Add new comment

አቦይ ስብሓት ነጋ የዘነጓቸው ነጥቦች

አስራት አብርሃም
ከመቀሌ
(አቶ አስራት አብርሃም የአረና ህዝብ ግንኙነት
ኃላፊ ሲሆን ከአገር በስተጀርባ እና መለስና ግብፅ
የሚል መጽሐፍ ለንባብ አብቅቷል)

አቦይ ስብሓት በነፃነት የሀሳብ ልዕልና ላይ ተመስርተው ለመከራከር ወደ ሚዲያ መምጣታቸው ምክንያታቸው ምንም ይሁን ምን ዋጋ እና ክብር ሊያሰጣቸው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ አቦይ ስብሓት ከሚታወቁበት መንገድ ለየት ብለው የብዕር ወንጭፍ ነው ይዘው የመጡት (አለበለዚያማ ጎልያድ በጎራዴው ዳዊት በወንጭፉ ነበር የሚሆነው..፡፡ እናም ..አሁን ደርሰው ለምን ብቅ አሉ..... ማለት ተገቢ ላይሆን ይችላል፡፡ በእኔ እምነት ዋናው ነጥብ መሆን ያለበት ወደ ሚዲያው ያመጡት ሀሳብ ወይም ፍሬ ነገር እውነትነት አለው ወይ? ትምህርት የሚሰጥ ነው ወይ? ያካበቱትን የህይወት ተሞክሮ ለማካፈል ነው ውይ? በረጅሙ የፖለቲካ ጉዞአቸው የፈፀሙአቸውን ስህተቶች እንደ ግለሰብም ይሁን እንደ ድርጅት የመፀፀት ነገር ይታይባቸዋል ወይ? የሚለው ነው፡፡
የአቦይ ስብሓት ፅሁፎች ከዚህ አንፃር ስገመግማቸው ሰውዬው ምንም አይነት የአስተሳሰብም ሆነ የአቋም ለውጥ ሳያደርጉ በፊት የሚታወቁበትን ነው ይዘው የመጡት፡፡ ይህ ደግሞ በየጊዜው የሚሰነዘሩባቸውን ትችቶችና ውንጀላዎች ለመከላከል ለማስተባበል የመጡ ያስመስልባቸዋል፡፡ ይህ የአቦይ ስብሓት መከላከል ደግሞ ልክ ፈረንጆቹ እንደሚሉት በመስተዋት ቤት ውስጥ ሆኖ ድንጋይ እንደሚወራወር ሰው ዓይነት ሆኖ ነው ያገኘሁት..
በመጀመሪያ ከአቦይ ስብሓት ጋር የምስማማባቸው ሀሳቦችን ላስቀድም፡፡ ታሪካችን የጥንቱን ብቻ ሳይሆን እስከአሁን ያለውን ጭምር በደንብ ከፖለቲካዊ ወገንተኝነት ነፃ በሆነ መልኩ መጠናት አለበት የሚለውን ሀሳብ እቀበላለሁ፡፡ ይህን ስል ግን ታሪክ ይሄ ይሻለናል ተብሎ በሪፈረንደም መወሰን እንደማይቻል በመሆኑ፤ ታሪክም የሚጠናው አንድም በፊት የነበሩትን ጥሩ ጎኖች ለማስቀጠል፣ አንድም ደግሞ የተፈፀሙትን ስህተቶች ላለመድገም ሲባል መሆኑን እረዳለሁ፡፡ ታሪካችን ህፀፅ የሚበዛበት፣ ከፖለቲካዊ ፕሮፓጋንዳ፣ ከውዳሴ ነገስታትና ከርግማን ያልፀዳ፣ ታሪክ ለመባል ብዙ የሚቀረው ሆኖ ነው የሚሰማኝ፡፡ ስለዚህ እኔም አቦይ ስብሓትም ሌሎች ከሚሉትም በተለየ መልኩ መጠናት አለበት ነው የምለው፡፡
ሌላው ፕ/ር መስፍን ወልደማርያምም ሆኑ አቦይ ስብሓት ነጋ፣ ወዳጄ ተመስገን ደሳለኝንም ጨምሮ የተስማሙበት ነጥብ በስርዓት፣ በመከባበርና በሰለጠነ መንገድ የሀሳብ ክርክር ማድረጉ ተገቢነት ላይ እኔም የምስማማበት ነው፡፡ በተለይ እኛ ወጣቶቹ አቋማችን ምንም ይሁን ምን ታላላቆቻችንን በሀሳብ ልንሞግታቸው ስንነሳ ተገቢውን ክብር መንፈግ የለብንም፡፡
አሁን ካለሁበት ፖለቲካዊ አሰላለፍ አንፃርም እንደዜጋም ከአቦይ ስብሓት ጋር የማልስማማቸው ሀሳቦች አሉ፡፡ ከአቦይ ጋር የማልስማማባቸው ጉዳዮች በጣም ብዙ ቢሆኑም፤ በዚሁ ጋዜጣ ባነሷቸው ነጥቦች ላይ ብቻ አተኩሬ ሀሳቤን እሰጣለሁ፡፡

1.ደርግ ..ኤርትራ መሬትዋ እና ባህሯ እንጂ ህዝቡ አያስፈልገንም.. ያለው መቼ ነው? በሬዲዮ ነው ያለው? በቴሌቪዥን ነው ያለው? በስብሰባ ላይ ነው ያለው? ማን የሚባል ሰውስ ነው እንዲህ ያለ ንግግር ደርግን ወክሎ የተናገረው? ደርግ አምባገነንና ጨፍጫፊ የነበረ ቢሆንም ከሌላው ህዝብ በተለየ ሁኔታ የኤርትራን ህዝብ በድሏል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ሐውዜን እንኳ ትግራይ ውስጥ ነው ያለው..
2.አቦይ ስብሓት ..ኢህአዴግ በረሀ ላይ እያለ በደርግ ዘመነ መንግስት ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጠቅልላ ወጣች.. ብለዋል፤ ለምንድነው የወጣችው? ኢህአዴግ ወደ መሀል አገር እየገፋ ስለነበር ነው.. አቦይ ስብሓት ደርግ በኤርትራ የተሸነፈው ህወሓት ሌላ የውጊያ ግንባር በመክፈቱ ከዚያም በላይ ሻዕቢያ አበቃለት ሲባል የህወሓት ሰራዊት ደርሶ ስላዳነው መሆኑ የሚረሱት አይመስለኝም፡፡ ደግሞ የደርግ ጦርና አስተዳደር ከኤርትራ ቢወጣስ?.. ደርግ ከትግራይም ጠቅልሎ ወጥቶ አልነበር.. ከኦሮሚያስ ጠቅሎ ወጥቶ አልነበር.. ይህ ለኤርትራ መገንጠል በራሱ ምክንያት ሊሆን አይችልም፡፡ ኤርትራ ኢህአዴግ አዲስ አበባ ከመግባቱ በፊት ነው ነፃ የወጣችው የሚለው ክርክር የማያስኬድ የሚሆነው ለዚህ ነው፡፡ ምክንያቱም፡-
አንደኛ ሻዕቢያ ኤርትራን ተቆጣጠረ ማለት ኤርትራ ነፃ አገር ሆነች ማለት አይደለም፡፡ ከኤርትራ ጋር ተመሳሳይ ታሪክ ያላቸው ሁለቱ የሶማሊያ አካል የነበሩት ሶማሌላንድ እና ፑንት ላንድ በወታደራዊ ሃይል ራሳቸውን ነፃ ማድረግ ቢችሉም እንደ አገር እውቅና የሰጣቸው አካል የለም፡፡ አንድ ቀን ሶማሊያ ጠንካራ ማዕከላዊ መንግስት ሲኖራት በውዴታም ይሁን በግዴታ መልሳ ልትጠቀልላቸው እንደምትችል ምንም ጥርጥር የለውም፡፡
ሁለተኛ የኢህአዴግ የሽግግር መንግስት ያውም በሌለው ስልጣን ኤርትራ ትገንጠልልኝ ብሎ ለተባበሩት መንግስታት በደብዳቤ በመጠየቁና ይህንን ተከትሎ ኤርትራ ሪፈረንደም እንድታካሄድ በመደረጉ ነው፡፡
