ከጓድ መንግስቱ ኃይለማርያም ‹‹ትግላችን›› ጋር…
ማን ይፈራል ሞት
ማን ይፈራል
ለእናት ሀገር ሲባል..
የጊዜው ወታደራዊ ደርግ አስተዳደር፣ የአብዮታዊ ጦር ሰራዊት ጠቅላይ አዛዥ፣ የኢትዮጵያ ሰራተኞች ፓርቲ ዋና ፀሀፊ፣ የኢህዴሪ ሊቀመንበር፣ የኢትዮጵያ ፕሬዘዳንት… ጓድ መንግስቱ ኃ/ማርያም ሰሞኑን በስደት ከሚኖሩበት ዙምባቤ ‹‹ትግላችን›› የተሰኘ መጽሐፍ አሳትመው በ39 የአሜሪካ ዶላር እየቸበቸቡ ነው፡፡ በእርግጥ ሀገር ከመሸጥ መጽሐፍ መሸጥ የተሻለ ነበር፡፡ ምን ዋ¬¬ጋ አለው እንጂ፤ ምክንያቱም ጓድ መንግስቱ መጽሐፋቸውን ቸብችበው ሳይጨርሱ ወይም ገበያው በደራበት ሰአት ‹‹የዚህን አምባገነን ሰው መጽሐፍ በነፃ ኮምኩሙ›› ያሉ የቀድሞ ተቀናቃኞቻቸው፣ ለእኛ ለ‹‹አቅመ መግዛት›› ላልደረስነው በድህረ ገፆች ለቀቁልን፡፡ (መጽሐፉን ያመጡልኝን ሰዎች ውለታ ማሳነስ ተደርጎ እንዳይወሰድብኝ) መቼም የመንጌን መጽሐፍ እንደ ጉልት ቲማቲም፤ ያውም በነፃ እንዲህ በየቦታው እንድናገኘው ያደረገው ኢህአፓ ከተሰኘው ፓርቲ ጥቂት የሙት ትራፊዎች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በመፃሀፉ ውስጥም ከግንባር ቀደም ተወጋዦች አንዱ ነው፡፡ ‹‹ኢህአፓ››፡፡ ለነገሩ ምን ያደርጉ ብለህ ነው ‹‹ከስልጣን ማውረድ›› ባይሳካለትም፣ እንዲህ ከገበያ ያውርዳቸው እንጂ፡፡
የሆነ ሆኖ የመንግስቱ ኃ/ማርያምን መጽሐፍ አንብቤ ጨረስኩት፡፡ በእርግጥ ይሄ ቅፅ አንድ ሲሆን፣ በቀጣይ ቅፅ ሁለት እና ሶስት ይታተማሉና ጠብቁኝ ስላሉን ጨረስኩ ማለት አይቻልም፡፡ ገና እናነባለን፡፡ እሳቸውም ገና ይፅፋሉ፡፡ እንደ መፀሀፈቸው ጭብጥ ደግሞ አብዮቱም ገና አልተቀለበሰም፡፡ የስልጣን ጥማቸውም ገና አልተቆረጠም፡፡ እናም ጥማቸው ይርካ ዘንድ እንዲህ አሉ፡-
‹‹ኢትዮጵያ ዛሬ ጀግና ብቻ ሳይሆን ሰው አልባ ምድረ በዳ እየሆነች ነው፡፡ ዛሬ ሰው የምንላቸው ኢትዮጵያዊያን አንድም ተገለዋል፣ አንድም ተሰደዋል፣ አብዛኛውም በወያኔ እስር ቤቶች ታጉረዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ የሚዋጋና የሚታገል ቀርቶ የሚናገርም የለም፡፡ ከዚህ እጅግ ከከፋና ከከረፋ ጨቋኝና ጎታች ጉልታዊ ስርዓት የኢትዮጵያ ህዝብ ነፃ ያወጡት አብዮታዊያን መሪዎችና የአገሪቱ ወጣቶች በወያኔ እስር ቤቶች በረት የተዘጋባቸው መሆናቸውን እያስተዋለ ሁሉም ዝም ብሏል፡፡›› (73-74)
‹‹ትግላችን›› መጽሐፍ በአንድ በኩል የመንግስቱ ኃይለማርያምን ብዙ ማንበብ በመጠቆም ከስልጣን ከተባረሩ በኋላ ጊዜያቸውን በአግባቡ እንደተጠቀሙበት ያሳያል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እንደተለመደው ራሳቸውን የተከላከሉበት እና የሁልጊዜም ‹‹እኔ ንፁህ ነኝ›› መዝሙራቸውን የዘመሩበት ነው፡፡ ስለዚህም መጀመሪያ ከመጽሐፉ የማይዋጡልንን በወፍ በረር ቃኝተን፣ ለጥቀን ደግሞ የሚዋጡልንን ወይም ፍሬያላቸውን እናያለን፡፡
