ዳግማዊት ጃፓን፣ ዳግማዊ ቴዎድሮስ (ክፍል ሁለት)
Submitted by Admin on Sun, 04/29/2012 - 08:04በእውቀቱ ስዩም
ዓለማየሁ ገላጋይ በቀደምለት፣ ስለስልጣኔ ባቀረበው ሐተታ ስለጃፓንና ስለ ኢትዮጵያ መመሣሠል እንዲሁም ስለዳግማዊ ቴዎድሮስ የስልጣኔ አርአያነት ተናግሮ አናግሮኝ ነበር። የዛሬ ሁለት ሰንበት እኔ ባቀረብሁት ሂስ ላይ መልስ ይዞ ቀረበ። በመልሱ ውስጥ ራሱን በሃገር ፍቅር የነደደ፣ እኔን ደግሞ የሃገር ፍቅር የጐደለኝ አስመስሎ በማቅረብ ከመርማሪዎች ያጣውን ድጋፍ ከአርበኞች ለመሰብሰብ ሞከረ።
ነገሩን በዝርዝርዝ እንየው።
ወይ መመሣሠል!
አንባቢ እንደሚያስታውሰው፣ ጥንታዊት ኢትዮጵያና ጥንታዊት ጃፓን ስለለውጥ ተመሣሣይ አመለካከት እንዳልነበራቸው ፅፌ ነበር። ኢትዮጵያዊያን ለውጥን የሚያስጠላ ህዋስ ይዘው ተወልደዋል ብዬ አላስብም። ይሁን እንጂ ለውጥን እንዲፈሩና እንዲጠራጠሩ ያደረጋቸው ክፉ ገጠመኝ ተፈራርቆባቸዋል ብዬ አምናለሁ።
በታሪካችን፣ ነባሩን ካዲሱ ጋር የሚያቻችል የርዕዮተ ዓለም ሽግግር እምብዛም አልታየም። ክርስትና በሚስፋፋበት ጊዜ መነኮሳቱ የአረሚያውያኑን ክብር፣ ርስት፣ አልፎ አልፎም ሕይወት ይነጥቁ ነበር። ቤተክርስትያኖችንም በጣዖት ቤተመቅደሶች ላይ ገንብተዋል። ኢማም አህመድ ወልደ አብራሂም እስልምናን ሊያስፋፋ የሞከረበት መንገድ ከደብረሊባኖስ አጠገብ መስጊድ በመገንባት ሳይሆን ደብረሊባኖስን በማቃጠል ካህናትን በመግደል ነው። አዲስ ሐሳብ አዲስ ጥፋት ተደርጐ እንዲፈራ ያደረገው ይህን የመሳሰለው ክፉ ገጠመኝ ነው። በጃፓን ታሪክ ግን ቡዲዝም በእንግድነት ሲመጣ ባላገሩን ሺንቶይዝምን አላባረረውም። ስለዚህ ሁለቱ ጥንታዊ ሕዝቦች ለውጥን በተመሣሣይ አይን አያዩትም ነበር ማለት ይቻላል።
አለማየሁ ተቃወመ። በ1614 (1638?) ጃፓኖች ክርስትያኖችን በአዋጅ ማሣደዳቸውን ቤተክርስቲያንንም ማገዳቸውን ለውጥን የመጥላት መገለጫ አድርጐ በመተርጐም ‹‹…ይሄን ይሄን ስንመለከት ጃፓን እንዲያውም ከዓለም ህዝቦች ሁሉ በተለየ ለውጥን ባዋጅ ያገደች ድንበሯን የጠረቀመች ብቸኛ አገር ነች›› ብሎ ፃፈ።