እርስዎ እንደሚሉት ከሆነማ ኤርትራ ሪፈረንደም ማካሄድም አያስፈልጋትም ነበር ማለት ነው፡፡ አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ግን በአንድ ወቅት ከአሰር መጽሔት ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ላይ ለኤርትራ ነፃነት ሪፈረንደሙ ወሳኝ እንደነበር ነው የገለፁት፡፡ እንዲያውም በሪፈረንደሙ ያልተሳተፉ ኤርትራውያን ..ኤርትራዊ ነን ብለው እንዴት ሊናገሩ ይችላሉ.. በማለት ነው በወቅቱ ያልተሳተፉትን ሁሉ የነቀፉት፡፡
3.አቦይ ስብሓት ..ኢህአዴግ አገር ተቆጣጥሮ ሌሎች ለመገንጠል ሲዋጉ የነበሩ የብሄር ድርጅቶችንም አሰባስቦ የሽግግር ዘመን ቻርተር ሲነድፉ፤ ያው ኤርትራ በሻዕቢያ ስር ነበረች ፡፡ ሻዕቢያ ይቅርና አብዛኞቹ ሌሎች ድርጅቶችም የቻርተሩ አባል ለመሆን ፈቃደኝነት አልነበራቸውም፡፡.. ብሏል፡፡ እዚህ ላይ መመለስ ያለበት ጥያቄ አለ.. ሻዕቢያ በሽግግር መንግስቱ ውስጥ እንዲገባ መቼ ነው የተጠየቀው? እኔ በተቻለኝ አቅም ሁሉ ጥናት አድርጌያለሁ እንደዚያ የሚል ነገር አላገኘሁም፡፡ እርስዎ አስመራ በሻዕቢያ እንደተያዘች ወዲያው ከደሴ ተመልሰው ወደ እዚያው ሄደው እንደነበር ይነገራል፡፡ ያን ጊዜ በግልዎ ለሻዕቢያ ይህን ነገር አንስተው ጠይቀው ከሆነም ይንገሩን፡፡በሌላ በኩል ደግሞ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፣ አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ በሽግግር መንግስቱ ቻርተር ማርቀቁ ሂደት ላይ መሳተፋቸውን የሚጠቁም መረጃ እንዳላቸው ገልፀዋል፡፡ ይህ ደግሞ ሻዕቢያ በሽግግር መንግስቱ ውስጥ ለመሳተፉ ፍላጐት እንደነበረው ሊያመላክት ይችላል፡፡
ሌላው ..ሻዕቢያ እምቢ ሲል ምን ይደረግ? የህዝቦችን የራስ እድል በራስ የመወሰን ፅኑ ፖለቲካዊ እምነት (አሁንም በህገ መንግስት ያለ) ስላለን እድሉን ራሱ እንዲወስን ተደረገ፡፡ ምን አማራጭ ነበር?.. የሚል ነገርም ተናግረዋል፡፡ እስኪ እዚህ ላይ ጥያቄ ልጠይቅ ሻዕቢያ እምቢ ነው ያለው ወይስ የራሱን እድል በራሱ እንዲወስን ነው የተደረገው?.. ለእኔ ምንም ግልፅ አልሆነልኝም.. ሁለት እርስ በእርስ የሚጋጩ ሀሳብ የተናገሩ መሰለኝ (መሰለኝ ነው ያልኩት፤ እኔ ተሳስቼ ከሆነም የግንዛቤ እጥረት ሊሆን ይችላልና ከይቅርታ ጋር ነው የምጠይቀው) በአንድ በኩል ..