መንግስቱ ኃ/ማርያም በመጽሐፋቸው ካመሰገኗቸው ሰዎች መካከል ልክ እንደ አቶ በረከት ስምኦን ባለቤታቸውም ይገኛሉ፡፡ በእርግጥ መንጌ እንደ በረከት ‹‹የእኔ ውድ፣ አለኝታ፣ የአንች…›› ምናምን ሲሉ በፍቅር አንጀት አልበሉም የ‹‹አብዮቱ ቆራጥ›› መሪ ናቸውና፡፡ እናም በቀጥታ እንዲህ ነው ያሉት ‹‹…ለመጽሐፉ ዝግጅት የሚያስፈልጉኝን ቁሳቁሶች በማቅረብ ብቻ ሳይሆን የእኔንም ጤንነት በመንከባከብ፣ በመላላክ እንደነሱ ፍላጎት ቢሆን ኖሮ ከወሰደብኝ ጊዜ ባጠረ ጽፌ እንድጨርስ ከእኔ ባለመለየትና በመትጋት የረዱኝ ውድ ባለቤቴ ጓድ ውብአንቺ ቢሻው…››(ገፅ 5)፡፡ መንጌ ጋ አንጀቴ፣ ሆዴ፣ ጉበቴ… አይሰራም፡፡ ወላ ሚስት፣ ወላ ፍቅረኛ፣ ወላ... ‹‹ጓድ›› ነች፡፡ ጓድ መንግስቱ ኃ/ማርያም፤ ጓድ ውብአንቺ ቢሻው…
ይሄም ሆኖ መጽሐፉን ከማየታችን በፊት ጥያቄ ማንሳት ያለብን ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ዘመኑን ስንመረምርው የወጣው የሚወርድበት ሲሆን፤ ማን ያውቃል የወረደውም... መቼም ከመንጌ ጋር በአንድ ነገር እንስማማለን፡፡ የወጣው በሚወርድበት፡፡ ‹‹የወረደው...›› በሚለው ግን እዛው በፀበላቸው፡፡ እናም ጥያቄ እናንሳ፡፡ ለምሳሌ መንግስቱ መፅሐፋቸው በዚህ ወቅት ለምን እንዲታተም ፈለጉ? (እንዲያውም በመጽሐፉ የተነሳ ከእሳቸው ጋር ቅርበት ያለው ሰው እንደነገረኝ መጽሐፉ እንዲታተም የፈለጉት በዘንድሮ መስከረም ሁለት ቀን ነበር፡፡ በሳቸው ደግሞ ሰላሳ ምናምነኛው የአብዮት በአል፡፡ ይሄ ስላልተሳካላቸውም ከመጠን በላይ ተበሳጭተዋል አሉ) ይሄ እንግዲህ የመጽሐፉ አንዱ አለማ ‹‹ራስን ለመከላከል ነው›› ከሚለው ባሻገር መሆኑ ነው፡፡
በእርግጥ በመጽሐፉ ‹‹መቅድም›› ላይ እንደተገለፀው መጽሐፉ ሊፃፍ የነበረው የአስረኛው አብዮት በአል ዋዜማ አካባቢ ነበር፡፡ እንዲያውም ታሪኩ እንዲፃፍ ካሳሰቡት ምሁራን መካከል ፍቃደኛ የነበሩትን አሰባስቦ ‹‹የታሪክ አርቃቂ ምሁራን ኮሚቴ›› ሁሉ ተመርጠው ነበር፡፡ (የኮሚቴው አባላቶች ጓድ ሻለቃ ናደው ዘካሪያስ፣ ጓድ ፍሰሃ ዘውዴ፣ ዶ/ር መርዕድ ወ/አረጋይ፣ ዶ/ር ባህሩ ዘውዴ፣ ዶ/ር ብርሃኑ አበበ እና አቶ ሽፈራው በቀለ እንደነበሩ ጠቅሰዋል) የመጀመሪያው ረቂቅ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተዘጋጅቶ ሲቀርብላቸም መንጌ ‹‹የፖለቲካዊ ስርዓት አመራር አካላት በስልጣን ላይ እያለን የታሪኩ ፀሐፊዎች ያለአንዳች ስጋት ፍርጥርጥ አድርገው ለመፃፍ ድፍረቱ ይኖራቸዋል ወይ?›› ምናልባት ፀሐፊዎቹ ለዚህ ብቃት አላቸው ብለን ራሳችንን ብናሳምንም እንኳን አንባቢው ህዝብ ፀሐፊዎቹ በተሟላ ህሊና የፃፉት ታሪክ ነው ብሎ ይቀበለዋል ወይ? በሚሉ ጥያቄዎች ላይ እንደ ተወያዩበት ገልፀዋል፡፡ ከውይይቱ በኋላም ታሪክ መፃፉ እንዲቆም ተደረገ ይሉናል፡፡ በዚህም ምትክም ለአብዮቱ ሲታገሉ ለተሰዉ እና በህይወት ላሉ አብዮተኞች መታሰቢያ ይሆን ዘንድ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ግቢ ውስጥ ያለው ‹‹ትግላችን›› ሀውልት