ዓለማየሁ ጃፓኖች ክርስትናን በ1614 ማገዳቸውን የጠቀሰው ልክ ነው። ይሁን እንጂ ክርስትና ከዚህ በፊት ለመቶ አመት ያላነሰ ጊዜ በጃፓን በነፃነት ይንሸራሸር እንደነበር የሚያውቅ አልመሰለኝም። ከበደ ሚካኤል በጃፓን እንዴት ሰለጠነች እንደገለፁት ‹‹…ጃፓኖች ለመጀመሪያ ጊዜ (በ1549) የፖርቹጋል ተወላጆች የሆኑ ካህናት ወደ አገራቸው በገቡ ጊዜ የክርስትያን ሃይማኖት በደግ አይን ተመልክተው እንዲያስተምሩ ፈቅደው አበረታቷቸው›› ። አለማየሁ ግን ክርስትና ገና የጃፓንን በር ሲያንኳኳ በካልቾ ተብሎ የተባረረ ይመሥል ቀዳሚ ታሪኩን ገድፎ ፅፏል።
ጃፓኖች መቶ አመታት የታገሡትን ሃይማኖት ሊያግዱ የተነሡበት ምክንያት የስፔን ቄሶች በተኩላ ገላቸው ላይ የበግ ሹራብ ደርበው ለቅኝ ግዛት ሲያደቡ ስለደረሱባቸው ነው። ይህም ራስን መከላከል እንጂ ለውጥን የመጥላት እርምጃ ተደርጐ አይቆጠርም።
ሌላው ቢቀር፣ ጃፓኖች ህልውናቸውን የወጠኑት በቻይኖች የተውሶ ፊደልና ባህል በመሆኑ አዲስ ሀሳብ ተቀባይነታቸውን ያጎላዋል፡፡
‹‹በበዕውቀቱ ስዩም ፅሁፍ ውስጥ›› ይላል ዓለማየሁ። ‹‹ራስን አሳንሶ የመመልከት አባዜ ጐልቶ ይስተዋላል። ለምሳሌ ዶክተር ዕጓለ ገብረዮሐንስ ያቀረቡት ምርምር ያለ ሂስ መቀበል ጉዳት እንዳለው ጠቅሶ የበርትራንድ ረስልን ዘበታዊ ንግግር አገላብጦ ሳይመረመር ይውጣል››
ዓለማየሁ ከነፃ አመለካከት የክርክር ሜዳ ወጥቶ ወደ አርበኝነት ጐሬ ስልታዊ ማፈግፈግ አደረገ። ዕጓለ ገብረዮሐንስና እንግሊዛዊው ፈላስፋ ረስል ባንድ ሐሳብ ላይ ተከራክረው እኔ ለፈረንጁ ያደላሁ ይመስል በራስ ማሣነስ ሊከሰኝ ሞከረ። እኔ ከበርትራንድ ረስል የጠቀስኩት ጃፓኖች ቡዲዝምን ከመቀበላቸው በፊት መጥቀም አለመጥቀሙን ፈተሹት የሚለውን ንባብ ነው። ይህም የረስል የግል አስተያየት ሳይሆን ታሪካዊ ሐቅ ነው። ዓለማየሁ ታሪካዊ ሐቁን ‹‹ዘበታዊ ንግግር›› ብሎ
የሚያናንቅበት መሠረት የለውም።
ዓለማየሁ ስለፈረንጅ ታሪክ የፈረንጅ ምንጭ መጥቀሴን ራስን ማሳነስ አድርጐ በተረጐመበት መጣጥፍ ውስጥ እሱ ራሱ ‹‹ጣይቱ ብጡል›› ስለተባለው የመኮንን እንዳልካቸው ያማርኛ ተውኔት የ‹‹ባዕዱ›› ሞልቬየርን አስተያየት ተውሷል። ራስን ማሳነስ ማለት እንዲህ ያለ ሳይቸግር ጤፍ ብድር ነው።
ስለዳግማዊ ቴዎድሮስ
