የአፍሪካ ኀብረት ዓለም በቃኝ ገባ

የአፍሪካ ኀብረት ዓለም በቃኝ ገባ
ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም
የዛሬ አርባ ዘጠኝ ዓመት ግድም በአፍሪካ አዳራሽ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (የዛሬው የአፍሪካ ኀብረት) ሲመሠረት ተመልካች ሆኜ ገብቼ እዚያው አድሬአለሁ፤ የዛሬዎቹ ወጣቶች ያቺን ኢትዮጵያና እነዚያን ኢትዮጵያውያን የሚያውቋቸው አይመስለኝም፤ አንዳንዴ ሳስበው ግምትም ያላቸው አይመስለኝም፤ የነሱ ጥፋት አይደለም፤ ሥርዓት ባለው መንገድ ሥራዬ ብሎ፣ የአገር ጉዳይ ነው ብሎ ያስተላለፈላቸው የለም፤ ዛሬ የንክሩማ ሐውልት በአፍሪካ ኀብረት ግቢ ቆመ የሚል ወሬ ስሰማ ደርግ በአፍሪካ አዳራሽ መግቢያ ላይ የሌኒንን ሐውልት መትከሉን አስታወሰኝ፤ ዛሬ ደግሞ ወያኔ ከማን አንሼ ብሎ የንክሩማን ሐውልት በአፍሪካ ኀብረት ግቢ ውስጥ ተከለ፤ ንክሩማ ትልቅ አፍሪካዊ ነው፤ ነገር ግን ለአገሩም አልበቃም፤ በምንም ዓይነት መንገድ አጼ ኃይለ ሥላሴን አይተካም፤ ኢትዮጵያ ሰው አጥታ ከጋና መበደርዋ ኢትዮጵያ የወረደችበትን አዘቅት ያሳያል፤ እነማን ይዘዋት እንደወረዱም ግልጽ ነው፤ አንድ ሰው ብቻ፣ አጼ ኃይለ ሥላሴ፣ የተዋረዱ እንዳይመስለን፤ የተዋረደችው ኢትዮጵያ ናት፤ እንደተለመደው ጠምዝዘው ጋናን ማጣጣል ወይም የጋናን ክብር መቀነስ አድርገው የሚያቀርቡት ይኖሩ ይሆናሉ፤ የምለው ጋና ከኢትዮጵያ አትቀድምም፤ ንክሩማም ከአጼ ኃይለ ሥላሴ አይቀድምም ነው፤ ንክሩማም ቢኖር በአፍሪካ ኀብረት ጉዳይ ከአጼ ኃይለ ሥላሴ ጋር ለውድድር አይቀርብም ነበር፤ ጋና ነጻ በወጣችበት እለት በዓሉን ለማድመቅ የሄዱት ልዑል ሣህለ ሥላሴና አቶ አበበ ረታ ነበሩ፤ ከተመለሱ በኋላ አቶ አበበ በብሔራዊ ቤተ መጽሐፍት ስለጋና ንግግር አድርገው አዳምጫለሁ፤ ኢትዮጵያኮ በኢጣልያ ወረራ ጊዜም የአርበኞችዋን ነፍስ ይማርና ሰንደቅ ዓላማዋ ሲውለበለብባት የነበረች አገር ናት፤ የአርበኞችዋን ነፍስ ይማር! ሐውልት ባናሠራላቸውም ሲናቁብን በአርምሞ ልናልፈው አንችልም፡፡
አርበኞችን ወደዳር ማስወጣትና የሥልጣን ወንበሮችን በባንዳዎች ማስያዝ አጼ ኃይለ ሥላሴ የጀመሩት ቢሆንም ለልጅ ልጅ የሚተላለፍ የአገር ውርደት መሆን የለበትም፤
በቅርቡ ሪፖርተር በርእሰ አንቀጹ የሀሳብ ማጠራቀሚያ (ቲንክ ታንክ) በሚል ርእስ ጽፎ ነበር፤ ከሹሞቹ ውጭ ሰዎች መኖራቸውን፣ የማሰብ ችሎታ ያላቸው መሆኑን፣ ሀሳባቸውን የሚያዳምጥ መኖሩን ካላረጋገጥን ሀሳቦች ዋጋ የላቸውም፤ የንክሩማን ሐውልት በኢትዮጵያ ለመትከል ወይም የሌኒንን ሐውልት በኢትዮጵያ ለመትከል ከአንድ ሰው በቀር አይወስንም፡፡