ከእኛ ጋር ሁን ብለነው እምቢ አለን.. የሚል አንድምታ ያለው ሀሳብ አቅርበዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ..የህዝቦችን የራስ እድል በራስ የመወሰን ፅኑ ፖለቲካዊ እምነት ስላለን እድሉን ራሱ እንዲወስን አደረግን.. ይላሉ.. የትኛውን እንውሰድ?.. እውነትም ሻዕቢያ ተጠይቆ እምቢ ያለበት አጋጣሚ ካለ በማስረጃ አስደግፈው ሊነግሩን ይገባል፡፡ እርስዎ እንዳሉት እምቢ ብሎ ከሆነ እንኳ ..እምቢ ካለ ምን ይደረግ?.. ተብሎ ብቻ የሚተው ነገር መሆን አልነበረበትም፡፡ ኢህአዴግ የኢትዮጵያን ህዝብ ወክሎ መንግስት እንደመሆኑ መጠን በወቅቱ ማድረግ የሚችለው ነገር ነበር፡፡
የመጀመሪያው እርምጃ ለኤርትራ ነፃነት እውቅና አለመስጠት ነው፡፡ ኢትዮጵያ እውቅና ካልሰጠቻት ደግሞ ሻዕቢያ ሺህ አመትም ኤርትራን ቢገዛ ሉአላዊት አገር የመሆን እድል በምንም መንገድ ልታገኝ አትችልም ነበር፡፡ ሌላው አማራጭ ደግሞ ለኤርትራ መገንጠልና ራሷን የቻለች ነፃ አገር መሆን እውቅና ከመስጠት በፊት መደራደር በሚያስፈልጉ ጉዳዮች ላይ መደራደር ነበር የሚያስፈልገው፡፡ ስለድንበር ጉዳይ፣ ስለባህር በር ጉዳይ፣ በኤርትራ ስለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጉዳይ፣ በኢትዮጵያ ስለሚኖሩ ኤርትራውያን ጉዳይ፣ በሁለቱ አገሮች መካከል ስለሚኖረው የኢኮኖሚ ግንኙነት ጉዳይ መደራደር ይቻል ነበር፡፡ እኔ ህወሓት፤ ሻዕቢያ በሽግግር መንግስቱ ማዕቀፍ ውስጥ እንዲገባ ይፈልግ ነበር የሚል እምነት ፈፅሞ የለኝም፡፡ ምክንያቱም ..የኤርትራ ህዝብ በፌዴሬሽን መልክ ሆኖ ኢትዮጵያዊነቱን ነው የሚሻለው.. ብሎ መጽሐፍ የፃፈው ተስፋፅዮን መድሀኔ የተባለውን ኤርትራዊ ምሁር ይህን አቋሙን ነቅፋችሁ መጽሐፍ ሁሉ ጽፋችኋል፡፡ በወቅቱ ህወሓት ስለኤርትራ የነበረው ትንታኔ ..የቅኝ ግዛት ጥያቄ ነው.. የሚል ነው፡፡
አንድ የረሳሁትን ነጥብ ልጨምር ..የህዝቦችን የራስ እድል በራስ የመወሰን ፅኑ ፖለቲካዊ እምነት ስላለን እድሉን ራሱ እንዲወስን አደረግን.. የሚል ነገር ተናግረዋል፡፡ ይህ እውነት ነው ብለን ብንወስደው እንኳ ይህ እድል መሰጠት የነበረበት ለኤርትራ ህዝብ እንጂ እርስዎ እንዳሉት ለሻዕቢያ መሆን አልነበረበትም፡፡ በእርግጥ ከዚህ በፊት የኤርትራ ህዝብ የሚባለው የቱ ነው የሚለው ጥያቄ መልስ የሚያስፈልገው መሰረታዊ ጉዳይ ነበር፡፡ ምክንያቱም በወቅቱ የቀይ ባህር አፋሮች ያለውዴታቸው በኢህአዴግ መልካም ፍቃድ በሻዕቢያ ታፍነው ኤርትራዊ እንዲሆኑ ተደርጓልና ነው፡፡ ይህን ተቃውመው መታገል ሲጀምሩ ደግሞ አቶ መለስና አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ደብዳቤ እየተፃፃፉ ስልክ እየተደዋወሉ በሁለት አቅጣጫ ጦርነት ይከፍቱባቸው እንደነበር የሚታወቅ ነው፡፡ ስለዚህ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት ከልብ ኢህአዴግ የሚያምንበት ቢሆን ኖሮና ፍላጎት ቢኖረው የኩናማ፣ የኢሮብና የአፋር ህዝቦች ከደረሰባቸው መከፋፈል ማዳን ይቻል ነበር፡፡ አንድ ሌላ ጥያቄ ልጨምር የራስን እድል በራስ የመወሰን ለምን በወቅቱ ለኦነግስ አልተሰጠውም?.. ይህን የምለው ፅኑ ፖለቲካዊ እምነታችን ነው ስላሉ ነው፡፡ ኦነግ ደግሞ ለመገንጠል ፅኑ ፍላጎት ነበረው፡፡
አቦይ ስብሓት በአንድ ወቅት የተናገሩትን በተድበሰበሰ መልኩ ሲደግሙት ..በኔ አመለካከት የማንኛውም የጎረቤት አገር ሲወረር ዝም ብሎ ማየት የለብንም፡፡ የኢትዮጵያ ጥቅምም ነው የሚጎዳው፡፡ ስለዚህ ተወራሪው መንግስት ከፈቀደ ይፈቅዳል፤ ኢህአዴግ የሚመራው መንግስት ባለው አቅም ጎረቤት አገርን ከውጭ ወራሪ ለማዳን ማገዝ አለበት፡፡ ከሁሉም ጎረቤት በላይ የኤርትራን ህዝብና ነፃነትን ከሌላው የውጭ ወራሪ ማዳን አለበት፡፡.. በማለት ነው ያስቀመጡት፡፡ ለምሳሌ ሱዳን ወይም የመን ኤርትራን ብትወራት ኢህአዴግ የሚመራው የኢትዮጵያ መንግስት ሻዕቢያን አስፈቅዶ ከሻዕቢያ ጎን ሆኖ ይዋጋል ማለት ነው፡፡ በዚሁ ሁኔታ የትኛውን የኢትዮጵያ ጥቅም ነው የሚያስከብረው?..
..ለባህር በር ብለን አንዋጋም.. ባላችሁበት አፋችሁ ተመልሳችሁ ደግሞ ..ኤርትራን ከውጭ ወራሪዎች ለመከላከል እንኳን ገንዘብ ህይወትም መቆጠብ የለብንም፡፡ ይህ የሀቀኞች ኢትዮጵያውያን አመለካከት ነው መሆን ያለበት፡፡.. የሚሉት እንዴት ነው.. ባለፈው ጊዜ ክቡር ጠ/ሚኒስትራችን ..ከሁሉም በላይ የኤርትራ ህዝብ ሰላም ያስፈልገዋል.. ብለውን ነበር፡፡ አሁን ደግሞ እርስዎ ..ከሁሉም ጎረቤት በላይ የኤርትራን ነፃነት መጠበቅ አለብን.. እያሉን ነው.. እዚያ ኤርትራ ውስጥ ያስቀመጥነው ወይም የቀበርነው ነገር አለ እንዴ?.. ኤርትራዊያን እኮ አንዴ ካዋጣ ያዋጣን ብለው ነፃነታቸውን አውጀዋል፡፡ ከዚያ በኋላ ስለሚኖረው ነገር ራሳቸው ናቸው ሀላፊነት መውሰድ ያለባቸው፡፡ እንደ እኔ እምነት የሀቀኛ ኢትዮጵያዊ ሀላፊነት የራሳቸውን ዳር ድንበርና የአገራቸውን ልኡላዊነት ማስጠበቅ እንጂ ለኤርትራዊያን ነፃነት ዘብ መቆም አይመስለኝም፡፡ ባህራችንና ግዛታችን በነፃ መስጠታችን አንሶ ደግሞ ለኤርትራ ህልውናና ነፃነት ዘብ እንቁም እንዴ..
