“አኬልዳማ”ው የአይሁድ ወይስ የኢህአዴግ?

“አኬልዳማ”ው የአይሁድ ወይስ የኢህአዴግ?
ተመስገን ደሳለኝ

አኬልዳማ-የደም መሬት፡፡ አኬልዳማ የእብራይስጥ ቃል ነው፡፡ የአማርኛ ትርጓሜው የደም መሬት የሚል ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
የመለስ መንግስት ምን እንደነካው እንጃ ብቻ መሬት መሬት ብሏአል፡፡ የኢንቨስተር መሬት፣ የሪል እስቴት መሬት፣ የአባበ እርሻ መሬት፣ የሩዝ መሬት፣ ለህንድ የተሰጠ መሬት፣ ለሳውዳአረቢያ የተሰጠ መሬት፣የሊዝ መሬት፣ የደም መሬት (አኬልዳማ)...፡፡ በእርግጥ መንግስት እስከዛሬ ድረስ ..መሬት..ን የሚያየው ሸንሽኖ ከመሸጥ አንፃር ብቻ ነበር፡፡ ሰሞኑን ደግሞ የፊልም ርዕስ አድርጎታል፡ ፡ ... አኬልዳማ-የደም መሬት፡፡
ጥቂት ስል አኬልዳማ፡- በክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተተረከው አለምን ለማዳን የመጣው ኢየሱስ ክርስቶስ ወጌልን በሚሰብክበት ወቅት 12 ደቀመዛሙርት (ተከታይ ጓደኞችን) መርጦ እንደነበረ እናነባለን፡፡ በመጨረሻም ከእነዚህ ተመራጮች አንዱ የሆነው የአስቆሮቱ ይሁዳ የመረጠውን፤ ያከበረውን ኢየሱስ ክርስቶስን በ30 ዲናር ለጥላቶቹ ሸጠው፡፡ ሆኖም ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ይሁዳ ንፁህ ወዳጁን አሳልፎ እንደሰጠ ገባውና ተፀፀተ፡፡ ተፀፅቶም አልቀረ የተቀበላትን 30 ዲናር ለገዢዎቹ መለሰላቸው፡፡ ገዢዎቹም ..ካልፈለክ ተወው.. የራስህ ጉዳይ ነው.. ብለው ገንዘቡን ከተቀበሉ በኋላ መሬት ገዙበት፡፡ እነሆ ያ መሬት በወዳጁ በተሸጠ ንፁህ ሰው ደም የተገኘ መሬት በመሆኑ ዛሬም ድረስ “አኬልዳማ” (የደም መሬት) እየተባለ ይጠራል፡፡
ይሄ ከሆነ ከሁለት ሺ አመት በኋላ የኢትዮጵያ ገዥ ፓርቲ “አፍ” የሆነው ኢቲቪ፤ የገዢው ፓርቲ “ጠላቶች”ን ወንጀል የሚተርክ ፊልም አዘጋጅቶ ወይም ጣጣ ፈንጣጣው ያለቀለትን ፊልም ተቀብሎ “አኬልዳማ” በሚል ስም ለሶስት ቀን ያህል አሳይቶናል፡፡ በእርግጥ ያ በክርስቶስ ደም የተገኘው የ”አኬልዳማ” ትርጓሜ እና የኢቲቪ የፊልም ጭብጥ ሀራምባና ቆቦ ነው፡፡ ምክንያቱም የአይሁድ ካህናቶች “አኬልዳማ” ያሉት መሬት የተገዛው ይሁዳ የተባለ ሰው፤ ክርስቶስ የተባለውን ወዳጁን ሸጦ ባገኘው ገንዘብ ነው፡፡ የኢህአዴግ “አኬልዳማ” ጭብጥ ደግሞ ከሀገር በቀሎቹ እስከ አልቃይዳ፣ አሊ-ታሀድ፣ ሻዕቢያ፣ አልሼባብ... ድረስ ያካተተ ነው፡፡ እናም የፊልሙ እርስ የፊልሙን ጭብጥ ሊወክል ይችል የነበረው በፊልሙ ላይ አንዳርጋቸው ፅጌ፣ ብርሃኑ ነጋን አሳልፎ ሲሰጠው የሚታይ ቢሆን ኖሮ ነበር፡፡ ወይም አልቃይዳ ተተኪ ሊቀመንበሩን አይማን አልዛሃዋሪን ሲሸጥ የሚያሳይ መሆን ነበረበት፡፡
የሆነ ሆኖ በአኬልዳማ ፊልም ላይ የሚጣረሱ ነገሮች በመኖራቸው “ሂስ” መስጠቱ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ሌላው ቢቀር ዳሬክተሩ እና ደራሲው በሚቀጥለው ለሚያዘጋጁት ዶክመንተሪ ፊልም ገንቢ አስተያየት ሊያገኙ ይችላሉና፡፡ መማር ከፈለጉ ማለቴ ነው፡፡ አሊያ እንዲህ እንዳየነው አይነት ቀሽም ፊልም እየሰሩ መሳቂያ መሳለቂያ መሆን ነው፡፡ መቼም የዚህ ፊልም ደራሲ እና ዳሬክተር እንደእነ ሠራዊት ፍቅሬ እና ጓደኞቹ ሰማያዊ ፈረስ፣ ሄሮሺማ፣ አባይ ምናምን ቬጋስ... እንደሚሉን “አርቲ-ካድሬ”ዎች አይደሉም፡፡ እነዚህኞቹ (የአኬልዳማ ባለቤቶች.. ፊልም የሚሰሩት ገንዘብ ለማግኘት አይደለም፡፡ ገንዘብ ሞልቶ የተረፋቸው ናቸው፡፡ ገንዘብ ከፈልጉም እንኳ ከፊልም ይልቅ በጥቂቱ የታክስ ጭማሪ ቢያደርጉ ገቢው የትየለሌ እንደሆነ ከልምድ ያውቁታል፡፡ እናም እነሱ ፊልም የሚሰሩት ሲያሻቸው ታክስ እንዲጨምሩ፣ ሲያሻቸው መሬት እንዲሸጡ፣ ሲያሻቸው ከትዳር ጓደኛቸው ጋር በሚሊኒየም አዳራሽ እንዲደንሱ፣ሲያሻቸው... ብቻ የፈቀዱትን ለማድረግ የሚያስችላቸውን እና የሚንደላቀቁበትን “ስልጣነ መንግስት” ለማስጠበቅ ነው፡፡ ...ማንነታቸው ላይ መነጋገሩ እዚህ ይገታና ስለፊልሙ እናውራ
ከጭብጡ እንጀምር፡፡ እንግዲህ የወቅቱ ፖለቲካ “አሸባሪ” እና “ሽብርን መከላከል” እንደሆነ ግልፅ ነው፡፡ እናም አሸባሪ በሚል ጋዜጠኞች፣ ፖለቲከኞች፣ መንገደኞች... በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡ ይህንን ተከትሎም መንግስት ሰዎቹን ያሰራቸው ስለተቹት እና ስለተቃወሙት እንጂ አሸባሪ ሆነው አይደለም የሚል ተቃውሞ ከውስጥም ከውጭም መነሳት ሲጀመር፤ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ሰዎቹ የተያዙት በበቂ ማስረጃ መሆኑን ገልፀው በሁለት ሳምንት ውስጥ ማስረጃውን ለህዝብ ይፋ አደርጋለሁ አሉና ተቃውሞውን አስተባበሉ፡፡ ሆኖም ከአምስት ሳምንት በኋላ ማሰረጃ የተባለው “አኬልዳማ” በሚል ስም የቀረበ ፊልም ሆነ፡፡ (ምናልባትም የፊልሙ ደራሲ ራሳቸው አቶ መለስ ሊሆኑ ይችላሉ)
ብዙሃኑም ፊልሙን በንቃት ተከታተለ፡፡ የቴሌቪዥን ኤቲክስ (ስነ-ምግባር) እንደተጠበቀ ሆኖ ማለቴ ነው፡፡ ምክንያቱም ሆሊውድ የሚሰሩ አስፈሪ ፊልሞች እንኳ ቢያንስ ከ16 አመት በታች እንዳያዩት የሚከለከል ሆኖ እያለ፤ ኢቲቪ ደግሞ የተቆረጠ አንገት፣ የተገነጠለ እጅ፣ የተፈረከሰ ጭንቅላት... እያሳየ 13 ዓመት የሞላው በሙሉ ሊያየው ይችላል ይላል፡፡ ያውም ሲኒማ ቤት ሳንሄድ እቤታችን ድረስ መጥቶ ማለቴ ነው፡፡
...ወደ ጭብጡ እንመለስ፡፡ የመለስ መንግስት “አሸባሪ” ብሎ ለአሰራቸው ጋዜጠኞች እና ፖለቲከኞችም ሆነ እየተፈለጉ ባሉት ያልተያዙ “አሸባሪዎች” ላይ በአኬልዳማ ፊልም ከቀረበው አንዱ ማስረጃ መላ ቤተሰባቸውን ያጡ አንድ ግለሰብ በሚሰጡት ምስክርነት የሚጀምር ነው፡፡ ግለሰቡ ባለቤታቸው እና ልጆቻቸው በኦነግ እንደተገደሉ የሰጡትን ቃል ነው በአኬልዳማ ፊልም ያየነው፡፡ ሆኖም በፊልሙ የቀረበውን አልደግመውና፤ ኢቲቪ ከሰውየው ቃል የቆረጠውን ቀጥዬ፤ ሰውየው የተናገሩትን ሙሉውን እንደወረደ ላውርድላችሁ፡-
“...ዘጠኝ ቤተሰቤን ወሰዱብኝ፡፡ ቀጥቅጠው ባለቤቴንም ገደሏት፡፡ የእኔ ወንድሞች ልንገራችሁ ባለቤቴን ገደሉብኝ፤ 34 አመት አብረን የነበረን፤ ለንብረቴ አላለቀስኩም፡፡ ስሜንም አልገልፅም፡፡ እናንተ ሄዳችሁ እዩት ሽባ ልጅ፣ አይኑ የፈሰሰ፣ እጁ የተሰበረ ልጅ መልሰውልኛል አሉ፣ አላየኋቸውም እኔ፡፡ የእኔ ወንድሞች ብትተውኝ ጥሩ ነው፡፡ ትንሽ አንጎሌ ልክ አይሰራም፡፡ እና ይሄ ነው ድርጊቱ፤ የሚደረገው ድራጎት የከተማ ወሮበላን አስታጥቀው ህዝቡን ፈጁት፡፡ አምስቱን ጓደኞቼን ገደል ከተቷቸው፡፡ የጓደኛዬን ሚስት እና የእኔን ሚስት ገደሉ፣ እንዲህ ያለ ግፍ ይሰራል፡፡ ይሄን ሁሉ የሚያደርገው መለስ ዜናዊ ነው” የሚል ነው፡፡ (ኢቲቪ የቀረፀው ይሄ ፊልም እኔም ጋር አለ ምናልባትም ኢቲቪ ጠፍቶበት ከሆነ ቆራርጦ ያቀረበው ላውሰው እችላለሁ፡፡)