የአፍሪካ አንድነት የተቋቋመው እ.ኤ.አ. በ1963ዓ.ም. ነው፤ በዚያን ጊዜ ኢትዮጵያ በመላው ዓለም ከፍ ያለና የተከበረ ስም ነበራት፤ በአፍሪካ ያለምንም ጥርጥር ቀዳሚዋ አገር ነበረች፤ ኢትዮጵያን ለዚህ ያበቃት ረጅም የነፃነት ታሪክዋ፣ የህዝቡ ጨዋነት፣ የመሪዎቹ፣ በተለይም የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ግርማና ሞገስ አንድ ላይ ሆነው ኢትዮጵያን የተከበረችና የተፈራች አገር አድርገዋት ነበር፡፡
ለአፍሪካ ኀብረት የተሰበሰቡት በዘመኑ የነበሩ ታላላቅ መሪዎች፣ አገሮቻቸውን ከቅኝ አገዛዝ ያወጡ ሰዎች ነበሩ፤ መሪዎቹ በየሰፈራቸው የጎረቤቶች መኀበር እያቋቋሙ ለትልቁ የአፍሪካ አንድነት እምብዛም ግድ አልነበራቸውም፤ ምናልባትም የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን በማቋቋም እያንዳንዳቸው በየአገራቸው ያላቸው ሥልጣን የሚ¬¬¬-ቀነስባቸው መስሎአቸው የነበረ ይመስለኛል፤ አብዛኛዎቹ እናጥናው፣ እናብላላው በማለት የድርጅቱን ምሥረታ ለማስተላለፍ በፓም ይጥሩ ነበር፤ አጼ ኃይለ ሥላሴ ግን የድርጅቱ ሰነድ ሳይፈረም ማናችንም ከአዳራሹ አንወጣም ብለው ገትረው ያዙአቸው፡፡
የአጼ ኃይለ ሥላሴ ትልቅነትና የኢትዮጵያ የመንፈስ መሪነት በገሀድ ታየ፤ እንደናስርና እንደቤን ቤላ ያሉ አብዮተኞች ሳይቀሩ ከጃንሆይ ጋር ሲነጋገሩ ጎንበስ ብለውና እጆቻቸውን ወደኋላ አጣምረው ነበር፤ መቼም የዚህ ፊልም አንድ ቦታ ይኖራል ብዬ ተስፋ አለኝ፤ የዛሬ ወጣቶች ሁሉ ሊያዩት የሚገባ ነው፤ እምቢተኞቹንና አፈንጋጮቹን ሁሉ አንድ በአንድ እያነጋገሩ፣ እንደኒዬሬሪና አሚን ተጣልተው የማይነጋገሩትን እያስታረቁ ሰነዱ ሳይፈረም መውጣት የለም አሉ፤ እንደማስታውሰው ሰነዱ ከሌሊቱ በስምንትና በዘጠኝ መሀከል ተፈርሞ አለቀና ሲነጋ በየቤታችን ገባን፡፡
