የእብድ መዝናኛ አለው። በመኳንንቱ ፊት መኳንንቱ እርስ በእርስ ትግል እንዲገጥሙ ማዘዝ። አንዱ ይጥላል፣ ሌላው ይወድቃል። ካሊጉላ ይስቃል። ቄሳሩ ከሳቀ የተቀረው መኳንንት አያኮርፍም- አብሮ ያውካካል። ከዚህ ትዕይንት ካሊጉላ የሚያተርፈው መዝናናትን ብቻ አልነበረም። ፖለቲካዊ ረብጣም አለው። የወደቀው መኳንንት በጣለው መኳንንት ላይ ያቄማል፤ ጠላትነትም ያበቅላል። እርስ በእርስ ተፈላላጊ ይሆናሉ።

ወደኛ አገር እንምጣ… …ፊታውራሪ ተክለሐዋርያት ተክለማሪያም ‹‹ኦቶባዮግራፊ (የህይወቴ ታሪክ)›› የተሰኘ መጽሐፋቸው ላይ የሚያስተዋውቁን ልጅ ኢያሱም የካሊጉላ ከፊል መንፈስ ያረፈባቸው ናቸው። የተከበሩትን መኳንንቶች ለእረኝነት እንደወጣ ኩታራ ትግል ያጋጥሟቸዋል። ፊታውራሪ ተክለሐዋርያት እንዲህ ይላሉ፡-

‹‹… ታዲያ ልጅ ኢያሱ ቀኛዝማች ወልደአማኑኤልንና ቀኛዝማች ፋሪስን አታገሏቸው። ቀኛዝማች ወልደአማኑኤል በንቀት አስተያየት እያየ ተጋጠመ። (ቀኛዝማች ወልደአማኑኤል በራስ መኮንን ቤት ጉልበታምነቱ የታወቀ ነው።) ቀኛዝማች ፋሪስ ጣለ፣ ልጅ ኢያሱ እያጨበጨቡ ደስታቸውን ገለጡ። እኛ ግን ዐፈርን። ቀኛዝማች ወልደአማኑኤል ተገረመና እንደገና ታገሉ። ቀኛዝማች ወልደአማኑኤል ጣለ።››

በፊታውራሪ ተክለሐዋርያት ግምጋሜ ልጅ ኢያሱ ለመቦረቅ ያመጡት የልጅነት ፍላጐት እንጂ የመኳንንቱን ትግል መግጠም በፖለቲካ ትርፍነት አይተውት አልነበረም። ይሁንና ለታዛቢዎቹ ለእነፊታውራሪ ተክለሐዋርያት ትግሉ ከግለሰቦች አልፎ ብሔርና ሃይማኖት ተኮር ሆኖ ተተርጉሞላቸዋል። በቅንፍ ውስጥ ይሄንን ትርጓሜ ጣል ያደርጋሉ። ‹‹በልባችን ውስጥ የሚታገሉት ወልደአማኑኤልና ፋሪስ አይደሉም ሸዋና ወሎ፣ ክርስቲያንና እስላም ናቸው (አልን)›› ይላሉ። የዚያ ወቅት ፖለቲካ ይሄው ነበር። ከሸዋ ወገን እነደጃዝማች ተፈሪ (ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ)፣ ከወሎ እነራስ አሊ (ንጉስ ሚካኤል) የተፋጠጡበት። ትውልዳቸውንና ሃይማኖታቸውን የወከሉት ቀኛዝማቾች በግጥሚያው አንድ ለአንድ ባይወጡ ምን አይነት ቂም ውስጣቸው ይፈጠር ነበር? በእንዴት አይነት ሁኔታስ ወደበቀል ይለወጥ ነበር?