ቆመ ካሉን በኋላ ‹‹ታሪክ የመፃፉን ተግባር ለራሱ ለታሪክና ለህዝቡ እንተወው በሚለው አቋማችን ጸንተን ለአገራችን አንድነት፣ ለአብዮቱ ደህንነትና ለህዝቡ የተፋጠነ ማህበራዊ እድገት ስንታገል በሰሜን አሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም፣ በከሃዲዎቹና አብዮት ቀልባሾቹ ሩሲያዊያን በተጎነጎነ ታላቅ ሴራ የተገፉትና የተመሩት የውስጥ አድህሮት ኃይላት፣ በመምሰልና በማስመሰል አብረውን የተሰለፉ ከሀዲዎች ከያሉበት ተጠራርተውና ተረባርበው የኢትዮጵያ ህዝብ አምጦ የወለደውን አብዮት ቀለበሱት፡፡ የወጠነውንና የገነባውን ሁሉ አፈረሱት፡፡ ለአገሩ ታማኝና አለኝታ፣ ለህዝቡ መከታና የሰላሙ ዋስትና የሆነውን ህዝባዊና አብዮታዊ የመከላከያ ሰራዊት በመበተን ከአንድ አናሳ ብሄረሰብ መካከል በወጡ ጎጠኞችና የባዕድ ምንደኞች፣ ሀገርን በመገንጠል የእናት ጡት ነካሽና አባት አስለቃሽ በሆኑ ህዝብ አሸባሪ ቀማኛ ፋኖዎች ተኩት፡፡ ኤርትራን ገንጥለው በሕብረት አዲስ አበባ የገቡት ምንደኞች ኢትዮጵያ ቅኝ ሆና፣ በቋንቋና በጎጥ ተሸንሽና ዳግም የባሕር በር አልባ ሆነች፡፡ የአገራችን ታሪካዊ ጠላቶችን ወክለው አገራቸውን የወጉ ምንደኞች ራሳቸውን ታጋይና የነፃነት አርበኛ፣ የፍትህ ዳኛ፣ እነሱ ከሳሽም ፈራጅም ሲሆኑ የኢትዮጵያ ህዝብ ዘር አጥፊና የጦር ወንጀለኛ ተብሎ መፈረጁን በመስማቴ ለታሪክና ለህዝቡ የተውነውን የኢትዮጵያ ህዝብ አብዮታዊ የትግል ታሪክ እኔ እራሴ ለመፃፍ ተገደድኩ፡፡›› ሲሉ የፃፉበትን ምክንያት ዘርዝረዋል፡፡ በእርግጥ መንጌ ዛሬም ከስልጣን መውረዳቸው የተዋጠላቸው አይመስለኝም፡፡ በእርግጥ እሳቸውን የ‹‹ተንሳኤው ተስፋ›› አድርጎ የሚጠብቅ የለም፡፡ በእርግጥ መንጌን የተኳቸውን መለስንም ቢሆን የሚፈራ እንጂ ተስፋ ያደረጋቸው ያለ አይመስለኝም፡፡ በእርግጥ መንጌ ለጀግናው የኢህአዴግ አመራር አንድ ነገር አስተምረዋል፡፡ ‹‹የፖለቲካ ስልጣን የያዙ ታሪክ ታሪክ ይሰራሉ እንጂ ታሪክ አይፅፉም›› ሲሉ፡፡ እውነት ግን እንዲህ በሽሚያ ታሪካቸውን እየፃፉ እና እያፃፉ ያሉ መሪዎቻችን ይህንን ሲያነቡ ምን ይሉ ይሆን? ...ልክ እንግሊዞች ሲገቡ ሀገራቸው፤ ምን አሉ? እንደተባለው... ሰው የለ በእጃቸን ብለው ይሆን? ይሄ ጥያቄ ነው፡፡
መልስ የሚሰጥ ካለ ደህና፤ ካሌለም ወደ መፀሀፉ እንመለስ፡፡ እኒህ ‹‹የግዴታ ታሪክ ፀሀፊ›› ለ17 ዓመት ሀገሪቱን የጦር አውድማ ከማድረጋቸው ባሻገር፣ ከአንድ ትውልድ ወጣት ለወሬ ነጋሪ ጥቂቱ ሲቀር ሙሉውን ለማለቁ ምክንያት ናቸው፡፡ እናም የእልቂቱ መሪ የነበሩት ጓድ መንግስቱ ስለዚህ እልቂት ትንሽ ሳይሉ ነው 505 ገፅ ያለው መጽሐፋቸው ያለቀው፡፡ ወይም እስከ 1970ዓ.ም ድረስ ይተርካል የተባለው መፀሀፍ ያለቀው፡፡ መቼም ‹‹ቀይ ሽብር›› እና ‹‹ነጭ ሽብር›› እየተባለ ዛሬም በፖለቲካ ፋይዳው ለጓድ መለስ ዜናዊ እያገለገለ ያለው ‹‹ሽብር›› በዋናነት የተካሄደው በ1969 እና በ1970 መጀመሪያ ላይ ነው፡፡ ከ1970ዓ.