የ “ተቃውሞ” ተቃዋሚ ታጋዮች...
(ገጽ 5 ቅፅ 4 ቁጥር 150 አርብ 20 ነሐሴ 2003ዓ.ም)
ተመስገን ደሳለኝ
የትግል ሜዳ እና የትግል ፖለቲካ፡፡ በእርግጥ ትግል ጥሩ ነው፡፡ ፖለቲካም እንዲሁ፡፡ ሰው እንኳን ለሀገሩ፤ ለግል ጥቅሙስ ይታገል የለም እንዴ? ትዕዛዙስ ቢሆን “ታግለህ ብላ (ጥረህ ግረህ ብላ…” ነው የሚለው፡፡ እናም ሀገራችን ከውልደቷ ጀምሮ ዛሬም ድረስ በትግል ላይ ነች፡፡ በእርግጥ ከእኛዋ ኢትዮጵያ በኋላ የተወለዱ ብዙ ሀገሮች የትግል ጉዞአቸውን ጨርሰው፤ በትግል የአገኙትን በማስፈፀም እና በማጨድ ላይ ናቸው፡፡ ...እዚህ ደግሞ ገና በመዝራት ላይ እና...
...አፄ ኃ/ስላሴን ለመጣል ብርቱ ትግል ተደርጓል፡፡ ከብርቱ ትግል በኋላም አፄ ኃ/ስላሴ ወረዱ፡፡ ትግሉ ግን ተፋፋመ እንጂ አልበረደም፡፡ “ፋኖ ተሰማራ እንደ ቼጉቬራ...” ተዘመረ እንጂ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት አልመጣም ወይም የህግ የበላይነት አልተከበረም፡፡ የመደራጂያ ስማቸው ላይ “ትግል” የሚል ቃል እየጨመሩ በርካታ ድርጅቶች ተመስርተውም ትግል ጀመሩ፡፡ የማታ ማታም ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ (TPLF) ደርግን ታግሎ የመጣሉ ትግል ተሳካለት፡፡ ይሄም ሆኖ ግን ትግሉ አልቆመም፡፡ የቱ ትግል? የፀረ ድህነቱ፣.. በጭራሽ፡፡ የፖለቲካ ትግሉ እንጂ፡፡ ዴሞክራሲ የለም፣ የሰብዓዊ መብት ይጣሳል፣ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት የለም፣ በነፃ የመደራጀት መብት አልተከበረም፣ሃሳብን ያለገደብ በነፃነት የመግለፅ መብት አልተከበረም ወዘተ... የሚሉ ታጋዮች “ታጋይ ይሞታል እንጂ ትግል አይሞትም” ብለው ትግላቸውን ቀጥለዋል፡፡ በእርግጥ ህወሓትም ቢሆን ትግሉ አልቋል ብሎ የአመነ አይመስለኝም፡፡ ለዚህ ደግሞ እንደምክንያት ሊጠቀስ የሚችለው የመታገያ ስሙ እንኳ አለመቀየሩ ነው፡፡ ዛሬም Tigray People Liberation Front (የትግራይ ህዝብ ነፃ አውጪ ድርጅት) እንደሆነ ነው፡፡ ይሄ ለምን ሆነ የሚለው ጥያቄ የእኔ ብቻ ሳይሆን የብዙዎች ነው፡፡ ..ነፃ አውጪ ..... ሲባል እያሉም ይጠይቃሉ፡፡ ማን ከማን ነው ነፃ የሚወጣውስ? ሲሉም ይመራመራሉ፡፡ አንዳንዶች ይህች ቃል “የትግራይ ህዝብ”ን ማደናገሪያ ናት ሲሉም መላምት ይሆን ትንተና ያለየ ነገር ያቀርባሉ፡፡
የሆነ ሆኖ ግን የዚህ ፅሁፍ አላማ የፀረ ደርግ ትግሉ ተጠናቆ የፀረ ኢህአዴግን ትግል የተቀላቀሉ “ታጋይ ድርጅቶችን” ጉዞ በጨረፍታ ማየት ነውና ወደዛው ብናመራ ይሻለናል... የደርግ ፀሀይ ጨልማ፣ የኢህአዴግ ፀሐይ በፈነጠቀች ማግስት በርካታ የፖለቲካ ድርጅቶች “የፀረ ኢህአዴግ ትግሉን” ተቀላቀሉ፡፡ የትግል ካርዳቸው ሲፋቅ ደግሞ ..አዲሱ መንግስት (ኢህአዴግ) ሀገር አስገንጣይ እና በብሔር ከፋፋይ ነው.. የሚል ነበር፡፡ በእርግጥም ይሄ ወቅት ብዙዎች ተስፋ የቆረጡበት ነው፡፡ ምክንያቱም ደርግ ከወደቀ በኋላ የኢትዮጵያውያኖች ትግል የፖለቲካ ሳይሆን የፀረ-ደህነት ይሆናል የሚል ተስፋ በመሰነቃቸው ነበር፡፡ የሆነው ግን ሌላ ነው “አዲስ ዙፋን እንጂ ለውጥ...” እንደተባለው ማለቴ ነው፡፡ እናም ትግሉ ቀጠለ፡፡ ይች ሀገር የተፃፈላት እጣ ፈንታ “ህዝቦቿ ዝንተ አለማቸውን ሲታገሉ ይቆዩ” ተብሎ ይሆን ወይም አንዳንድ የዋህኖች እንደሚሉት አፄ ኃ/ስላሴ “ወጣት አይብቀልብሽ” ብለው እረግመዋት ይሆን አይታወቅም ብቻ ሀገሪቱ ዛሬም በፖለቲካ ትግል ውስጥ ነች፡፡ እናም እነዛ ታጋይ ድርጅቶችም ብዙ ተስፋ ሲሰጡ ከረሙ፡፡ ተስፋ... የተስፋ ዳቦን፡፡ ከቶስ ተስፋ አድርጎ ያገኘ ማን ይሆን?
ስፍር ቁጥር የሌላቸው ፓርቲዎች ተመስርተው እንደነበረ ይታወቃል፡፡ በእርግጥ ከእነዚህ ውስጥ “ጓዳ ሰራሽ” ፓርቲዎች አብዛኛውን ቁጥር ይይዛሉ፡፡ በይበልጥ ደግሞ እነ አማራጭ ሀይሎችን እና መአህድን ለይተን ካወጣን የቀሩት ሙሉ በሙሉ በኢህአዴግ ጓዳ የተሰሩ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ የዚህ ፅሁፍ አላማም ነፃ የሆኑት ፓርቲዎች እራሳቸው በ20 ዓመት ትግላቸው ምን አመጡ? የሚለውን ማየት ነው፡፡ ሆኖም ግን እዚህ ቦታ ላይ ፓርቲዎቹን ዘርዝሮ ለመፃፍ አንድ ችግር አጋጥሞኛል፡፡ ያ ችግር ምን መሰላችሁ? ፓርቲዎቹ በህዝብ ዘንድ ካላቸው ታዋቂነት ይልቅ አመራሮቹ (በተለይ ሊቃነመናብርቱ) ያላቸው ታዋቂነት በብዙ እጥፍ በልጦ መገኘቱ ነው፡፡ እናም አብዛኛው ህዝብ ፓርቲውን ሳይሆን ሊቀመንበሩን ነው የሚያውቀው ማለት ነው፡፡ ስለዚህም እንደ መፍትሄ ይሆን ዘንድ ከፓርቲው ስም ይልቅ የአመራሩን ስም በመጥቀስ ብንነጋገር ይሻላል፡፡
በየነ ጴጥሮስ፣ ኃይሉ ሻወል፣ ጌታቸው መንግስቴ፣ መራራ ጉዲና፣ ግዛቸው ሽፈራው፣ ኃይሉ አርአያ፣ ልደቱ አያሌው፣ አስራት ጣሴ፣ማሙሸት አማረ... እያልን ብንዘረዝራቸው መልካም ነው፡፡ እነዚህን ስሞች ሚሊዮናት ኢትዮጵያውያን ጠንቅቀው ያውቋቸዋል፡፡ ፓርቲያቸውንስ? ለምሳሌ በየነ ጴጥሮስ በ1983 ወርሀ ሰኔ የሽግግር መንግስቱ ሲመሰረት ጀምሮ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ናቸው፡፡ ፓርቲያቸውን ግን ስንቱ በስም ለይቶ ያውቀዋል? የሚለውን ብናየው ጥሩ አስረጅ ነው፡፡ እሳቸውን ግን ብዙዎቻችን ጠንቅቀን እናውቃቸዋለን፡፡ ግለኝነት ማለትም ይሄ መሰለኝ፡፡ መራራ ጉዲና በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በረዳት ፕሮፌሰር ማዕረግ ስመ ጥር የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ናቸው፡፡ በፖለቲካው ትግል ላይ ግን ምን አበረከቱ? ብለን ብንጠይቅ፤ አብዛኛው ሰው ትዝ የሚለው ሹፈት እና ቀልዳቸው ነው፤ ይሄ እንግዲህ የትግሉ አካል ሆኖ ቆይቷል፡፡ ኢ/ር ኃይሉ ሻወል የ97ቱን ቅንጅት በሊቀመንበርነት የመሩ ብርቱ ታጋይ ነበሩ፡፡ ዛሬስ? ዛሬማ የጥቂት ሰዎች አለቃ ብቻ የሆኑ ይመስለኛል፡፡ ቴዎድሮስ አደባባይ ያለው ቢሮአቸው ብቅ ብትሉና በሩን ብትቆረቁሩ የጥበቃ ሰራተኞች ማንነታችሁን በቀዳዳ አይተውና አረጋግጠው ነው የሚከፍቱላችሁም እንጂ በዋዛ ማንም አይከፍትላችውም፡፡ መቼም የዚህ አይነቱን ገጠመኝ በባለስልጣናት መኖሪያ ቤት እንጂ ህዝባዊ ትግል እያካሄድኩ ነው በሚል ፓርቲ ጽ/ቤት ውስጥ ይኖራል ብሎ የሚያስብ የለም፡፡ ግን አለ፡፡ ማየት ማመን ነውና ብቅ ብላችሁ ማረጋገጥ የእናንተ ፋንታ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ስለ መኢአድ ሙት አመት እዚህችው ቦታ ላይ ተነጋግረን እርም መብላታችን ይታወሳል፡፡ በቅርቡ በመኢአድ ሰዎች መካከል ያለውን ሽኩቻ ስናየው ደግሞ ከፊታችን ቀድሞ ድቅን የሚለው “ክትክት የበዛበት የቻይና ካራቴ ፊልም” ነው፡፡ ከ7 ወር በፊት መኢአድ ጠቅላላ ጉባኤውን ሲያካሄድ የመኢአድ ሰዎች “ያዕቆብ ልኬ ወደ ምክትል ተቀዳሚ ሊቀመንበርነት መምጣት የለበትም” ብለው ተከራከሩ፡፡ ኃይሉ ሻወል ደግሞ ‘በያዕቆብ ላይ የሚወራው ሁሉ አሉባልታ ነው፡፡ ይሄን ፓርቲ ሊመራ የሚችለው ያዕቆብ ልኬ ብቻ ነው” አሉና ፍርድ ሰጡ፡፡ ጥቂት የማይባሉ የፓርቲው ሰዎች ‘ፍርደ ገምድልነት ነው” ብለው አጉረመረሙ፡፡ አጉረምርመው ሲያበቁም፤ በታዲዎስ ቦጋለ እና በማሙሸት አማረ እየተመሩ የካራቴ ክህሎታቸውን ሊያሳዩን ግብ ግብ ገጠሙ፡፡ ማስተሩ (ኢንጂነር ኃይሉ) ምክትል ሊቀመንበር የነበሩትን ዶ/ር ታዲዎስ ቦጋለን እና ዋና ፀሐፊውን ማሙሸት አማረን ጨምሮ በርካታ አመራር እና አባላትን ህጋዊ ይሁን ህገወጥ ለይቼ ባላወኩት የእግድ ደብዳቤ ድራሻቸውን አጠፉ፡፡ ድራሻቸው መጥፋቱን ካረጋገጡ በኋላ ደግሞ ያዕቆብ ልኬን ባለሙሉ ስልጣን ተቀዳሚ ሊቀመንበር አድርገው ቀቡአቸው፡፡ እኛ የዳር ተመልካቾች በወቅቱ በ “ሹመት” በመቀባት.... እና በ “መመረጥ” መካከል ትልቅ ገደል አለ ብለን ብንናገርም ኢንጂነሩ ሊሰሙ አልወደዱምና የወደዱትን አደረጉ፡፡ በዚህ ሰሞን እንደሰማነው ከሆነ ደግሞ ያዕቆብ ልኬም በተራቸው የካራቴዋን ፀበል ቀምሳው ከፓርቲው “ንካው ወደ መጣህበት” ተብለዋል፡፡ ሌላው የመኢአድ አስቂኙ ድራማ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ በነበሩት ጌታቸው ባያፈርስ ተደርሶ እና በራሳቸው ተዘጋጅቶ፤ እራሳቸው የተወኑት ነው፡፡ የድራማውን ጥቂቱን ክፍል ብናስታውሰው እንዲህ የሚል ሆኖ እናገኘዋለን፡፡...እኔ ጌታቸው ባያፈርስ መኢአድ ከአንድነት ጋር የተጀመረውን ውህደት ከግብ እንዳይደርስ “ወገቤ”ን እያለ በመሆኑ ከምወደው ድርጅት ለቅቄ ወደ አንድነት ተቀላቅያለው... በዚህች ቅንጫቢ ድራማ ወይ ጉድ ብለን ተገርመን ሳናበቃ ወደ መኢአድ ለመመለስ እንደ ፋብሪጋስ እየተደራደሩ ነው ተባልን፡፡ እነሆ እንግዲህ እነሱ እንደሚሉት ከሆነ ደግሞ ይሄም ለህዝብ የሚደረገው ትግል አካል ነው፡፡