ስለቃል ሰጪው ሰውየ ደግሞ ትንሽ ልንገራችሁ፡- አቶ ይርጋ ይመር ይባላሉ፡፡ ነዋሪዎነታቸው በኦሮሚያ አቡ ሴራ በተባለ የቀበሌ ገበሬ ማህበር ውስጥ ነው፡፡ አደጋው የደረሰባቸው በጥቅምት ወር 1984ዓ.ም ነው፡፡ በአደጋውም ባለቤታቸውን አልጋነሽ ጃራን፣ የ18ዓመት ልጃቸውን ሲሳይ ይመርን እና የ9 አመቱን አሸናፊ ይመርን አጥተዋል፡፡ እሳቸውን ጨምሮ ደግሞ በላይነሽ እና ወሰኔ የተባሉ ልጃቸው በጥይት ቆስለዋል፡፡ ሆኖም አደጋውን ያደረሱት ሰዎች ለጥቂት ጊዜ ተይዘው በዋስ ተለቀዋል፡፡ አቶ ይርጋ እስከ 2000 መጨረሻ ድረስ ፍትህ አለማግኘታቸውን እና መዝገቡ ተሰረቀ መባላቸውን በሰኔ ወር 2000ዓ.ም በወጣችው ፍትህ ጋዜጣ ላይ ተናግረዋል፡፡
አኬልዳማ ፊልም ሆዬ ደግሞ ለዚህ ሁሉ ተጠያቂው “መለስ ዜናዊ ነው” የሚለውን የተበዳይ አቤቱታ ቆርጦ፤ አደጋውን እና እነእስክንድር ነጋን እያፈራረቀ ያሳየናል፡፡ ምን ለማለት ፈልጎ እንደሆነ ግን ግልፅ አይደለም፡፡ መቼም ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ከበቂ በላይ ማስረጃ አለን” ያሉን ይሄንን ነው ብዬ አላስብም፡፡ ከሆነ ግን ደባ ራሱን፣ ስለት ... አይነት ነገር መሆኑ ነው፡፡
ሌላው ፊልሙ ሲፋቅ የምናገኘው ሀቅ አቶ ይርጋ እና ቤተሰቦቻቸው ላይ ይሄ አደጋ የደረሰው በ1984ዓ.ም በወርሃ ጥቅምት መሆኑን ነው፡፡ በዛን ጊዜ ኢትዮጵያን የሚያሰተዳድረው ወይም የሚገዛው ማን ነው? ደርግ ይሆን እንዴ? በጭራሽ፡፡ ደርግ ደግሞ በ1983 ነው የወደቀው፡፡ ...አሃ.. ትዝ አለኝ ለካስ “ጊዜያዊ መንግስት” የሚባል ተመስርቶ ነበር፡፡ እሺ! ይሄ ጊዜያዊ መንግስት በእነማን ነበር የተመሰረተው? ጥሩ ጥያቄ ነው፡፡ በኢህአዴግ እና በኦነግ በጋራ ነበር የተመሰረተው፡፡ ይሄም ጥሩ መልስ ነው፡፡ እንዲያውም በወቅቱ የኦነግ ሊቀመንበር ሌንጮ ለታ የመከላከያ ኮሚቴ ሰብሳቢ ነበሩ፡፡ (የመከላከያ ሚኒስትር እንደማለት ነው)
ያን ጊዜ እነ አንዷአለም አራጌስ የት ነበሩ? የአንዱአለም ሲቪ እንደሚነግረን ከሆነ፤አንዱአለም በወቅቱ የኮከብ ፅብሃ የ10ኛ ክፍል ተማሪ ነበር፡፡
እንግዲህ እግዜር ያሳያችሁ! ይሄ የኢቲቪ ፊልም አሁን በማን ላይ የሚቀርብ ማስረጃ ሆኖ ነው እንድናየው የተደረገው? ...ደህና! አኬልዳማን መመልከታችንን እንቀጥል፡፡
የአኬልዳማ ፊልምን ስናይ ከተወናያኖቹ አንዱ ጋሽ ደቤ በማዕከላዊ እስር ቤት ዘና ብሎ፤ የዶሮ አይን የመሰለ ቡናውን እየተጎነጨ ስለሽብር ተግባሩ ሲዘረዝር የሚታይበት ፓርት አለ፡፡ ከዚሁ በተቃራኒ ደግሞ ከሶስት ሳምንት በፊት (ምን አልባትም ፊልሙ እየተቀረፀ ባለበት ጊዜ ሊሆን ይችላል) ናትናኤል መኮንን የተባለው ተከሳሽ በማዕከላዊ እስር ቤት የደረሰበትን ለፍርድ ቤቱ ሲናገር ግን ስለቡና ግብዣ አላነሳም፡፡ ይልቁንም እንዲህ ነው ያለው፡-