የአፍሪካ አንድነት በጋዳፊ (ነፍሱን ይማረውና) ውትወታ የአፍሪካ ኀብረት ተባለ፤ ስልቻ ቀልቀሎ፣ ቀልቀሎ ስልቻ ነው፤ ዓላማው የአፍሪካን ሕዝቦች የኑሮ ደረጃ ከፍ ለማድረግ፣ የአፍሪካ አገሮችን ሉዓላዊነትና ነጻነት ለመጠበቅና ከማናቸውም ዓይነት ቅኝ አገዛዝና ቄሣራዊ ተጽእኖ ለመከላከል ነበር፤ ነበር፤ ነበር፤ በአገሮች መሀከል የሚከሰቱ ችግሮችን ሁሉ በሰላማዊ መንገድ መፍትሔ እንዲገኝላቸው ማድረግ ነበር፤ ነበር፤ ነበር፡፡
እንደዚያ ዕለት በኢትዮጵያዊነቴ ኮርቼ አላውቅም፤ ስለዚህም የኢትዮጵያውያን የዩኒቨርስቲ መምህራን ማኀበር ስብሰባ ጠራሁና ያየሁትን ገልጬ ለአጼ ኃይለ ሥላሴ የምስጋና ደብዳቤ እንጻፍላቸው የሚል ሀሳብ አቀረብኩ፤ አንዳንድ ተቃውሞ ተነሥቶ ከተከራከርንበት በኋላ እንዲጻፍላቸው ተወሰነ፤ ዳብዳቤውን ጽፌ ለጃንሆይ እንዲሰጥልን ለዩኒቨርስቲው ፕሬዚደንት ለልጅ ካሣ ወልደማርያም አስረከብሁት፤ ከጥቂት ቀናት በኋላ ጠራኝና አንተው ወስደህ ብትሰጥ ይሻላል አለኝ፤ የምሄድበትን ቀንና ሰዓት ነገረኝ፤ ወስጄ በእጃቸው ሰጠኋቸው፤ እንዳነበቡት ወይም እንደተነበበላቸው ፍልቅልቅ ባለ ደስታቸው ይታይ ነበር፡፡
ዛሬ የአፍሪካ አንድነት (ኀብረት) በቻይና ቸርነት ፎቅ ተሠርቶለት ዓለም በቃኝ ገባ አሉ፤ የአፍሪካ መሪዎችም እዚያው ተሰበሰቡ፤ አቶ መለስም ለቻይና አስተዋጽኦ ዋጋ ለመክፈል ለማኦትሴ ቱንግ ተማሪ ሐውልት አስተከለ፤ ቀጥሎም የአፍሪካ መሪዎች በምን ምክንያት ወደ አውሮፓ ዓለም-አቀፍ ፍርድ ቤት ይሄዳሉ በማለት አቶ መለስ ተቆጥቶ በዓለም-በቃኝ ፎቅ ውስጥ የአፍሪካ ፍርድ ቤት ማቋቋም እንችላለን የሚል ሀሳብ አቀረበ ተባለ፤ ማን በማን ላይ እንዲፈርድ ይሆን? የአውሮፓ ዓለም-አቀፍ ፍርድ ቤት የተፈራው ምኑ ነው? ወይስ የዓለም-አቀፍ ትርጉም ችግር ሆኖ ነው? መቼም የአፍሪካ ፍርድ ቤት ዓለም-አቀፍ ደረጃ ላይ ይውጣ ማለት…ምን ማለት ይሆን? የተባበሩት መንግሥታትስ መቼ ነው ተለይቶ ‹‹አፍሪካዊ›› የሚሆነው?
ለማናቸውም በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ሆነው የሚመለከቱን የኢትዮጵያ አርበኞች ይቅር ይበሉን፤ ለኢትዮጵያም ከሌኒን ያወጣት አምላክ ያውቃል!