ወደ አንድነት ፓርቲ ደግሞ እንመለስ፡፡ በምስረታው ወቅት የነበሩት የአመራር አባላት ከፓርቲው የወጣቶች የአመራር አባላት (ፕ/ር መስፍን፣ አቶ አመሃ ዳኘው፣ አርቲስት ደበበ እሸቱ እና ዶ/ር ሽመልስ ተ/ፃዲቅንም ይጨምራል) ጋር በተፈጠረ እሰጥ እገባ በፓርቲው ጽ/ቤት በር ላይ እንደጦስ ዶሮ ደማቸው ሁሉ ደመ ከልብ የሆነ አባላት ነበሩ፡፡ ከደም መፋሰሱም ባሻገር በግዛቸው ሽፈራው የሚመራው የአመራር አባል በፓርቲው ውስጥ ዴሞክራሲ ይስፈን፤ መርህ ይከበር ያሉትን አሁንም “ማገጃ” የሚል ስያሜ ባለው ደብዳቤ ከፓርቲው ጽ/ቤት 40 ክንድ አራቃቸው፡፡ “ታጋጆቹም” የዋዛ አልነበሩምና ከአመት በላይ ነክሰው ይዘው የተቃዋሚ “ፎቢያ’ እስኪይዘን ድረስ አንገሸገሹን፡፡ በነገራችን ላይ ያን ሰሞን (በአንድነት ውስጥ ችግር የተፈጠረ ጊዜ) ለብዙ ሰዎች ኢህአዴግ ከስልጣን የለቀቀ መስሎአቸው ነበር፡፡ ምክንያቱም አንድነቶች እና ዝም አንልሞች እርስ በእርሳቸው “ሲቀዋወሙ” ኢህአዴግን እስከነ መፈጠሩም በመርሳታቸው ነው፡፡
መራራ ጉዲናም ቢሆኑ የሚያስጨበጭብ የትግል ታሪክ የላቸውም፡፡ በኢህአዴግ ላይ መቀለድ የመጀመሪያም የመጨረሻም የትግል ስልት እስኪመስለን ድረስ ቀልድ በቀልድ ስላደረጉን ነው፡፡ መቼም በቀልድ ስልጣን የለቀቀ ፓርቲ በየት ሀገር እንደሚገኝ ዋቢ እያቀረቡ ቢቀልዱልን ኖሮ ቢያንስ ቀልዳቸውን “አሁንስ በዛ” ብለንም ባላማረርንም ነበር፡፡ የዶ/ሩ ፓርቲ የኦሮሞ ህዝብ ኮንግረስ የሚል ስያሜ ይዞ በግልባጩ ደግሞ የሀገሪቱን እስር ቤት ያጣበቡት ንፁሃን የኦሮሞ ተወላጆች ስለመሆናቸው ትዝም ብሎት የሚያውቅ አይመስለኝም፡፡ በእርግጥም አብዛኛው ኦሮሞ በመሆናቸው ብቻ የታሰሩ እንደሆነ ሲገባን ነው የቀልድ ፖለቲካ የሚደብረን፡፡ ለነገሩ እኮ እሳቸው ግልፁን ተናግረዋል “ቢራ እየጠጣው ነው መታገል የምፈልገው”ሲሉ፡፡ አልሰማ ያልነው እኛ ነን እንጂ፡፡
ብቻ ምን አለፋችሁ ብዙዎቹ ፖለቲከኞቻችን ከቆሙለት አላማ ይልቅ፤ የግል ስብዕና (Personal cult) ሲገነቡ መክረማቸውን አሁን አሁን ነው እየተገለፀልን የሄደው፡፡ እዚህ ጋር ግን መታለፍ የሌለበት አንድ ነገር አለ፡፡ ምስጋና፡፡ እነዚህ ስማቸው የተጠቀሱ ሰዎች ፓርቲያቸውን የቱንም ያህል እንዲራመድ ባያደርጉትም በኢትዮጵያ ውስጥ የተቃዋሞ እንቅስቃሴ ባልታሰበ እና ባልተጠበቀ ሰዓት “ጃም” ተደርጎ አንቀሳቃሾቹ ዘብጥያ ሊወርዱ እንደሚችሉ እያወቁ፤ ቤተሰቦቸውን ትተው ወደ ትግሉ መግባታቸው በእጅጉ የሚያስመሰግናቸው ነው፡፡ “ሆድ ብቻ’’ ያላቸው ኢትዮጵያውያኖች እንደ አሸን በፈሉበት ምድር እነዚህ ሰዎች ሀገር እና ህዝብ ማለታቸው በራሱ ትልቅ አክብሮት እና ምስጋና የሚያሰጣቸው ነው፡፡ ሆኖም ግን አክብሮት እና ምስጋና ዴሞክራሲም የመድብለ ፓርቲ ስርዓትም ሆኖ አያውቅም፡፡ እናም ወደ ትግሉ መቀላቀላቸው ሲያስመሰግናቸው፤ መስራት እየቻሉ ባለመስራታቸው፤ በውስጣቸውም “ቀጫጫ አምባገነንነት በመስረፁ” እንዲህ ልንተቻቸው በቁ ማለት ነው፡፡ ለነገሩ ያልተተቸ የት ይደርሳል፡፡
