መሬት፣ መሬት፣ ሁለት

ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም

መሬት ማለት ብዙ ነገር ነው፤ ገበሬው መሬት ሲል ለም አፈር ነው፤ ለከብት አርቢው የግጦሽ መሬት ነው፤ መሀንዲሱ መሬት ሲል ደልዳላ ሜዳ፣ ድንጋይና አሸዋ ነው፤ ስለመሬት ስናስብ በግድ ስለዓየር ጠባዩና ስለውሃም እናስባለን፤ ለደላላውና ለኪራይ ሰብሳቢው መሬት ሸቀጥ ነው፤ የመሬቱ መሸጥ የሚጎዳው በኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ ተከታታይ ትውልዶችን ነው፤ ገንዘባቸውን ይዘው ወደሌላ አገር የሚንሸራተቱትን አይደለም፡፡

ኢትዮጵያ ነዳጅ ዘይት ወይም ሌላ ማዕድን ስለሌላት ከቡናና ከቆዳ የበለጠ ገቢ ያስገኛል ተብሎ የተገመተው መሬት ነው፣ መሬትን በመሸጥ ወይም እያከራዩ ኪራይ በመሰብሰብ በመበልጸግ ይቻላል ተብሎ ታስቦአል፤ ለውጭ አገር ሰዎች በማናቸውም መንገድ የመሬት መብትን ማስተላለፍ ውሎ አድሮ አብዛኛውን የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያደኸይ እንደሚሆን አያጠራጥርም፤ ጥቂት ሰዎች በጣም እንደሚከብሩም አይጠረጠርም፡፡

የመሬት ድልድል አንደኛ የህዝቡን ቁጥርና ዓመታዊ እድገት፣ በሥራ ላይ የዋለው መሬት ምርታማነት፣ ለአቅመ አዳምና ለአቅመ ሄዋን የደረሱት ሰዎች በምርታማነት፣ የሕዝብ ብዛት በመሬቱ ላይ ያለው ጫና፣ ኑሮው በመሬት ላይ የተመሰረተው ህዝብ (እርሻ፣ ከብት እርባታ፣ አትክልት፣ ፍራፍሬ፣…) ቁጥሩ እያደገ ወይም እየቀነሰ መሄዱ፣ የእርሻው ዘዴ በአለፉት ሁለት ሺህ ዓመታት የነበረው ዓይነት ሆኖ መቀጠሉ፣… የእነዚህና የእነዚህን የመሰሉ ጥያቄዎች ትክክለኛ መልስ ከአገኘን በኋላ በአሁኑ ጊዜ የሚሰራበት የመሬት አስተዳደር ለሚቀጥለው ትውልድ ምን ውጤት እንደሚኖረው በትክክል ለመገመት እንችላለን፤ ለጊዜው ግን በሚሰማው የመሬት ችሮታና ጅምላ ችብቸባ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ከካስትሮ አብዮት በፊት ኪዩባ የነበረችበት የአገሩ ሰው መሬት-የለሽ ባይተዋር ሆኖ፣ ባለመሬቶቹ ሁሉ የውጭ ሰዎች የነበሩበት ሁኔታ የሚመጣ ይመስላል፤ በዚያን ጊዜ ስለነበረው የኪዩባ ሁኔታ ሟቹ ፕሬዚደንት ኬኔዲ ‹‹በቅኝ አገዛዝ ስር ያሉትን ጨምሮ የኢኮኖሚ ቅኝ አገዛዝ፣ ውርደትና ብዝበዛ ከኪዩባ የባሰ የታየበት አገር የለም፤›› ብሎ ነበር፤ የተያዘው የመሬት ሸቀጥነት ከቀጠለ ኬኔዲ ስለዱሮው ኪዩባ የተናገረው በኢትዮጵያ አይደርስም ለማለት አዳጋች ነው፡፡

ዛሬ የኢትዮጵያን መሬት እኩል ብንካፈል ለእያንዳንዳችን የሚደርሰን 14 123.63 ካሬ ሜትር ነው፤ ይህ አባጣ-ጎርባጣውን፣ ገደላ- ገደሉን፣ በረሃውንና ምድረ-በዳውን ጨምሮ ነው፤ ይኸው መሬት ለመኖሪያ፣ ለስራ፣ ለምግብ፣ ለግጦሽ፣ ለጨዋታ፣ ለመመላለሻ፣ ለቆሻሻ መጣያ፣ ለመቃብር፣ ለማገዶና ለቤት ሥራ ዛፍና ለሌላም አስፈላጊ ነገር ሁሉ የሚያገለግል ነው፤ ከጠቅላላው የአገሪቱ መሬት ላይ 3 000 000 ሄክታር ብናነሳለት፣ ለእያንዳንዳችን የሚደርሰን በዚያው መጠን ይቀንሳል፤ 13 790.3 ካ.ሜ ብቻ ይሆናል፤ ሆኖም ችግሩ በዚህ ትውልድ ላይ አይከሰትም ይሆናል፤ አሁን የመሬት ችግር መኖሩን የማያውቁ ባለስልጣኖችና የደላቸው ሀብታሞች ብቻ አይደሉም፤ በመንገድ ላይ የሚተኛው ደሀና ዘመድ ሲሞትበት የሚቀብርበት እያጣ የሚንከራተተውም ነው፤ ለአንድ መቃብር አስርና አስራ አምስት ሺህ ብር ሲከፈል መሬት አልተወደደም ለማለት ይቻላል? ዘመናዊ ቀባሪዎች ተፈጥረዋል፤ ስርዓቱ ዘመናዊ መሰለ እንጂ ያው መሬት መብላቱን አልተወም፤ ቀብርን የሚተካውና መሬት የማያስፈልገው የሬሳ ማስተናገጃ ማቃጠል ገና አልተጀመረም፤ የባህሉ ጣጣ አስሮታል፤ ማገዶውም እየተወደደ ነው፤ ነገር ግን ሬሳ ማቃጠሉ ቢለመድ መሬትን ይቆጥባል፤ ለደሀውም፣ ለአካባቢ ንጽሕናም የተሻለ ይሆን ነበር፤ ሹሞቹ ግን ገና አላሰቡትም፡፡