ስለዳግማዊ ቴዎድሮስ ለመናገር ትንሽ ፖለቲካዊ መናፍቅነት አስፈላጊ ነው። በበኩሌ ዓለማየሁ ንጉሡን የሞራል ስልጣኔ አርአያ ባያደርጋቸው ኖሮ እኔም ወደ ክርክሩ አልገባም ነበር። ንጉሡ፣ በዘመናቸው ከነበሩ ወደረኞቻቸው ጋር ሲነፃፀሩ በሞራል ኋላቀር ነበሩ ብዬ ነበር። እግርና እጅ በመቁረጥ መቅጣትን በይፋ የተቃወሙትንና
ራሳቸውን ንጉሠ ዘብሔረ ኢትዮጵያ ብለው የሚጠሩትን ንጉሤ ወልደሚካኤልን ጠቅሻለሁ። በነበረው ላይ ለመጨመር፣ የራስ አሊን ሆደ ሰፊነት መጥቀስ ይቻላል። የሰሜኑ ራስ ውቤ በራስ አሊ ላይ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ አድርገው ነበር። መፈንቅለ መንግስቱ ሲከሽፍ ራስ ውቤ በራስ አሊ እጅ ወደቁ። አሸናፊው ለተሸናፊው ምሕረት አድርገው ወደ ጥንቱ ማዕረጋቸው መለሷቸው።
ባገራችን ከደጐች ይልቅ ጀግኖች ይከበራሉ። ወትሮ በጠላት ተከብበን የምንኖር ሕዝብ በመሆናችን ጀግንነት ለሚባለው ነገር ዋጋ መስጠታችን ተገቢ ነው። ይሁን እንጂ በብዙ የታሪክ አጋጣሚዎች እንደታየው የውጭ ጠላትን አባርረን ስንመለስ እርስ በርሳችን ተከባብረን መኖር ያቅተናል። ለምን? ለአብሮ መኖር መሠረት የሆኑትን እነ መሐሪነትን፣ እነ ደግነትን፣ እነ ታጋሽነትን፣ መበልፀግ የሚገባቸውን ያህል አላበለፀግናቸውም። ወይም ለመሐሪዎቹ፣ ለደጐቹ፣ ለታጋሾቹ ተገቢውን ክብር
የሰጠን አይመስለኝም።
ዓለማየሁ ቀጠል አደረገና ‹‹አፄ ቴዎድሮስ ያከናወኗቸው የጭካኔ ተግባራት በዕውቀቱ እንዳደረገው በሌጣው የሚታዩ አይደሉም። ከህዝቡ፣ ከከባቢ ሁኔታው ጋር ተገናዛቢ እንጂ›› በማለት የማያዋጣ ክርክር አመጣ። ይሄ ምን ማለት ነው? በቴዎድሮስ ዘመን የኖረው ሕዝብ በንጉሱ የደረሰበት ግፍ ተገቢ አለመሆኑን ያውቅ እንደነበር የምንገነዘበው
‹‹…አንድ እግር በርበሬ መንቀል አቅቷችሁ አንድዶ ለብልቦ አቃጥሎ ይፍጃችሁ›› የሚለው የምንትዋብ ግጥም ስንሰማ ነው። ዓለማየሁ ገላጋይ ነበልባሉ ከማይደርስበት ዘመን ላይ ተወልዶ የጭካኔውን ተገቢነት ሊያፀድቅ ይሞክራል። ያልተመለሰው ጥያቄ፡- የርህራሄን ትርጉም የሚያውቁ ሰዎችን ማግኘት በማይቸግርበት በዚያን ዘመን ዳግማዊ ቴዎድሮስ በርበሬ (Barbarian) የሚል ቅጽል ያስለጠፈባቸው ጭካኔ ውስጥ ለምን ገቡ የሚል ነው። ዓለማየሁ የመጨረሻ ሙከራ ለማድረግ የሚከተለውን የመርዕድ ወልደ አረጋይን ጥቅስ የሙጥኝ አለ።