ብንቀበለውም ባንቀበለውም አሁን ያሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች አሁን ካላቸው Performance (ብቃት) ብዙ ሺ ጊዜ ካላደጉ የትም አለመድረሳቸውን ነው፡፡ ከታግሎ ማታገል ይልቅ ፓርቲዎቹ እርስ በእርሳቸው፤ አመራሩ ከሌሎች አመራር እና አባላቱ ጋር ሲወጋገዝ መሽቶ እየነጋ ነው፡፡ የተቃውሞ ድምፃቸው በሙሉ ከገዥው ፓርቲ ይልቅ በተቃዋሚዎች ሰፈር ይስተጋባል፡፡ እርስ በእርስ መጯጯህ ለማን ጠቀመ? ለባቢሎንም ቢሆን እንኳ... ተቃዋሚ ፓርቲዎች እርስ በእርስ ሲቀዋወሙ በርካታ የማታገያ ካርዶቻቸውን ኤክስፓየርድ እያደረጉት ነው፡፡ በተለይም የወቅቱ የአፍሪካና የአረብ ሀገራት ሁኔታ እንዲሁም የኑሮ ውድነት፣ ድርቅ የግብር ጣጣ ፈንጣጣ... የሚባል ዋጋ ያላቸው ካርዶች ኤክስፓየርድ እያደረጉ መሰለኝ...

Comments
Anonymous (not verified)
Sat, 09/10/2011 - 11:11
Permalink
My dear u wrote what u feel
My dear u wrote what u feel but simply u wrote it b/s they exert a lot though u discourage them z field s not fare gun &bare hand r not equal +ty r in a way of strugle &in z mind of people as well but u insult them dr,merara &others u may write for bread pls don't discourage all z real 1.&z reader.u become 'agemtekem'.believe or not all oponent party except 'teletafi' r in our heart.
ሄለን (not verified)
Wed, 09/14/2011 - 17:01
Permalink
Go Depper
You have got a good and uncommon idea of critisizing the opposition. If we were brave enough to share our critics of the EPRDF to the opposition, our camp could have enjoyed a lot of sucess. So I would love if you keep on the good work so that we will have a chance to discuss on the essue on greater detail. I was looking for an argument on major parties like OFDM and EDP
Add new comment