ም በኋላ ‹‹ነጭ ሽብር››፣ በ‹‹ቀይ ሽብር›› በመመታቱ የጎዳና ላይ ግድያውም ሆነ በጠፍ ጨረቃ ከእየእስር ቤቱ እየተጎተቱ አብዮታዊ እርምጃ መወሰዱ ቆሟል፡፡ እናም መንግስቱ በ‹‹ትግላችን›› ስለዚህ ሁኔታ በሚገባ አልገለፁም፡፡ ወይም አንዳች የጥፋተኝነት ፀፀት እንዳለባቸው አላሳዩም፡፡ በግልባጩ ‹‹የኢትዮጵያን ህዝብ ነፃ ያወጡት አብዮታዊያን መሪዎችና የአገሪቱ ወጣቶች በወያኔ እስር ቤቶች በረት የተዘጋባቸው መሆናቸውን እያስተዋለ ሁሉም ዝም ብሏል፡፡›› ሲሉ ከአብዮቱ የተረፈውን ህዝብ ወቅሰዋል፡፡ ወቀሳው ግን ፈር የሳተ ነው፡፡ ይሄ ትውልድ ለአብዮታዊያን መሪዎቹ ባለዕዳ አይደለም፡፡ የሞራልም፣ የውለታም፡፡ ለምን? ከተባለ ከእነሱ አብዮት ያተረፈው በጥይት ተደብድቦ መሞት እና ከሀገር መሰደድ ነው፡፡ በተቀረ አብዮታቸው ልክ እንደኢህአዴግ አብዮት ራሳቸውን ነው የጠቀመው፡፡ እናም ስለታሳሪዎች ከተነሳ ትውልዱ ባለእዳነቱ ለወጣት ታሳሪዎች ብቻ ነው የሚሆነው፡፡
ጓድ መንግስቱ ‹‹ጲላጦስ ነኝ›› ያሉት በቀይ ሽብር ከፈሰሰው ደም ብቻ አይደለም፡፡ ከራሳቸው ጓዶችም ደም እንጂ፡፡ እንደዋዛ ‹‹ለምሳ ሲያስቡን፣ ለቁርስ አደረግናቸው›› እያሉ በጥይት ያስደበደቧቸውን የ‹‹አብዮቱ›› መሪዎችንም ግድያ ምክንያት ፈልገው ለጥፈውበታል፡፡ ለምሳሌ ‹‹አብዮቱ››ን በመምራት ከራሳቸው ከመንግስቱ ሳይቀር ቀዳሚ የነበሩት እና ‹‹አብዮት ልጆቿን ትበላለች›› በሚል ቧልት ስለተበሉት አጥናፉ አባተ ሞት፤ አስፈላጊነት ብዙ ምክንያት ደርድረዋል፡፡
ጓድ መንግስቱ የምስራቁን ጦር ወክለው አጥናፉ በሚመሩት 4ኛ ክፍለ ጦር ጊቢ የተሰባሰቡትን አማፂ ወታደሮች በተቀላቀሉ የመጀመሪያዋ እለት በአዳራሹ በተናገሩት ንግግር አጥናፉ እንደተቀየሟቸው ጽፈዋል… ‹‹እኔ በሰጠሁት አስተያየትና ባቀረብኩት ሂስ ደስተኛ አልነበረም፡፡ ከዓላማ አኳያም ሆነ ከአሰራር ጉድለት የተናገርኩት ሁሉ የሱን (የአጥናፉን) አመራር በመንቀፍ ስልጣን ፍለጋ አድርጎ ነው የተመለከተው፡፡›› (ገጽ 151) ሲሉ ፡፡
በአጠቃላይ አጥናፉ አባተ የኮንጎ ዘመቻ በመሆናቸው የኮንጎ ዘማቾችን የአባል ይከፈለን ጥያቄ ከጀርባ ሆኖ የሚያቀሳስሩ ብቻ ሳይሆን እስከዛሬ ያልሰማነውን ‹‹የክርስቲያን ዴሞክራቲክ ፓርቲ›› የሚባል ፓርቲም በድብቅ መስርተው መንግስቱ ‹‹ለስራ ጉዳይ ወደ ውጭ ሀገር ሄድኩ›› ባለበት ሰዓት መፈንቅለ መንግስት እንደተሞከረባቸው ገልፀዋል፡፡ እንዲሁም የኢህአፓ አባል ነበሩ ሲሉ ከወነጀሏቸው በኋላ በአንድ ሰብሳባ ላይ አጥናፉ አባተ ‹‹በአገራችን ባህል፣ ሃይማትና ታሪክ ጋር ፈፅሞ የማይገጥምና የማይስማማ የሶሻሊስት ስርዓት እንከተላለን ብለን አገሪቱን የጦርነት አውድማ አደረግናት፡፡›› (254) ማለታቸውን ተከትሎ መላው የደርግ አባል አወገዛቸው፡፡ እንዲያውም አንድ አባል ተነስቶ ‹‹ይህ ደርግ እኝህን ሰው ምንድን ነው የሚያደርገው? የኢትዮጵያ ትቅደም ሰይፍ መመዘዝ ያለበት ዛሬ ነው፡፡ የኮሎኔል አጥናፉ ከእኛ ጋር ጉዞ እዚህ ላይ ያበቃል ብሎ መፈክር ሲያሰማ ሁሉም የደርግ አባላት ተነስተው መፈክሩን አስተጋቡ›› (255) ይሉንና ስለግድያው ደግሞ በገፅ 258 ላይ ሲነግሩን ‹‹በየዋህነቱና በክፉ መካሪዎቹ ወደ ኋላ ቃል ኪዳኑን ሳተ፡፡ አብዮት ልጆቿን ትበላለች እንደሚባለው ጓድ አጥናፉንም የፈጠረው ደርግ በላው›› በሚል ስላቅ ነው፡፡