‹‹…ቴዎድሮስ ከልጅነታቸው ጀምሮ በሰዎች ተወዳጅነትን ወይም መጠላትን ካፈሩላቸው ጠባዮች መካከል ሐቀኝነታቸውና ታማኝነታቸው ነበሩ። በረጅሙ የኢትዮጵያ ታሪክ ሒደት ኢትዮጵያውያን እውነት በመናገራቸውና በቃላቸው ፅኑ በመሆናቸው በጐረቤትና በሩቅ ሕዝቦች ታውቀዋል። ካስራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ግን እነዚህ ጠባዮች ለብዙ ኢትዮጵያውያን እንግዶች እየሆኑ መጥተዋል። በግራኝ ወረራ አብዛኛው ሰው ጉልቱንና ሕይወቱን እንዳያጣ
ፈርቶ ንጉሱን ከድቷል። ሃይማኖቱን ክዷል። ከግራኝ ወረራ በኋላም ሰላምና የመንፈስ እረፍት የሚያሳጡ ሁኔታዎች በመፈራረቅ በመነሳታቸው የአድርባይነትና የምቀኝነት ጠባዮች እየጐሉ ሄዱ። በፊት ኢትዮጵያውያን በሐቀኝነታቸው የታወቁትን ያህል ከዚህ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በወላዋይነታቸውና
አጠራጣሪነታቸው ዝናን አተረፉ። ይህን የጠባይ ለውጥ ያስመጡ የፖለቲካ አለመረጋጋትና የኑሮ አስተማማኝ አለመሆን ሲሆን ቴዎድሮስ እነዚህን ገና ሳያሻሽሉ የአስተያየት ለውጥ ማምጣትን አስቀደሙ››
ዓለማየሁ ይህንን ጥቅስ የጠቀሰው የቴዎድሮስ ጭካኔ ከህዝቡና ካካባቢው ጋር ተገናዛቢ ነው ለሚለው ጭብጥ ማጠናከሪያ ይሆነኛል ብሎ ነው። ግን የመርዕድ ጥቅስና የዓለማየሁ ጭብጥ አራምባና ቆቦ ናቸው። የመርዕድ አንቀፅ ሲጨመቅ ከግራኝ በኋላ ኢትዮጵያውያን አጉል ባሕርያትን አዳብረዋል። ቴዎድሮስ ከህዝቡ ጋር ሲነፃፀሩ የባሕርይ ብልጫ አሳይተዋል። ቴዎድሮስ የስርዓት ለውጥ ለማምጣት ከመሞከራቸው በፊት የሕዝቡን ባሕርይ የማሻሻል ጥረት ማድረግ ነበረባቸው የሚል
ነው።
አጠቃላይ ሐሳቡ በንጉሱ አመራር ቅደም ተከተል መፋለስ ላይ የቀረበ ሂስ እንጂ ጭካኔያቸውን የሚያፀድቅ አይደለም። ዓለማየሁ ጭብጤን ይደግፍልኛል ብሎ ይህን መጥቀሱ ያስተዛዝባል። የመርዕድ ወልደአረጋይ ጥቅስ የዓለማየሁን ሐሳብ ባይደግፍም በራሱ ትክክልነቱ ያጠራጥራል። በመጀመሪያ የግራኝ ወረራን ተከትሎ የተከሰተ
የሕዝብ ባሕርይ ድቀት መኖሩን የምናረጋግጠው እንዴት ነው? በአጤ ቴዎድሮስ ዘመን የነበረው አድርባይነት ባጤ ዘርዓያዕቆብ ዘመን ከነበረው አድርባይነት እንደከፋ የምናውቀው በምን ሚዛን ነው?