“በተከታታይ ለሃያ ሶስት ቀናት የፌደራል ፖሊስ መርማሪዎች ኃላፊ እና በስራቸው የሚገኙ መርማሪዎች በአካሌ፣ በሞራሌ ላይ ጉዳት አድርሰውብኛል፤ ምግብ ተከልክዬ እርቃኔን እጄ ወደ ኋላ ታስሮ ለሃያ ሶስት ቀን ውሃ እላዬ ላይ እየተደፋብኝ እነርሱ የሚፈልጉትን እንድናገር ሲያስገድዱኝ ነበር፡፡ ለአራዳ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በደሌን አቅርቤ ዛሬ መልስ እንዲሰጡ ታዞ ነበር፡፡”
የተከበረው ፍርድ ቤትም የናትናኤልን ሰቆቃ ካዳመጠ በኋላ በመሀል ዳኛው በኩል መልስ ሰጠ፡-
“ዛሬ የክሱን ቻርጅ ዐቃቤ ህግ ለፍርድ ቤቱ የሚያቀርብበት ወቅት ስለሆነ ክርክሩ ሲሰማ በደልህን ታቀርባለ፤ አሁን የምናደምጥህ መናገር ስለጀመርክ ብቻ ነው፡፡”
እሺ! ክቡር ፍርድ ቤቱ፤ ለሀቅ መፍርዱ ቀርቶ ማዳመጡ ከሆነ ሀላፊነታቸው፤ መቼስ ምን ይደረጋል፡፡ እኛ ግን ስራችንን እንቀጥል፡፡ ናትናኤል “እነሱ የፈለጉትን እንድናገር አሰቃዩኝ” ያላትን ስንመነዝራት የአኬልዳማ መስካሪዎች በዚህ በኩል የተገኙ ሊሆኑ ይችላሉ የሚል ብርቱ ጥርጣሬ ያድርብናል፡፡ መቼም ማዕከላዊ አንድ ነው፡፡ ቦታውም ያው ከአራዳ ጊዮርጊስ ትንሽ ከፍ ብሎ የሚገኘው ነው፡፡ ሆኖም አንዱን ቡና እየጋበዘ፤ ሌላውን እርቃኑን አቁሞ ውሃ እየደፉበት የሚውል ከሆነ ከዚህ በላይ የሰበአዊ መብት አክባሪነት የትም የለ፡፡ ይሄ ተባራሪ ወሬ አይደለም፡፡ ራሳቸው የጉዳዩ ባለቤቶች ናቸው በአንደበታቸው የተናገሩት፡፡ ስለቡናውም ስለ እርቃኑም፡፡
“...ቶርቸር” ስልሚባል ነገር ብዙ ሰምተናል፡፡ ያውም ከደርግ ጊዜ ጀምሮ፤ ያውም በማዕከላዊ እስር ቤት፡፡ ኢትዮጵያ የሰው ዘር መጀመሪያ እንደመሆኗ ሁሉ የ..ቶርቸር..ም መጀመሪያ ትሆን እንዴ? ፕ/ር መስፍን ወልደማርያም ለደቂቀ እስጢፋኖስ መፃሀፍ “ቀዳሚ ቃል” ይሆን ዘንድ አዘጋጅተውት፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬስ ውድቅ በተደረገባቸው መጣጥፍ ላይ “ቶርቸርን” እንዲህ ይገልፁታል፡-
“ይህን መፃሀፍ ሳነብብ ምዕራባውያን (በእንግሊዝኛ) ፣ቶርቸር፣ (የግዕዝ ፀሐፊዎች ፣ኩነኔ፣ የሚሉትን ሰውን የማሰቃየትን ዘዴ) እኛ የፈጠርነው መሰለኝ፡፡ ቻይናውያን በዚህ ክፉ ዘዴ እንደሚታሙ አውቃለሁ፡፡ እኛም ሆንን ቻይናውያን የታሪካችንን ርዝመትና ያለንበትን የደኽነትን አዘቅት ለመገንዘብ ይህ የክፋት ዘዴአችን ማስረጃ ሆኖ ሊያገለግል የሚችል ይመስለኛል፡፡”