መቼም ይሄ ቧልት ነው፡፡ እውነታው አጥናፉን ደርግ በላው ከሚሉን እኔው እራሴ በላሁት ቢሉ ትልቅ ንሳሐ በሆነላቸው ነበር፡፡ ነበር… ነው ያልኩት፤ በእርግጥ ‹‹ነበር›› በሚል ርዕስ ጓድ ገስጥ ተጫኔ (ዘነበ ፈለቀ) በተባሉና የጓድ ለገሰ አስፋው ልዩ ረዳት በነበሩ ሰው የተፃፈው መጽሐፍ በአጥናፉ ላይ የተወሰነው የሞት ቅጣት በደርግ አባላት እንዳልተወሰነ ያትታል፡፡ በወቅቱም የቋሚ ኮሚቴ አባላት ካልሆኑ በቀር ብዙሃኑ ደርግ በየክፍለ ሀገሩ መበተኑን ይገልፃል፡፡ በገፅ 208 ላይም እንዲህ ይላል ‹‹እነ ብርጋዴር ጄነራል ተፈሪ ባንቲ ሲገደሉ አንድም የደርግ አባል እጅ አውጥቶ አልወሰነም ነበር፡፡ ነገር ግን በተወሰደው እርምጃ አብዛኞቹ የደርግ አባላት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የተስማሚነት አዝማሚያ አሳይተዋል፡፡ ‹ርምጃው ልክ ነው› በማለት ሲናገሩም ተደምጠዋል፡፡ የሌ/ኮሎኔል አጥናፉ ጉዳይ ሲነሳ ግን ለየራሳቸው በመፍራት በግልፅ አውጥተው አይናገሩት እንጂ ውስጥ ውስጡን ያጉረመርሙ ነበሩ፡፡ ሐዘናቸውም አመዝኖ ይታይ ነበር፡፡›› ጓድ መንግስቱ ደግሞ በጓድ አጥናፉ ላይ መላው ደርግ ሞት ፈረደባቸው፤ መፈክር ፈከረባቸው፤ ከዛም በቅፅል ስሙ ‹‹አብዮት›› የሚባል ሰይፍ መዘዘባቸው ይሉናል፡፡
እነሆ አሁንም የመንጌ ‹‹ጲላጦስነት›› ቀጥሏአል፡፡ በደርጉ የሀገሪቱ ርዕሰ ብሔር እና የራሱ የደርጉ ሊቀመንበር ተብለው የተመረጡት ጄነራል አማንእንዶም የሻዕቢያ አባል እንደሆኑ፣ ከሲጋራ እና መጠጥ በተጨማሪም ሀሺሽ ተጠቃሚ መሆናቸውን ይገልፁና ከፍተኛ የስልጣን ጉጉት ያለባቸው አድሀሪ ነበሩ ይሏቸዋል፡፡ እናም መንግስቱ ኃይለማርያም እኚህን አንጋፋ ጄነራል በነመኖሪያ ቤታቸው እንዳሉ በታንክ አስደፍጥጠው ገደለዋቸው ሲያበቁ፤ በ‹‹ትግላችን›› መጽሐፍ ላይ ግን ‹‹ጄነራል አማን አንዶም ካረፋ በኋላ…›› እያሉ ፅፈውልሃል፡፡ ልክ በወባ በሽታ ህይወቱ እንዳለፈ ሰው አስመስለው ማለቴ ነው፡፡
መንግስቱ ኃ/ማርያም ማለት እኚህ ናቸው፡፡ ከ20 አመት የስደት ኑሮ በኋላ በፃፉት መጽሐፍ እንኳ ቅንጣት ታህል አንዳች የመፀፀትም ሆነ ሀላፊነትን የመውሰድን አዝማሚያ የማያሳዩ፡፡ በአጠቃላይም በሀገሪቱ የተደረጉ በጎ ነገሮች በሙሉ የእሳቸው ጭንቅላት ያመነጨው ሲሆን፤ ሁሉም መጥፎ ነገሮች ደግሞ የጠቅላላው ደርግ ውሳኔ እንደሆነ አድርገው ነው የፃፉልን፡፡ መቼም ሌላው ሌላው ቢቀር ለያ ትውልድ እልቂት ከጓድ መንግስቱ በፊት ማንም ተጠያቂ ሊሆን አይችልም፡፡ መንግስቱ ሀይለማሪያም ግን ማንም ሊጠይቀኝ አይችልም እያሉ ነው፡፡ ይልቁንም እነዛ ሺ ምንተ ሺ፣ በሀገር ፍቅር የነደዱ ወጣቶችን የፈጀው እኔ ሳልሆን የኢትዮጵያ ህዝበ ነው፡-
ማን ይፈራል ሞት
ማን ይፈራል
ለእናት ሀገር ሲባል...