አብዛኛው መንግሥት የራሱን ፖለቲካዊ ሁኔታና ሥልጣን የሚያስጠብቀው ትኩረት የሰጠባቸውን ‹‹ቀኛዝማች ወልደአማኑኤል እና ቀኛዝማች ፋሪስ›› በጠላትነት አኳኩኖ በማታገል ነው። ለምሳሌ በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን የነበሩ ትግል ገጣሚዎች ‹‹በተወላጅነት›› እና ‹‹በትምህርት›› ሥልጣን የያዙ ሁለት ቡድኖች ነበሩ። የእነዚህ ቡድኖች ጠላትነት በአፄ ኃይለሥላሴ የሥልጣን ማስጠበቅ ፖለቲካዊ ፍላጐት የተፈበረከ ቢሆንም ደርግ እስኪመጣ ድረስ እንደተናነቁ ሥራ መሥራት ተስኗቸው ቆይተዋል። አንዴ አንዱ ሲጥል አፄ ኃይለሥላሴ እንደልጅ እያሱ ያለ ግን ስውር ጭብጨባ በማካሄድ ደስታቸውን ሲገልጡ፤ ሌላ ጊዜ ሌላው ሲጥል እንዲሁ ሲደረግ በመካከል ዋነኛው የንጉሱ ሥልጣን ከመካከላቸው የሚማትረው ሳይኖር ለረጅም ጊዜ ቆይቷል። ስለዚህ ጉዳይ ባህሩ ዘውዴ እንዲህ ይላሉ፡-

‹‹የአብዛኛዎቹ ሚኒስትሮች የመደብ ጀርባም በንጉሰ ነገሥቱ ፊት ነፃ አቋም ለመውሰድ የሚያደፋፍር አልነበረም። ብዙዎቹ የመሣፍንት ወገን ባለመሆናቸውና ሹመቱና ክብሩንም በቀጥታ ከንጉሠ ነገሥቱ ያገኙ በመሆናቸው ታማኝነታቸው የተረጋገጠ ነበር። በዚህም አኳኋን ንጉሠ-ነገሥቱ ሚኒስትሮቹን የመሣፍንቱን ኃይል ለመቋቋም አይነተኛ መሣሪያው አድርጓቸው ነበር። የድህረ 1933 የኢትዮጵያ ፖለቲካ አንዱ ገፅታ ይህ በመኳንንቱና በመሣፍንቱ መካከል ይካሄድ የነበረው ስውር ትግል ነበር ማለት ይቻላል።›› (‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ…›› ገፅ 213)

በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን በጠላትነት ትግሉን የገጠሙት ከመኳንንቱ ወገን ልዑል ራስ ካሣ ኃይሉ ሲሆኑ ከሚኒስትሮች ወገን ደግሞ የእርሻ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር የሆኑት መኮንን ኃብተወልድ ናቸው። ሁለቱም በሥራቸው የስለላ ቡድን በማቋቋም አንዱ የሌላውን ድክመት ሲያነፈንፍ ይውልና ያድር ነበር።

በደርግ ዘመን ‹‹ቀኛዝማች ወልደአማኑኤልም ሆነ ቀኛዝማች ፋሪስ›› እራሱ ደርግ ነበር። ለጠላት ሌላ ጠላት ፈጥሮ ከማታገል ይልቅ አድሀሪ፣ በዝባዥ፣ ከላሽ፣ ቀልባሽ፣ ገንጣይ፣ አስገንጣይ… የሚለውን እራሱ እጅጌውን ሰብስቦ ይገጥማል። ከጣለ በኋላ በአዋጅ ይፎክራል። የሚወረሰውን እራሱ ይወርሳል፣ የሚገደለውን እራሱ ይገድላል፣ የሚሾመውን እራሱ ይሾማል…። በሽኩቻ ጠላት በጠላት እስኪጣፋ አይጠብቅም፣ ትዕግሥት የለውም። ዘው ብሎ እራሱ አጣጥሞ ቁልጭ ለማለት ይፈጥናል።

ወደዚህ ዘመን እንምጣ…

…ከሁሉም ዘመን እጅግ የከፋው የዚህ ወቅት ሽኩቻ ነው። ያለማጋነን ህዝቡ እንዳለ ‹‹ቀኛዝማች ወልደአማኑኤሎችንና፣ ቀኛዝማች ፋሪሶችን›› እንዲሆን ተጥሯል። በብሔር፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በክልል አስተዳደር፣ በፖለቲካ… እየተናነቀ ሙሉ ትኩረቱን አጠገቡ ያለ ወገኑ ላይ እንዲያደርግ እየተሴረ ነው። በገዢዎች የተመደበለትን ተጋጣሚ የመጣል ባዕድ ትልም ግቡ አድርጐ እንዲቀርና ወደላይ እንዳያማትር በዕለት ተዕለት ሽኩቻ እርስ በእርሱ እንዲጠላለፍ ተደርጓል። ከበድ ያሉትን አገር አቀፍ ጉዳዮች ትተን በህግ፣ በፖሊሲና በደንብ እየታከኩ የሚጠሩትን የእርስ-በርስ ጠላትነቶች እንመልከት።