Comments

hi i like u so.i respect all of u .
we love u

Long live "Abatachen" Prof. Mesfin. You are a live, truth and nationalistic encyclopedia of Ethiopia

splendid

ኢትዮጵያ ብሩክታዊት አገራችን ልጆቿ እንደ ባቢሎናውያን ቋንቋ የማይግባቡባት የረመጥ ምድር ሆና ዘመናት አስቆጠረች::ሁሉንም የጦርነት ጊዜዎች እያሳለፉ እና የሚፈጁትን አሕዛብ እያፋጁ ዛሬ ወደ ተደፈቅንበት የደም ግንዳ ቁልቁል ተወርውረናል::ውርደትን ከለበስን እና ስደትን በሞት ድፍረት ከተጫማን ሁለት አሥርተ-ዓመታት መቆጠራቸውን በየልቦናችን ፅላት ያልጻፍን ብንኖር"አለን" ብለን ለመናገር ሌላ ልብ ያስፈልገናል:-እናም የለንም::
ወደተነሳሁበት ዓላማ ልውሰዳችሁና:-ማንኛውም ሰው ጊዜን ተጠልሎ ሥልጣኑን ጨብጦ ብልጣብልጥ ሆኖ"ከቼስ ጨዋታ"በላቀ ከሮቦት ፍጥነት በመጠቀ ከሰይጣን ባገኘው ክፉ-መንፈሳዊ ችሎታ ተጠቅሞ የሚፈልገውን ደም አፍስሶ ያሻውንም ገድሎ ለሚመስለው ጠቅሞ ማንም ሳያቆመው በዕድሜው ሊኖር ይችላል::ኃያሉ እግዚአብሔር ግን ታጋሹ አምላካችን ግን እንደነዚህ ዓይነቱን ሰዎች ባደባባይ ትቢያ እና የተዋረዱ መሆናቸውን ለሕዝብ በመቀጣጫነት ያሳያቸዋል::
ለምሳሌነት እኛ ከምናውቃቸው እንጀምር:-ለምን???ምሳሌም አያስፈልግም:-የእግዚአብሔር መምጫው አይታወቅም::እኛን ኢትዮጵያውያንንም የሚቀጣን ለዓለም ሕዝብ ታምራትን ሊያሳይ ነውና እኛ በሰብዓዊነታችን ማድረግ የሚገባንን ሥጋዊ ግዴታ እንወጣ::በመንፈሳዊ ህሳቤዬ ግን የሚታየኝ ሁለት አማራጮች ናቸው ያሉት:-ወይ እንደ ቻይናውያን ዕምነት እግዚአብሔርን ወደሚከዳ የቁስ-አምልኮት መጓዝ አሊያም ወደኢትዮጵያውያን በእግዚአብሔር መኖር አምኖ ለተሻለ ሕይወት በፀሎት ማደር::ምርጫው ከየግላችን ሕይወት ይጀምራል::
በሥጋዊ ሕይወታችን ስንመጣ ግን ገንዘብ የሰጠኝ ሰው ሥጦታው ዕምነቴን ላለማስቀየሩ በቂ መረጃ ሊኖረኝ ይገባል::ዛሬ ቻይናውያን በየመንግሥታቶቻችን ልመና በሰላም ሥም እየተዘሩ ነው:-ነገ በኃይል የአፍሪቃን አህጉር ላለመያዝ ምን በቂ ኃይል አለን ከእግዚአብሔር በስተቀር::
ብታምኑም ባታምኑም Chinese Women Army MUST SEE ይህን"ፔስት;ጫን"አድርገው የሴቶቹን ወታደሮች ብዛት ብቻ ይመልከቱ::በነገራችን ላይ የአሜሪካ ሕዝብ ብዛት 298,244,215 ሲሆን የሚገርመው የወንዶችን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ሳይጨምር የሴት ወታደሮች ቁጥር ብዛት ብቻ 324,701,244 ነው::ምን ማለት እነዚህ በእግዚአብሔር የማያምኑ እና ከሒትለር ግድያ ልዩነት የሌላቸው የማኦ ሴንቱንግ:-የስታሊን እና "የዳርዊንን"አስተሳሰብ አራማጆች ዛሬ በኢትዮጵያ ቅድስት ምድር ላይ ሰፍረዋል::ዋናው የጥፋት ምንጭ የራሳቸውን ሕዝብ ያፈኑና ለአምባገነኖች ከፍተኛ ድጋፍ የሚሰጡት ጥፋቱን ያለርህራዬ ስለሚያፋጥኑላቸው እንጂ እቅዳቸው አለምን ዛሬ በስምምነት ነገ በኃይል ይዘው የምን እግዚአብሔር ሊሰኙን ነውና ትግሉ የትውልድ ስለሆነ ዛሬ አናስጀምራቸው ቢያንስ እንወቀው::የመጨረሻው ጦርነት በኢትዮጵያ እና በቻይና ማለትም በእግዚአብሔር በሚያምኑ በእግዚአብሔር ባማያምኑ ሕዝቦች መካከል ይሆናልና::

...ጎበዝ ምን ይሻላል ሀገሬው አይቶ እንዳለየ ሠምቶ እንዳልሠማ ጆሮ ዳባ ልበስ አለ ወጣቱ ኢትዮዺያዊነቱ እስኪየጠራጥር ፈሪ ሆነ መንግስታችን አሳፋሪ ተግባራቶቹ በዙ እንዳውም ቅርብ ቀን ፓርላማቸው ላይ ፍርድ ቤት ጥፋተኛ ያላላቸውን ኢቲቪ ጥፋተኛ ለምን አለ ለሚለው ጥያቄ "እንዳጠፋሽ አጥፍቻለው"ብሎ መለሠ ይገርማል ሀገር እናስተዳድራለን የሚሉ እናንተ ጥፋተኛ ስላላችሁን እኛም እንላለን አሉ ጉድ ነው ዘንድሮ....

yayit misker denbit yilu for African dictator China built big building on their head. then completely they become great Rock!

Metenfese menor kehone eyenorku new yaninm bewid lijochua fikare netsanet new 10 q pro m

Add new comment

Filtered HTML

  • Web page addresses and e-mail addresses turn into links automatically.
  • Allowed HTML tags: <a> <em> <strong> <cite> <blockquote> <code> <ul> <ol> <li> <dl> <dt> <dd>
  • Lines and paragraphs break automatically.

Plain text

  • No HTML tags allowed.
  • Web page addresses and e-mail addresses turn into links automatically.
  • Lines and paragraphs break automatically.