እያሉ ያሾፉብናል፡፡ እውነት ለመናገር አባገነኖች እንደ ባልና ሚስት ከአንድ ወንዝ ነው የሚቀዱት፡፡ መንግሰቱ ሀይለማሪያም የተባሉ አባገነን በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ ወጣቶችን ፈጅተው ሲያበቁ ‹‹...ለእናት ሀገር ሲባል›› ይሉናል፡፡ መለስ ዜናዊ የተባሉ አባገነንም እንዲሁ ናቸው፡፡ እነእስክድር ነጋን ህዝቡ ተረባርቦ አሳሰረቻው ሲሉ የሚቀልዱ ማለቴ ነው፡፡
አሁን ደግሞ ወደ መጽሐፉ ጠንካራ ጎን እንለፍ፡፡ በእርግጥም የአምባገነኑ መሪ ‹‹ትግላችን›› እንድናነበው የሚያስገድዱን ብዙ ነገሮች አሉት፡፡ የኢትዮጵያን ታሪክ ከአክሱም ዘመን ጀምሮ የሚተርክ ነው፡፡ ያውም በአብዮቱ ቋንቋ ‹‹የግራኝ መሀመድ ጦር አከርካሪውን ተመቶ፣ የደጃዝማቹ እብሪት ተነፍሶ… የፋሽስቱን ጦር አራውጠው በማባረር… ከበውና ሰንጥቀው፣ የተቅበጠበጠውን የንጉስ ጦር…›› በመሳሰሉት ቃላቶች፡፡ በእርግጥም እነዚህ እነዚህ ዘና ያደርጋሉ፡፡ ወይም መጽሐፉን እያነበብነው በአይነ ህሊናችን መንጌ ‹‹አብዮታዊት እናት ሀገር ወይም ሞት›› ሲሉ እየፎከሩ ይመጡበናል፡፡ የሀገራችን አምላክ በእውን አያድርገው እንጂ፡፡
በእርግጥ ጓድ መንግስቱ በገፅ 315 ላይ ‹‹በአንባቢያን ዘንድ ይታወስ እንደሆነ በአብዮት አደባባይ የአገሪቱን ወህኒ ቤቶች ወደ ሆስፒታልና ወደ ትምህርት ቤት እንለውጣቸዋለን ያልነው በዚህ ጊዜ ነበር›› ቢሉም በተግባር ያየነው ግን የመኳንቱን ቤቶች ሳይቀር፣ ወደ እስር ቤት ሲቀይሩ ነው፡፡ ለነገሩ ጓድ መለስም ቢሆኑ ሀገሪቱን ወደ ሆቴል እና ጭፈራ ቤት እየቀየሯት ነው መሰለኝ፡፡ ከአላሙዲ ጀምሮ የመጣው ባለሀብት ሁሉ የሚከፍተው ወይ ሆቴል ቤት ነው፡፡ ወይ ጭፈራ ቤት ነው፡፡ አሊያም መሸታ ቤት ነው፡፡ በዚህ አያያዝም ምናአልባትም ከጥቂት አመት በኋላ ከኢህአዴግ ቢሮ በስተቀር መላው ሀገሪቱ ሆቴል ከመሆን የሚያግደው ላይኖር ይችላል፡፡ ከኢህአዴግ ካድሬም በቀር ሰፊው ህዝብም አስትናጋጅ ሊሆን ይችላል፡፡ አይበለው እንጂ፤ ካለው መቼስ...