አቦይ ስብሓት ስለህገ መንግስቱ ሲናገሩ ..አገራችን ተበታትና የዓለም መሳቂያ ከመሆን ያዳነ ህገ መንግስት ነው.. ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከመበታተን የዳነችው ከህገ መንግስቱ በላይ የሆኑ ሌሎች ምክንያቶች ሊኖሩ አይችሉም? በባህል፣ በሀይማኖት፣ በታሪክ፣ በስነልቦና በመሳሰሉት ለዘመናት የቆየው ትስስር በአንድነት ለመቀጠል የሚኖረው አስተዋፅኦን እንዴት ነው የሚያዩት?.. ለምሳሌ የትግራይ ህዝብ ያልተገነጠለው በህገ መንግስቱ ምክንያት ነው አይደለም፡፡ እርስዎም ያስቀመጡት ሃቅ አለ፡፡ ህወሓት ስለመገንጠልና ስለትግራይ ሪፖብሊክ መመስረት ድምፁን ከፍ አድርጎ በሚሰብክበት ወቅት ህዝቡ ምን ይል እንደነበር ራስዎ የጠቀሱትን እዚህ መልሼ ልድገመው ..ተገንጥለን ምን ልንባል ነው? የትግራይ መንግስት? እንደሌሎቹ የሸዋ ንጉስ፣ የጐጃም ንጉስ.. በሚል አስተሳሰብ በትግራይ ህዝብ ስለተወጠርን ..ካቃተን መገንጠል.. የሚል በህዝቡ በጣም ስለሚጠላ ብዙ አይነሳም፡፡ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ነው የሚታየው ኢትዮጵያዊነት፡፡ አገር ውስጥም ውጭም ያለው የትግራይ ሰው ሊሰማው የማይፈልገውን የመገንጠል ፕሮግራም ይዘን አልታገልንም፡፡.. አቦይ ስብሓት እዚህ ላይ እውነት ብለዋል፡፡ ህወሓት የመገንጠል አጀንዳውን የሰረዘው በህዝቡ በነበረው ከፍተኛ ግፊት ምክንያት ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የሚጠቀሱ ሌሎች ምክንያቶቹም አሉ፡፡
አቦይ ስብሓት የህወሓት አቋም የለሽነት ከሁኔታዎች እየተማረ የሚሄድ ድርጅት ስለሆነ ነው የሚል ምክንያት ይሰጡታል፡፡ የትግል ስልትና ስትራቴጂ እንደሁኔታው በአጭር ጊዜ ውስጥ መቀየር ይቻል ይሆናል፤ ተገቢ ነውም ዓላማ ግን እንደከተማ ልብስ በየዕለቱ የምትቀየረው ነገር አይደለም፡፡ ህወሓት ከትግል ዓላማ አንፃር ከየት ወዴት ይዘል እንደነበር የሚረሱት አይመስለኝም፡፡ ይህ ባህሪው ነው አንዳንዶቹ ዞሮ ዞሮ ዓላማው የነበረው ስልጣን መያዝ ነው ያን ግቡን ደግሞ መቷል የሚሉት፡፡
የሌሎች ድርጅቶች በትግሉ ሂደት መክሰምና የህወሓት አሸናፊ ሆኖ መውጣት ብቻውን ህወሓት ትክክለኛ ዓላማ ስለነበረው ነው አያሰኘውም፡፡ ደርግ ወደ ስልጣን የመጣው ትክክለኛ ዓላማ ይዞ ስለተነሳ አልነበረም፡፡ የሌሎች ድርጅቶች በትግሉ ሂደት መክሰም አንዱ ምክንያት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ የመጠላለፍና የመጠፋፋት መድረክ ስለነበርና ስለሆነ ብዙዎቹ መጥለፍም ማጥፋትም ሳይችሉበት ቀርተውና ተቀድመው ጠፍተዋል፡፡