ልክ ኖት ፕሮፌሰር፡፡ እንደሚታወቀው የእኛ እና የቻይናውያን ፍቅር ከፍቅር እስከ መቃብርም በላይ ነው፡፡ በህግ ባለሙያዎች ዘንድ ብቻ ሳይሆን በሀገራችን ህግም “በቶርቸር” የተገኘ መረጃ፤ እንኳንም በፓርላማ ሊያስፎክር ቀርቶ፤ በአጥቢያ ዳኛም ቢሆን ተቀባይነት የለውም፡፡ ያውም በህግ አውጪው ፊት... “ከምር ማስረጃ አለን” ሊያስብል ቀርቶ...
ይሄ አይነቱ አሰራር መንግስትን ከ “መንግስትነት” ደረጃው አውርዶ የጎበዝ አለቃ ያስመስለዋል፡፡ ወይም ምዕራባውያኖቹ እንደሚሉት “Police state” ማለቴ ነው፡፡
የሆነ ሆኖ ቶርቸር በዋናነት በሁለት መንገድ ይገለፃል፡፡ አካላዊ እና ስነ ልቦናዊ ተብሎ፡፡ ለምሳሌ ናትናኤል ደረሰብኝ ያለው የቶርቸር አይነት አካላዊ በሚለው ሊመደብ ይችላል፡፡ ከቤተሰብ እንዳንገናኝ ተደረግን ያሉት ደግሞ የደረሰባቸው የቶርቸር አይነት ስነ ልቦናዊ ሊባል ይችላል፡፡
እዚህ ጋር አስቂኟ ነገር ሁሉም የአኬልዳማ መስካሪዎች በራሳቸው ላይ ከመሰከሩ በኋላ ከእስር ቤት መለቀቃቸው ነው፡፡ በእርግጥ የታሳሪዎቹ መለቀቅ መልካም ነገር ነው፡፡ እኔ ሲጀመርም የታሰሩበት መንግድ አልተዋጠልኝም፡፡ ተደጋጋሚ ጊዜ ሰዎቹ ይፈቱ ዘንድ ፅፌአለሁ፡፡ ሆኖም ታሳሪዎቹ የተለቀቁት በፊልሙ ላይ የታየውን ተናግረው፤ እንዲለቀቁ ተደራድረዋቸው ከሆነ ግን ከቶርቸር ጥቃቶች አንዱ እንደደረሰባቸው ነው የሚያስቆጥረው፡፡
ሌላው የአኬልዳማ ድራማ በማዕከላዊ እስር ቤት ሆነው ስለሽብር እቅዱ እና አፈፃፀሙ ታሳሪዎቹ ከነገሩን ውጪ መንግስት ከማሰሩ በፊት አለኝ ሲል ስለነበረው ማስረጃ አንዳች ማየት አለመቻላችን ነው፡፡ እውነት ለመናገር ኢቲቪ ፊልሙን እንደሚያሳይ ከአንድ ቀን በፊት ሲያስተዋውቅ፤ ስለእነ እስክንድር ነጋ ንፁህነት ስንመሰክር የነበረውን ምስክርነት፤ ገደል የሚከት ማስረጃ አቅርቦ ሊያሳፍረን ይሆን እንዴ ብዬ ራሴን ተጠራጥሬው ነበር፡፡ እናም የመጀመሪያው ክፍል ታየ ምንም አዲስ ነገር የለም፡፡ ሁለተኛው፤ ሶስተኛው እያልኩ ጠበኩ፡፡ ሆኖም የቀረበው ማስረጃ አንዳንዶቹ ኦነግ ከኢህአዴግ ጋር በጋራ መንግስት ሆኖ የፈፀማቸው፤ ሌሎቹም እስረኞቹ ራሳቸው ከታሰሩ በኋላ ማዕከላዊ ሆነው እንዲህ ልናደርግ ነበር እንዲህ አስበን ነበር ጂኒ ቁልቋል... የሚል ሆነና አረፈው፡፡ የእኛ ጥያቄ መንግስት ሰዎቹን ከማሰሩ በፊት ሰበሰብኩ (አገኘሁባቸው) ያለው ማስረጃ የት አለ? የሚል ነው፡፡ ...ወይም እንደ መሬት ወረራው መረጃው ተሰርቆ ተወስዶ ከሆነም ይንገሩን? ኢህአዴግ እኮ ሞኝ ነው፡፡ የማይሰረቀው ነገር የለም? የምርጫ ድምፅ ይሰረቃል፣ ኮሮጆ ይሰረቃል፣ማስረጃ ይሰረቃል፤ አሁን ደግሞ የሰበሰበው ማስረጃ...፡፡ ከዚህ ውጭ ኢህአዴግ እንኳንም ጋሽ ደቤን የራሱን ታላቁ ተጋዳላይ ታምራት ላይኔንም በፓርላማ “ተመክሬ ተመክሬ አልሰማ ብያለሁ” የሚል ዘፈን አዘፍኗል፡፡ አቶ መለስ “ስንይዛቸው ይዘፍናሉ” ያሉት ይሄን ችሎታቸውን ይሆን እንዴ? ብቻ ኢህአዴግ በማናዘዝ (በማዘፈን) የተካነ ይመስለኛል፡፡
እዚህች ጋር አንዲት ቀልድ ትዝ አለችኝ ፡- ከእለታት አንድ ቀን የፌደራል ፖሊስ አባላት በከተማው ያሉትን ዝሆኖች በሙሉ ይዛችሁ ኑ ተባሉ አሉ፡፡ ከተፎ ፖሊሶቹም ያለ የሌለ የዝሆን መንጋን እየነዱ አመጡ፡፡ አዛዡም ግድያቸውን ሊጐበኙ ከቢሮ ሲወጡ ከዝሆኖቹ መሀል በድብደባ ብዛት ሁለት ጥርሱ የወለቀ እና አናቱ የተፈነከተ ፍየል ያያሉ፡፡ በሁኔታው ተደንቀው እንዲህ ሲሉ ጠየቁ “ዝሆን ብቻ አይደል እንዴ አምጡ የተባላችሁት?”፤ ከተፎ ፖሊሶቹም መለሱ “ጌታዬ! ዝሆን ነኝ ብሎ አምኗል፡፡”
የሆነ ሆኖ መለስ በቂ መረጃ አለኝ ከአሉ በኋላ እና ፊልሙ እንደሚታየ ሲነገር ከፊልሙ የጠበኩት እስክንድር ነጋ እንደ ኦሰማ ቢላደን ክላሽ ከጎኑ አድርጐ፤ ፊልድ ጃኬት ለብሶ ከሀገራችን ተራራ ስር በአንዱ መሽጐ የሽብር ትእዛዝ ሲሰጥ ነበር፡፡ ሆኖም በፊልሙ ላይ የቀረበው ግን በጋዜጣ ማስታወቂያው ተነግሮ፤ በይፋ በተጠራ የውይይት መድርክ ላይ ጥናታዊ ጽሑፍ ሲያቀርብ ነው፡፡ ይሄ ነው እንግዴ አኬልዳማ- የደም መሬት፡፡
ለአንዱአለም አራጌ ደግሞ እንደ ማጠናከሪያ ሆኖ ቀርቦ ያየነው ውንጀላ ወንድሙ በኤርትራ ለሽብር ተግባር እየሰለጠነ መሆኑ ነው፡፡ ይሄ ፌር አይመስለኝም፡፡ በምንም ሊገናኝ አይችልምም፡፡ እንዲህ ከሆነማ ዛዬም በኢትዮጵያ በስልጣን ላይ ያሉት የኢሳያስ አፈወርቂ ዘመዶች ምን ሊባሉ ነው፡፡ ...ይገናኝ ከተባለ ደግሞ እኛም የግድ ደርግ “ስዬ አብርሃ የወንበዴ መሪ ነው” በሚል ምክንያት ብቻ የስዬን ታናሽ ወንድም አሰፋ አብርሃን ለ7 አመት በእስር ቤት ማሰቃየቱን እንደ ህጋዊ እርምጃ ልንወስደው ነው ማለት ነው፡፡ አያችሁ የአኬልዳማ ፕሮዲሰሮች፡- ጉድጉድ ሲቆፈር ብዙ መጥለቅ የለበትም፡፡ ማን እንደሚወድቅብት አይታወቅምና፡፡