የሆነ ሆኖ ‹‹ትግላችን›› መጽሐፍ በርካታ ቁምነገሮች እና አዳዲስ መረጃዎችንም ይዞአል፡፡ በተለይ ከሀገር አንድነት ጋር የተያያዙ፣ ከታሪክ ትንተናው በተጨማሪ ማለት ነው፡፡ ...ጅቡቲ እንዴት የኢትዮጵያ እንደ ነበረችም በስፋት እና በአሳማኝ ሁኔታ ፅፈዋልናል፡፡ በነገራችን ላይ መንጌ ‹‹ኤርትራ የኢትዮጵያ ነች አይደለችም›› የሚል ጥያቄ እንዲነሳባቸው አይፈልጉም፡፡ የአሠብ ወደብም ጥያቄን ማንሳት አይፈልጉም፡፡ ምክንያቱም በእሳቸው እሳቤ ኤርትራ እና አሰብ ብቻ ሳይሆኑ ጅቡቲም ሙሉ በሙሉ የኢትዮጵያ ህጋዊ አካል ነችና፡፡ ይኼ ይኼ ነገራቸው እኮ ነው የሚመቸው፡፡
መንግስቱ ኃ/ማሪያም የዚያድባሬን ወረራ የጦር ስልት ራሳቸው ነድፈው እንዴት መመከት እንደቻሉ እያንዳንዱን ነገር ዘርዝረዋል፡፡ በጦርነቱ ዋዜማም ከሱማሊያ ጋር በየመን- ኤደን የመጨረሻ ድርድር ተደርጎ ስለአለመሳካቱ በገለፁበት ምእራፍ እውነተኛውን ባህሪያቸውን እናገኘዋለን፡፡ ቁጡነታቸውን፡፡ እናም በመፃሀፉ እንደተገለፀው የዚህ የመጨረሻ ድርድር አደራደሪ ፊደል ካስትሮ እና የወቅቱ የየመን መሪ አብዱል ፈታህ ድርድሩ ሊጀመር ጥቂት ደቂቃ ሲቀረው መንግስቱ ኃ/ማርያምን እንዲህ ብለው መከሩ ‹‹ሶማሊያዎቹ የእናንተን ትእግስት የሚፈታተን የብልግናና የዘለፋ ቃላቶችን ከመሰንዘርም ስለማይመለሱ በእናንተ በኩል እስከ መጨረሻው ትዕግስታችሁን እንጠይቃለን›› (35) መንጌም ምክሩን ካደመጡ በኋላ ‹‹በዚህ በኩል ምንም ስጋት አይግባችው፤ ለትግስቴ ወሰን የለውም›› ሲሉ ቃለ ገቡላቸው፡፡ የሆነው ግን ተቃራኒው ነው፡፡ ያውም ገና ወደ ስብሰባው አዳራሽ ሳይገቡ የጓድ መንግስቱ ትዕግስት ጠፋች፡፡ ‹‹የሶማሊያው መሪ ማንንም ሳያነጋግር ወይም ሳይጨብጥ አዳራሹ ማዕከል ሜዳ ላይ ሁለት እጁን ሱሪ ኪሱ ከቶ ዘለግ ባለ ድምፅ ‹ሁለት ስቱፒድ የሆንን ህዝቦች አስቸገርናችሁ አይደለም?› በማለት ተናግሮ ወደ መቀመጫው ሲያመራ፤ ከአነጋገሩ በላይ ጠቅላላ ሁኔታው፣ ኩራቱና ትዕቢቱ ደሜን ስላፈላው፣ ለትዕግስቴ ዳርቻ አይኖረውም ብዬ ለራሴ ቃል የገባሁት ሰውዬ ‹የራስህን ስቱፒድነት ተናገር፣ እኛ ግን አንተን ወይም እናንተን አይደለንም› ስለው አስተናጋጆቹ ተደናገጡ፡፡›› ይሉናል ጥቃት የማይወዱት እና ‹‹ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር››ን ዝነኛ መፈክር እያሉ የሚያንቆለጳጵሱት ‹‹ቆራጡ›› መሪ፡፡
በዚህ የመጨረሻ ውይይት ላይ ጓድ ዚያድባሬ እና ጓድ መንግስቱ በጦርነት ስልት አዊቂነት ላይም ሲዘላለፉ እና ‹‹አንተ አታውቅም፣ እኔ ነኝ የማውቀው›› የሚል ክርክር አድርገው እንደነበር ተፅፏል፡፡ በወቅቱ ሶማሊያ በኢትዮጵያ ድንበር አካባቢ ይፋ ያልሆነ ውጊያ ማካሄዱን መንግስቱ በመጥቀሳቸው፣ ዚያድባሬ መልስ ሰጡ ‹‹ውጊያው ተጀምሯል ያልከው ስለውጊያ ምንም እውቀት ስለሌለህ ነው፡፡ ውጊያ አልጀመርንም፡፡ ውጊያ ስንጀምር ውጊያ ምን እንደሆነ ታይና ከዚያ ትማራለህ›› አለኝ፡፡ እኔም አስተናጋጁን ይቅርታ ጠይቄ ከጀመራችሁት ሌላ ያቆያችሁት ውጊያ ካለ በማናቸውም ጊዜና ስፍራ ጦርነቱን ልትከፍቱ ትችላላችሁ፡፡ በዚህ ጦርነት ማን ትምህርት እንደሚያገኝ እዚህ ያሉት ኩባዊያንና የመናዊያን ጓዶቻችን ብቻ ሳይሆኑ የአለም ህዝብ በጠቅላላ በቅርብ ጊዜ ውስጥ የሚረዳው ይሆናል ስለ፤ ዚያድባሬም ‹በል ጥሩ ነው ከእንግዲህ ወዲያ በጦር እንገናኝ› ብሎ ከስርዓት ውጪ በብልግና መድረኩን በመርገጥ ስለወጣ የመጨረሻው የሰላም ጥረት በዚሁ ተዘጋ›› ይሉሃል፡፡ በእርግጥ መንግስቱ ያሉትን አድርገዋል፡፡ ምክንያቱም ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ አለም የጦርነቱን አዝማሚያ አይቶ የተጨነቀው ‹‹ኢትዮጰያ ልትሸነፍ ትችል ይሆናል›› ብሎ ሳይሆን ‹‹የኢትዮጵያ ጦር ዳር ድንበሩን በማስከበር ብቻ አይመለስም፡፡ ይልቁንም የሶማሊያን ወሰን ጥሶ የበቀል ወረራ ሊያደርግ ይችላል›› በሚል በመሆኖ ነው፡፡