የልማት ተነሺ በመሆናችን ስንት የቀበሌ ነገሥታት እያጣደፉና እያክፋፉ እንድንጠላቸው አደረጉን? መኖሪያችንን በላያችን ላይ ለማፍረስ ሲቋምጥና ሲቁነጠነጥ በማየት ስንት አፍራሽ ግብረኃይል ላይ ቂም ያዝን? ስለመፈናቀሉ
በመደስኮር በቁስላችን እንጨት እየሰደደ ስንቱ ጠላታችን ሆነ? በቤት ግምት ወሽመጣችንን ከቆረጠ ስንት ባለስልጣን ጋር ተቂያቂያምን? ያልተገባ፣ የተጋነነ የቤት ግምት የወሰደ ስንት ጐረቤት ታዘብን?...

….ደግሞ በተከራይ አከራይ ያልተብላላ ደንብ ስንቱ ተባላ? ስንቱስ ስንት የዘለአለም ባላጋራ አፈራ? ምን ያህሉስ ለመጋደል ተፈላለገ? እኔ እንኳን ሦስት አሰቃቂ የተከራይ አከራዮች ጭፍጭፍ አጋጥሞኛል። ሃያ ሁለት አካባቢ ገብርኤል ሆስፒታል መስመር፣ አትክልት ተራ እና ካሳንቺስ። ካልወረስክ መንግሥት ይወርሰዋል የተባለ ተከራይ ምርጫ በማጣት ከአከራዩ ጋር ጥርስ ከተናከሰ በኋላ እንደገና መልስለት በሚል የመንግሥት ትዕዛዝ ነው እንደጐሣ ወረራ በገጀራ ሲጨፋጨፉ የታዩት።

….እናስ? ልጅ ኢያሱ ያታገሏቸውን ቀኛዝማች ወልደአማኑኤልንና ቀኛዝማች ፋሪስን አልሆንም? ያታገለንን ትተን የታገለንን አልጠላንም? ከመታገላችን የሚያተርፈውን ‹‹የፖለቲካ ቁማርተኛ›› አልፈን የኛ ብጤ ሰለባውን ጠላት አላደረግንም? ለመሆኑ ጠላታችን ማነው?

Comments

Since Lij Iyasu was fond of jokes it is no wonder if he lure his nobility into wrestling.Teklihawryat cynically misinterpreted this as politically motivated. Ato Alemayehu Gelagay misconceived this anecdote as a metaphor which can be applied to the divide and rule tactic of Ethiopian regimes. The use of old propaganda to analyze the new political condition makes the article superficial.

ዝግ ብለህ እንደገና አንብበው፤ ልጅ ኢያሱ እንዳልተደላደሉና ተቀናቃኝ እንደነበራቸው ረሳኸው መሰለኝ። ሌላው ቢቀር የመኳንንቱን ሚስት ይደፍሩ የነበረው አንደኛው ምክንያት አዋርዶ ለማንበርከክ ጭምር ነበር። ሥልጣን የተገባቸው የመሰላቸው ሁሉ፣ ሌላ መተኪያ እንደሌለ በሚያስቡ ሁሉ ዘንድ ይህ ስልት የኖረ ስልት እኮ ነው። የዓለማየሁን ትንታኔ ለምን ፕሮፓጋንዳ እንዳልከው አልገባኝም። ተክለሃዋርያት የዘገቡት ምን ሌላ ዓላማ ይኖራቸዋል ብለህ ታስባለህ? ጽሑፉን ደግሜ ባነበውም አንተ ያልከው አልታይህ አለኝ። ድምዳሜህ ችኩል ድምዳሜ መሰለኝ። እስቲ ቀስ ብለህ አንብበው። ካልሆነም፣ ጸሐፊው ያብራራ ዘንድ እጠይቀዋለሁ።

dedeb

Ato Abiy, it is very clear that you have neither read in depth, and have a full knowledge of Fitawrari Tekle Hawariat's work, if at all . Fitawrari was never a "cynically" motivated interpreter of Ethiopia's history his life time. He lived it VERY CLOSE! In fact, Fitawrarie was, as the details in his book show, a learned observer and a highly capable participant in very important historical junctures in our history.