በተቀረ ሽብርተኝነትን መከላከል አስፍላጊ ነገር ነው፡፡ የሽብር ድርጊትም አረመኔያዊ ተግባር መሆኖን ለማወቅ ምንም አይነት ትንተና አያሰፈልግም፡፡ ምክንያቱም ዋነኛ የጥቃቱ ኢላማ ሰላማዊ ዜጋ ነውና፡፡ ይሄንን ማንኛውም ዜጋ አይደግፈውም፡፡ ሻዕቢያም ፀረ ኢትዮጵያ አቋም እንዳለው ከማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ በዚህ በኩል ልዩነት ያለ አይመስለኝም፡፡ ልዩነቱ የሚመጣው ጋዜጠኞችን እና ሰላማዊ ፖለቲከኞችን እያሰሩ ከእነ ቢላደን እና ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ሲደመሩ ነው፡፡አሁንም የአኬልዳማ ፊልም ላይ አንድ ግልፅ ያልሆነ ነገር አለ፡፡ እርስ በእርሱ የሚጣረስ ማለቴ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ “ሽብርተኝነትን በተመለከተ ከአሜሪካ ጋር እንደጋገፋለን፤ መረጃ እንለዋወጣለን” ብለውን ነበር፡፡ ሆኖም በአኬልዳማ ፊልም ላይ ያየናቸው የአሸባሪዎቹ አለቆች ነዋሪነታቸው በአሜሪካ ነው፡፡ ይሄ ባለበት ሁኔታ እንዴት ሆነ ነው እንደጋገፋለን የተባለው? መረጃ መለዋወጥስ ማለት ምን ማለት ነው? መቼም እነ ኦሳማ ቢላደን አዲስ አበባ በሰላም የሚኖሩ ቢሆን ኖሮ፤ አሜሪካ እንኳንም ልትደግፈን፣ እንኳንም ብድር ልትሰጠን፣ እንኳንም... ገና ድሮ አፈር ድሜ አብልታን ነበር፡፡ እናም ይሄ ፊልማችሁን ተልካሻ ከአደረጉባችሁ ምክንያቶች አንዱ ስላልሆነ በሚቀጥለው ፊልም ላይ ብትጠነቀቁበት ይጠቅማችኋል በሚል ቅንነት ነው ያነሳሁት፡፡
የሆነ ሆኖ አቶ መለስ የፎከሩበት ማስርጃ ሄዶ ሄዶ መንግስትን መቃወም... ከሚል ሊዘል አልቻለም፡፡ ወይም ውሃ የሚቋጥር አይደለም፡፡ ይሄ ደግሞ ህገ-መንግስታዊ መብትን መግፈፍ ነው፡፡ ህገ-መንግስታዊ መብት ደግሞ ለአንዱ የሚነሳ፤ ለአንዱ የሚሰጥ አይደለም፤ ለሁሉም እኩል ነው፡፡ እነ አንዱአለም አራጌ በሰላማዊ መንገድ የመንግስት ለውጥ ያስፈልጋል ማለታቸው እና ያለፈው እሁድ በተደረገው ታላቁ ሩጫ ላይ የተሳተፉ 36ሺ ሯጮች፡- “ሳንፈልጋቸሁ ሃያ አመታቸሁ” እያሉ መቃወማቸው ልዩነት የለውም፡፡ የሯጮቹም መብት ነው፡፡ የእነ እስክንድርም መብት ነው፡፡ በተቀረ አኬልዳማ ላይም ሆነ አዲስ አበባን እንደ ባግዳድ ወይም ከዚህ ቀደም ተሰርተው ያየናቸው ፊልሞችን ስም እና ተዋናይ እየለዋወጡ ማሳየቱ ከደረሲው እና ከአዘጋጁ በቀር ማንንም አያሳምንም፡፡
እናም የሚሻለው፤ ለሀገራችን የሚበጀው በእሳት የጋየ ቤት እና መኪና፤ ወይም በፈንጅ የተበጣጠሰን የሰው አካል እያሳዩ ማስፈራራቱ ሳይሆን የፖለቲካ መፍትሄ መስጠቱ ነው፡፡ ብሔራዊ እርቅ እንጂ የደህንነት አባላትን ቁጥር ማብዛት መፍትሄ አይሆንም፡፡ የዶክመንተሪ ፊልምም ብዛት እንዲሁ መፍትሄ አይሆንም፡፡ ለዚህም ጥሩ አስረጅ እንዲሆን ከፕ/ር መስፍን ቀዳሚ ቃል ልጥቀስ፡፡