...እኚያ የሀገሬ ድንበር ባድሜና ሽራሮ ሳይሆን ህንድ ውቂያኖስ ነው የሚሉት፤ እኚያ የአንድ ትውልድ ኢትዮጵያዊንን ደም በጎዳና ላይ ያፈሰሱት፣ እኚያ ኢትዮጵያ ትቅደም ሲሉ ልብ የሚያሞቁት፣ እኚያ ለስልጣን ካላ¬¬ቸው ጥልቅ ፍቅር ጓደኞቻቸውን ሳይቀር አርደው የጣሉት፣ እኚያ… ጓድ መንግስቱ ኃይለማርያም የፃፉት መፃሀፍ ሊነበብ የሚገባው ነው፡፡ ነገር ግን ግርድፉን ከፍሬው መለየት ይጠይቃል፡፡ የሰማዩ መፃሀፉ እንደሚለው ‹‹ሁሉ ተፈቅዷል፤ ነገር ግን ሁሉ አይበላም፡፡›› የገን ሂሉም መፀሃፈ ስለሀገራችን ድንቅ ታረክ እና ሀገርን ስለማፍቀር ብቻ ሳይሆን ስለክህድት እና ውሸትም ብዙ ያስተምራልና፡፡

Comments
tadesse (not verified)
Sun, 01/22/2012 - 03:23
Permalink
Mengistu book
What a great article ! I need the email adress of the author .
Anonymous (not verified)
Sun, 01/22/2012 - 16:55
Permalink
Thank u
Thank u
Anonymous (not verified)
Mon, 01/23/2012 - 13:09
Permalink
plz where i get the book.....
plz where i get the book......
Anonymous (not verified)
Mon, 01/23/2012 - 13:09
Permalink
plz where i get the book.....
plz where i get the book......
Anonymous (not verified)
Mon, 01/23/2012 - 13:09
Permalink
plz where i get the book.....
plz where i get the book......
Anonymous (not verified)
Wed, 01/25/2012 - 09:27
Permalink
i got the book freely from
i got the book freely from this site Thanks all
http://zelalemkibret.files.wordpress.com/2012/01/mengistu_book.pdf
ashe (not verified)
Tue, 01/24/2012 - 16:20
Permalink
wow great
wow great
ነጻነት.bh (not verified)
Fri, 01/27/2012 - 05:18
Permalink
እረ ተሜ ይህ እዳለ ሆኖ አረ ለነዚ ሰዎች
እረ ተሜ ይህ እዳለ ሆኖ አረ ለነዚ ሰዎች ንገሩአቸው ገንዘብ እያሳተሙ ገብያ ላይ መርጨት ምን ያህል አገር እንደሚጎዳ....የሚገርመው ይህ አትመው የሚያስገቡት ብር ማን እጅ ውስጥ እንደሚገባ ታውቃላችሁ እጅግ በጣም ጥቂት ግለሰቦች እጅ...እኛስ ምን ይዋጠን....ባንክ አከባቢ ስለሆንኩ ብዙ ነገር እናያለን እንሰማለን ...ባለፈው ወር መንግስት ከውጭ በ ቢሊዮን የሚቆጠር ብር እስገብቶአል ይሄ ምን ማለት ነው፤ በቅርቡ ደሞ ከ 200 ሺህ ብር በላይ የሚያንቀሳቅሱ ግለሰቦችን የግል ባንኮች ሪፖርት ለወያኔ ሪፖርት ያደርጋሉ ይሄስ አግባብ ነው ወይ እስኪ እናንተ ትንታኔ ስቱበት...አሁን በቅርቡ የተመሰረተችው ደቡብ ሱዳን ምን ያህል ከኛ የተሸለ ገንዘቦ ጠንከራ እንደሆነ በምዛሬ ዋጋ አይተናል...ለዚህ ነው ያገራችን እህቶቻችንና ወንድሞቻችን ወደዛ በችግር የሚሰደዱት....እረ መረረን የት እንሂድ
Add new comment