Secondly, the writer of the article in discussion neither misconceived, nor tried to make an inappropriate deduction. Indeed, Ato Sisay made a good reflection on issues of historical symbolism and their relevance to understand the psychology of a our society. It is a misjudgement on your part to call these informed reflections
"old propaganda" and the artcle "superficial"!
Sorry ato Abiy, I couldn't find anything of substance and educational in your comment. It may be helpful to avoid the tendency to hyphenate every idea with adjectives which are in this case a hindrance to dialogue.

Dear Alem, had you read the autobiography of Fitawarari Tekilehawariat you would have discovered Teferi was the major rival of Iyasu. In spite of the fact that Tekle ,was on the side of Iyasu, he finally defected to the Shewa nobility. Naturally,Tekle seems to have felt a pang of guilt sometimes later.And in his autobiography he tried to justify his betrayal by presenting Iyasu as an incompetent lad.Finally,you have accused Iyasu of adultery with the nobility.Since you don't to support this with any evidence I can say you are also a victim of an old propaganda.

good article. i relay appreciate the writer. This kinds of articles helps a lot

ጠላታችን በሚል ርዕስ መጻፉ አልተመቸኝም። የዚያ ዘመንም ሆነ ያአሁኑ መሪዎች ቢያጠፉም ጠላት የሚል ቃል ተጠቅሞ መጻፉ ያስከፋል።ይህ በኢትዮጵያ ወጣቶች አዕምሮ የሚፈጥረዉ መንፈስ መልካም የሚሆን አይመስለኝም።እርግጥ ነዉ ኢህአዴግ ስልጣኑን ለረጅም ጊዜ ለማቆያት በሚል ግልጽ አላማ ልዩነታችንን በብዙ እጥፍ አብዝቶታል። ብዙ ከፋፍሎናል።ህዝቡ እርስ በርሱ እንዲጠላለፍ ተደርጉዋል። ነገር ግን እኛ ኢትዮጵያዊያን ዘር ሀይማኖት ሳይገድበን ለብዙ ዘመናት በደም በስጋ የተሳሰረ የጋራ ማንነትን ገንብተናል። ይህ እዉነታ መሪ በተቀያየረ ቁጥር እንደማይለወጥ ለዘመናት ባሳለፍናቸዉና ኢህአዴግ እንዲከር ባደረገብን ፈተናዎች ተፈትነን አልፈነዋል።አሁን ያለዉ ያዘረኝነት ፈተናም የከፋ ነዉ።እዉነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ጠላታችን እያሉ መጻፉን አልወደድኩትም። ፍቅር ያሸንፋል!

Both Ato Abiy & Abiy Dagmawi, unless you are reading your own version of Fitawrari Tekle Hawariat's book, you couldn't have come to such a historically false premise and conclusion. Fitawrari was an ardent Ethiopian who didn't succumb to your concept of political servitude. Indeed all his life long, he lived a dignified Ethiopian without bowing to anyone, except to the God of his fathers.
It seems that "both" Abiys are on a version of "Ethiopian history" which is alien to Ethiopia and is replete with unhelpful polemics.
Ato Alemayehu has done a very good concise rendition of the salient ideas of Fitawrari Tekle Hawariat to make it useful to understanding our historical and contemporary times.

እባካችሁ በፍቅር እንኑር እግዚአብሄርም የምንፈልገውንና የጠየቅነውን ሁሉ የሚመልሰው እርስበርሳችን ስንዋደድ ነውና፡፡

Add new comment

Filtered HTML

  • Web page addresses and e-mail addresses turn into links automatically.
  • Allowed HTML tags: <a> <em> <strong> <cite> <blockquote> <code> <ul> <ol> <li> <dl> <dt> <dd>
  • Lines and paragraphs break automatically.

Plain text

  • No HTML tags allowed.
  • Web page addresses and e-mail addresses turn into links automatically.
  • Lines and paragraphs break automatically.