ፍትህ በጫና እና በማስፈራሪያ የሚዝሉ ክንዶች፤የሚሰደዱ እግሮች የሏትም!
Submitted by Admin on Sun, 12/25/2011 - 17:47አሁን አደገኛ ሁኔታ ላይ ተደርሷል፡፡ ፍትህን ወደ መቃብር ለመክተት በተቀናጀ እና በተደራጀ መልኩ የሚሴረው ሴራ እና የሚሸረበው ተንኮል ስጋና ደም ለብሶ እነሆ ከበር ቆሟል፡፡ ከዕሮብ (11/04/04) ጀምሮ በጋዜጣው ዋና አዘጋጅ ተመስገን ደሳለኝ፤እንዲሁም በአዘጋጆቹ ሙሉነህ አያሌው እና ኃይለመስቀል በሸዋምየለህ ላይ መፈናፈኛ የሚያሳጣ ክትትል እየተደረገ ሲሆን፣ ይሄ ርዕሰ አንቀጽ እየተዘጋጀም (13/04/04) የጋዜጣው ቢሮ በክትትል ቀለበት ውስጥ እንደሆነ ነው፡፡
በዚህም የተነሳ የመስራት ነፃነትን ብቻ ሳይሆን የመተንፈስ ነፃነትንም በሚያፍን መልክ በአዘጋጆቹ ላይ እየተደረገ ያለው ጫና ፍፁም ህገወጥ እንደሆነ ለማስገንዘብ እንፈልጋለን፡፡እናም እነዚህ የደህንነት ሰራተኞች በጠራራ ፀሐይ የዜጐችን የመዘዋወር እና በነፃ የማሰብ ህገ መንግስታዊ መብት እንዲያፍኑ የላካቸው አካል ህገ-መንግስቱን እየናደው እንደሆነ ህዝብ ሊያውቀው ይገባል፡፡ እነዚህ ሰዎች የጋዜጠኛ ኃይለመስቀልን ሲም ካርድ በነጠቁበት ጊዜ የደህንነት ሰራተኞች እንደሆኑ ቃል በቃል ከነገሩት በኋላ ከባድ ማስፈራሪያ ከተከበረው የጋዜጣው ቢሮ በር ላይ አድርሰውበታል፡፡
በፍትሕ እምነት ይሄ ሀገር የእናነት /የገዥዎቻችን/ እንደሆነ ሁሉ፤ የእኛም ነው፡፡ በእንደዚህ አይነቱ የደህንነት ጫና እና ማስፈራሪያ የምንለውጠው አቋምም ሆነ የምንሰደድበት ሀገር የለም፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ ነችና፡፡ ደግመን ደጋግመን እንደምንለው፤ ዛሬም እንላለን በወከባ እና በማስፈራሪያ በሀገሪቱ ቁጥር አንድ ተነባቢ የሆነችው ፍትህ ጋዜጣ የሚያጎነብስ አንገት እንዲኖራት አንፈቅድም፡፡ ለስደት የተዘጋጀ ልብ የላታም፡፡ ምንጊዜም የህዝብ ድምጽ፣ የህዝብ አንደበት እንደሆነች ትቀጥላለች፡፡ ከዚህ በተረፈ አፋኙን የፕሬስ ህግ ጨምሮ የተለያዩ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ ስላለ፣ ጥፋት ካለ በህግ መጠየቅ እንጂ፤ ለሀገር ደህንነት እና የህዝባችንን (እኛን ጨምሮ) ሰላም ለመጠበቅ የሰለጠኑ የደህንነት ሰራተኞች አላስወጣ አላስገባ እንዲሉን እንዲያደርጉ ማሠማራቱ ዛሬ ምናአልባት ሰማይ አይታረስ… ቢሆን እንኳ ነገ በህግ ያስጠይቃል፡፡ይህንንም ከታሪክ መማር ብልህነት እንደሆነ በዚህ ስራ የተሳተፋችው ሁሉ እንድትገነዘቡት አስፈላጊ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡
እንደሚታወቀው ፍትህ በወጣቶች የምትዘጋጅ ጋዜጣ ነች፡፡ በተቃራኒው ደግሞ በእድሜ ከእኛ ጋር የሚቀራረቡ ወንድም እና እህቶቻችን (የደህንነት ሠራተኞች) ትእዛዝ እየሰጣችሁ ስራችንን እንዳንሰራ እንቅፋት መፍጠሩ፤ ጉዳቱ ለሀገርም ጭምር ነው፡፡ የሆነ ሆኖ ግን በእነዚህ የእድሜ አቻዎቻችን ላይ አንዳች ቅሬታ የለንም፡፡ ቅሬታችን ለሀገር ጥቅም ሊውሉ የሚገባቸውን የደህንነት ሰራተኞች ሰላማዊ ዜጐችን እንዲያፍኑና እንዲያሰፈራሩ በመደቡት ላይ ነው፡፡ ይህ በይጊዜው ታገልንለት፣ ተሰዋንለት የምትሉትን ህግ-መንግስት መናድ ነው፡፡ ግልፅና አደገኛ ወንጀል እንደሆነ ልታውቁት ይገባል፡፡
ከዚህ ውጪ የመጣውን መከራ ለፕሬስ ህልውና ስንል እስከመጨረሻው እንቀበለዋለን፡፡ በእርግጥ ይሄ የእኛ የአለማ ፅናት ነው፡፡ ነገር ግን ቀጣዩ ጊዜ አስፈሪ እና አደገኛ ሊሆን እንደሚችል ይገባናል፡፡ ሆኖም ባመንበት አላማ ላይ ቆመን የመጣውን ከመቀበል ውጪ ሌላ አማራጭ እንደማይኖረን ለመንግስት፣ ለህዝብ እንዲሁም በአሁኑ ወቅት ፍትህን በኢትዮጵያ ከሚገኙ የፕሬስ ውጤቶች በህትመት ብዛት አንደኛ ትሆን ዘንድ ላደረጉ አንባቢዎቻችን ግልፅ ማድረጉ አስፈላጊ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ እናም የፍትህ አንገት በአቋም ለውጥ ሊቀለበስ እንደማይችል እና ለስደት የተዘጋጁ እግሮች እንደሌሏት ዛሬም ደግመን ደጋግመን እናረጋግጥላችኋለን፡፡