“ቁም ነገሩ ደቂቀ እስጢፋኖስ መሸነፋቸው አይደለም፡፡ ቁም ነገሩ እየተሰቃዩ መታገላቸው ላይ ነው፡፡ ለህገ አራዊት አንበረከክም ማለታቸው ነው፡፡ በጣም የሚያስደንቀው ነገር አንድም የደቂቀ እስጢፋኖስ አባል ሲሞት ሞተ አለመባሉ ነው፡፡ ሰማዕትነቱን፣ ወይም ፣ገድሉን፣ ፈጸመ ይላሉ፡፡ ይህ አስተሳሰብ ጥልቅ መልእክት ያለው ሆኖ ይሰማኛል፡፡ የሰው ልጅ ህይወት እንደ እንሰሳ ህይወት አይደለም፤ አላማ አለው፡፡ መልእክት አለው፡፡ ቁም ነገሩ ዓላማውን ወይም መልእክቱን መፈፀሙ ነው እንጂ መኖር ብቻ አይደለም፡፡ ሐሳብንና እምነትን እንደያዙ በነፃነት ማለፍ ሐሳብንና እምነትን አስረግጦ ከመኖር የተሻለ ነው ብለው የሚያምኑ ይመስለኛል፡፡ ለዛሬው ትውልድ ይህ ኃይለኛ መልዕክት ነው፡፡”