አጤ ቴዎድሮስ ከገባሮቻቸው የተሻለ ባሕርይ እንደነበራቸው መጥቀስም ልክ አይመስልም። በደህናው ቀን የንጉሱ ጓደኛ፣ በጐደሎው ቀን እስረኛ የነበረው ዋልድማየር እንደገመገመው በጊዜው የነበረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ብሩህና ንቁ የሚባል ነበር። ትምህርት ሲያገኝ ፈጥኖ ተቀባይ፣ ሩህሩህ ሲሆን በግፍ ሲነዱት ግን የቂም መንፈስ
የሚያቆጠቁጥ አድርጐ ገልፆታል። ዋልድማየር ከኢትዮጵያውያን ብላቴኖች መካከል ጥቂቱን ሂሳብ ጂኦግራፊና ታሪክ ማስተማር ጀምሮ በፈጣን የትምህርት አቀባበላቸው ተደምሞ ነበር።
ስለዚህ ነጂው ከሕዝቡ ብልጫ እንዳለው ተደርጐ መገመቱ ልክ አይመስልም። አጤ ቴዎድሮስን የሞራል አርአያ ሊሆኑ እንደማይችሉ ለማሳዬት ጥቂት ገጠመኞችን ጠቃቅሼ ነበር። ዓለማየሁ በመጋፈጥ ፈንታ እውነትን እንደ ድመት አይነምድር ለማለባበስ ስለጣረ የሚከተለውን ሁነት እጨምራለሁ። ባጤ ቴዎድሮስ ዘመን የተከሰተውን ሁሉ እየተከታተለ ለወዳጁ ለእንጠንዮስ ደ አባዲ ሲዘግብ የነበረው የዋድለው አሰጋኸኝ የሚከተለውን ይመሠክራል።
‹‹…ቴዎድሮስ ንጉሥ ከደብረታቦር ወደ ጎንደር ገሰገሰ። ቅዳሜ ቀን ደረሰ። የጎንደርን ገበያ ዘረፈ። ከተማውንም ዘረፈ፣ አቃጠለ። ብዙ ጎበዞችም አቃጠለ። ሴቶችንም… የተቀበረ ወርቅ አሳዩኝ እያለ እጃቸውንና ጠጉራቸውን በእሳት አቃጠለ። ልብሳቸውንም የሴቶችንና የወንዶቹን ሁሉ ገፎ ዕራቁታቸውን አቆመ። በዚህ ቀን ታናሽ ጨርቅ ታናሽ ማቅ ያገኘ ብፁእ ነው።… ቴዎድሮስም ድውያኑንና አረጋውያኑን በበቅሎና ባህያ በፈረስ ጭኖ በቃሬዛም ይዞ ምፅራሕ አጠገብ ሰፈረ። የምፅራሕ ዕቃ ሁሉ ተዘረፈ። ሰውንም ሁሉ ወደ ቤት አግብቶ አቃጠለ። ሰውም በተቃጠለ ጊዜ እስከ ፍርቃ ሸተተ። ሕፃናትና ሴቶች ወደ ጣና ባሕር እየገቡ አለቁ። የጎንደርም ነጋዶች ብዙ ደብተሮች በምጽራሕ ተቃጠሉ።
…የሜጫ ሦስት መቶ ወታደር ካንድ አጥር ውስጥ አግብቶ ዘጋ። እህል ውሃ ነሳቸው። ከቦ ነፍጠኛ ጠበቃቸው። ሽንታቸውን ለመጠጣት አይነምድራቸውን ለመብላት ተጣሉ። እኩሉ ባስር ቀን፣ እኩሉ በሃያ እኩሉ በሰላሳ እኩሉ ባርባ ቀን ሞቱ። ከአርባ ቀን በኋላ አንድ ሰው ብቻ ቀረ። እግዜር በተአምራት አዳነው እንዳይባል ቴዎድሮስ በነፍጥ ገደለው። የፍርጣን ቤተክርስትያን ሁሉ እያፈረሰ ማገደው››
ዝርዝሩ ይቀጥላል። እኔ እዚህ ድረስ ይበቃኛል። አለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ ዳግማዊ ቴዎድሮስን ዳግማዊ ግራኝ ማለታቸው ትርጉም አለው። ሁለቱ ሰዎች የኪነ ጭካኔ ባለሙያዎች ነበሩ። ዓለማየሁ ይህንን ‹‹ከህዝቡና ከከባቢው ጋር እንዴት እንደሚያገናዝበው ለማየት ጓጉቻለሁ፡፡
ካወቅንበት ከቴዎድሮስ አወዳደቅ ጥሩ ትምህርት ማግኘት እንችላለን። በጉልቤ ሕዝብን ማስተዳደር አይቻልም። ፖለቲካ የማሽኮርመም ጥበብ ነው።
በመጨረሻ
ዓለማየሁ ገላጋይ የዘመነ መሣፍንት መሪዎች ከቴዎድሮስ ጋር የሚወዳደር የስልጣን ፍላጐት እንደነበራቸው መፃፌ ገርሞት ማብራሪያ ጠይቋል። ተገቢ ጥያቄ ነው። እድሜና ወረቀት ከበረከተልኝ በሚቀጥለው እመለሳለሁ።__