ፕ/ር መስፍን ..የመሃይምነት ድፍረት.. የሚሏት ነገር አለቻቸው.. በእውቀትና በአስተሳሰብ ሻል ያሉት የተሻለ አማራጭ ሲያስቡና ሲፈልጉ ተራና ምንም የነበሩት ደግሞ ወደፊትና ወደኋላ ምንም ሳያዩ ደርሰው ያጠፏቸው ስለነበር ነው፡፡ ፖለቲካችን ውርደት፣ አድርባይነት፣ ቆሻሻነትና ሆዳምነት የሚበዛበት በመሆኑ ለአገራቸው አሳቢ የሆኑ ቅን ፖለቲከኞች ወደፊት የሚመጡበትና የሚሰሙበት እድል አላገኙም፡፡ ምናልባት እርስዎ ዕድለኛ ሆነው፤ ብዙዎቹ ሲሸኙ ከሸኚ ወገን ሆነው በመዝለቅዎ ክፉ መከራ አ ላገኘዎትም፡፡ በዚህም ምክንያት የፖለቲካችንን ሌላኛው አስቀያሚ ገፅታ አላዩትም እንጂ ስንቶቹ ባላሰቡትና ባልጠረጠሩት ሁኔታ ውሃ በልቷቸው ቀርተዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ነው ..አሸናፊ ሆነን የወጣነው ትክክለኛ ዓላማ ስለነበረን ነው.. የሚለው ሀሳብ በካድሬ ስብሰባ ላይ ካልሆነ በስተቀር በሌላ ቦታ ላይ ውሃ የሚያነሳ የማይመስለኝ..
ከሁሉም በላይ በህወሓት አመራር ዘንድ መርህ አልቦ መተጣጠፍና መገለባበጥ እንደነበር መካድ የለበትም፡፡ የደርግ ርዕዮተ ዓለማዊ አሰላለፍና አካሄድ በራሱ ለህወሓት አሸናፊነት ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ..አዲስ አበባን ግቡና ተቆጣጠሩ.. የሚል ፍቃድ ራሱ ከዋሽንግተን መገኘቱ በራሱ የሚያመላክተው ነገር ይኖራል፡፡ በወቅቱ አቶ መለስ በደስታ ብዛት እንባ የተናነቃቸው ይህን የአሜሪካ ቡራኬ ሲሰሙ ነው፡፡
ስለዚሁ ርዕስ ጉዳይ ብዙ ማለት እንደሚቻል አውቃለሁ፡፡ ነገር ግን ..ከአገር በስተጀርባ.. በሚለው መጽሐፌ ላይ በስፋትና በጥልቀት የዘረዘርኩት ስለሆነ አንባቢን ማሰልቸት ይሆንብኛል፡፡ አቦይ ስብሓት ይህን መጽሐፍ ያላገኙት ከሆነ ለእርስዎ አንድ መጽሐፍ በስጦታ በፍትሕ ጋዜጣ ቢሮ አስቀምጬ ሎታለሁና ማንበብ ይችላሉ፡፡
እንግዲህ ፅሁፌን እዚህ ላይ ላብቃ፡፡ መፈክር ስለማልወድ (የኮምኒስት ስለሚመስለኝም) ይህቺ አቦይ ስብሓትም፣ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝም የሚደጋግሟትን መፈክር ከማለት ራሴን ቆጥቤያለሁ፡፡ የሀሳብ ፍጭቱ ለዘላለም ባይሆንም እስከተመቸን እንቀጥልበት፡፡

Filtered HTML

  • Web page addresses and e-mail addresses turn into links automatically.
  • Allowed HTML tags: <a> <em> <strong> <cite> <blockquote> <code> <ul> <ol> <li> <dl> <dt> <dd>
  • Lines and paragraphs break automatically.

Plain text

  • No HTML tags allowed.
  • Web page addresses and e-mail addresses turn into links automatically.
  • Lines and paragraphs break automatically.