አ ዎ!ፕሮፌሰር ይሄ ለእኛ ትውልድ ሀይለኛ መልእክት ነው፡፡ “ታጋይ ይሞታል እንጂ፤ ትግል አይሞትም”ን የት ነበር የሰማሁት?

Comments

teme egezer yibarekih

enat weledku tibel teme, anjet aris neh mechem. Kudos my brother, may my country always never be short of determines sons like yourself.

thank you ተመስገን ደሳለኝ for this wonderful article .

thank you

This is the best educational rebut to EPRDF's recent harmful drama. Great Reply!

Highly circulated commentary!
Educational with good humor!

what the butchers tell you ones after they test your flesh, truth is no value if truth don't serve the interest of the current demagogue! if you are out of your mind you are not comprehensible even to a sane child. but you, you are my hope guys and we will see and time will tell.

may god bless u! keep in uncovering the facts of the buchers!!

Ato temesgen, if you really have the whole video with you why don't you post it on the utube or some other place on the internet so that doubters like me believe what you are saying.

My brother, you can see the video by Tamagn Beyene.I have believed Teme becuase I saw the video from Tamagn Beyene at Ethiomedia.Ofcourse, if you are in ethiopia I guess you dont have access to ethiomedia.

10Q

thank u Temesgen, her is very Realyyyyyyyyyyyyyyyyyyyyyyyy

abo edema ysetek anbesa nek ante!!!

i will repeat it again.'reading brings chanege' unless it is a reading in forest! like epdrf's

Wende, ye wende lij neh Teme!!
Thank you, Thank you Thank you very much for this well articulated article!! Mechem yewusten new yetenagerikew!

Excellent analysis! Take care of your self.

bravo teme !!!!

I really appreciate your idea and way of expression something to the others it is so easy and clear

10q

ልዩነቱ የሚመጣው ጋዜጠኞችን እና ሰላማዊ ፖለቲከኞችን እያሰሩ ከእነ ቢላደን እና ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ሲደመሩ ነው
እናም የሚሻለው፤ ለሀገራችን የሚበጀው በእሳት የጋየ ቤት እና መኪና፤ ወይም በፈንጅ የተበጣጠሰን የሰው አካል እያሳዩ ማስፈራራቱ ሳይሆን የፖለቲካ መፍትሄ መስጠቱ ነው፡፡ ብሔራዊ እርቅ እንጂ የደህንነት አባላትን ቁጥር ማብዛት መፍትሄ አይሆንም፡፡ የዶክመንተሪ ፊልምም ብዛት እንዲሁ መፍትሄ አይሆንም
we have talented man like you but government do not think for country

thank u

I know this is a rubbish drama that shows not only the unprofessional film producers of ETV but also depict their attitude to the people. One genuine journalist is still enough to refute the plethora of lies the government is established! God bless you.

Add new comment

Filtered HTML

  • Web page addresses and e-mail addresses turn into links automatically.
  • Allowed HTML tags: <a> <em> <strong> <cite> <blockquote> <code> <ul> <ol> <li> <dl> <dt> <dd>
  • Lines and paragraphs break automatically.

Plain text

  • No HTML tags allowed.
  • Web page addresses and e-mail addresses turn into links automatically.
  • Lines and paragraphs break automatically.