የመሬት አያያዛችን ጭራሽ ማሰብ የሚባል ነገር አይታይበትም፤ ለምሳሌ በአጼ ኃይለ ስላሴ ዘመን ጀምሮ የጮሁኩበት የአዲስ አበባ-ናዝሬት መንገድ አለ፤ ይህ መንገድ የሚያልፍበት መሬት ለእርሻ በጣም ጥሩ ከሚባሉት ውስጥ ነው፤ ነገር ግን ለመንገድና ለኢንዱስትሪ፣ ለከተማ ቤት አስፋልት እየለበሰ በመጥፋት ላይ ነው፤ ያልተማሩ የሚባሉ ሰዎች በየገጠር ከተማው ለገበያ (ሰኞ ገበያ… ቅዳሜ ገበያ) የሚመርጡት መሬት ኮረኮንችና ለእርሻም ሆነ ለግጦሽ የማይሆነውን ነው፤ መኖሪያ ቤታቸውንም ቢሆን አብዛኛዎቹ የሚሰሩት ለእርሻ የማይሆነው መሬት ላይ ነው፡፡ ዛሬ በአሜሪካ፣ በካናዳና በአውስትራልያ መንገድ ለመሥራት ወይም የባቡር ሀዲድ ለመዘርጋት ሲፈልጉ ስለመሬት ያስባሉ፤ ነገር ግን እንደ እንግሊዞች አይጨነቁም፤ እንግሊዞች መንገዱን ያጠማዝዙታል እንጂ በጥሩ እርሻ መሬት ላይ እንዲያልፍ አያደርጉም፤ በስዊትዘርላንድ ደግሞ የባሰ ነው፤ አሜሪካ፣ ካናዳና አውስትራልያ መሬት በሽበሽ ነው፤ በአሜሪካ እንዲያውም ገበሬ መሬቱን እንዳያርስ ገንዘብ ይከፈለዋል፤ ለሚመጣው ትውልድ ችግር እንዳያወርሱ ብለው የሚያደርጉት ነው፤ እኛ የምንመራው በእኔ ከሞትሁ ሰርዶ አይብቀል ነው፡፡

ከዚህ በታች ያለው ሰንጠረዥ ምናልባት ያሳስበን ይሆናል፤ ከ2004 እስከ 2044ዓ.ም በዓርባ ዓመት ውስጥ ሊደርስብን የሚችለውን ችግር በግርድፉም ቢሆን የሚያሳየን ይመስለኛል፤ አንድ ቤሰተብ በአማካይ አምስት አባሎች አሉት ቢባል ዛሬ አስራ ስምንት ሚልዮን ሲሆን በ2044 ሰባ ሁለት ሚልዮን ቤተሰቦች ይኖራሉ፤ ፍትሐዊ ማህበረሰብ ብንሆን ዛሬ ለአንድ ቤተሰብ ሰባት ሄክታር መሬት ያህል ይደርሰው ነበር፤ ይህ ባለመሆኑ ያለውን ችግር እናውቃለን፤ በ2044ዓ.ም የህዝቡ ቁጥር ሶስት መቶ ስድሳ ሚልዮን ሲደርስ ችግራችን የት ይደርሳል? ብሎ ለመጠየቅና አስፈላጊውን ዝግጅት ለማድረግ አእምሮና በጎ ፈቃድ ያሻል፡፡

ደርግ ሀብታሙን በወረሰ ጊዜ በሀብታሙ መደህየት ደሀው የሚያተርፍ መስሎት እንደተደሰተ፣ በዛሬውም አዋጅ ቤት የሌላቸው ሰዎች ሊቃወሙት አይገባም በማለት አንዱ ጮሌ ሹም በቲቪ ሲናገር ሰማሁት፤ ሹሙ የኢትዮጵያ ደሀ የተማረውን ሳይማር ቀርቷል፤ በጉን ሲከተል እንደዋለው ቀበሮ ነው፡፡

ስደተኞቹ ጠገራ ብራቸውን ይዘው ሲመጡ በቀላሉ መሬት እንዲያገኙ ለመዘጋጀት ከሆነ በወር በወሩ የሚለወጥ የመሬት አዋጅ ለጠገራ ብሩ ዋስትና ሊሆን ይችላል?

ዓ.ም የሕዝብ ቁጥር የመሬት* ስፋት
በካ.ኪ.
የሕዝብ
ጫና/ካኪ
ቤተሰብ ለቤተሰብ
በሄክታር
2004 90 000 000 1 271 127 71 18 000 000 7.06
2024 180 000 000 (በመደህየት ያንሣል
እንጂ አይጨምርም)
142 36 000 000 3.53
2044 360 000 000 283 72 000 000 1.77

Comments

ohhh Pro it's very good

Our mastermind God bless you.

Thanks a lot ,long live proffessor & other ethiopian acadamicians.

long live prof.mesfen

Prof please Keep on challenging our mind with such logical and wonderful approaches. Otherwise in the near future we can not talk a single word other than the dam and the PM. But I believe that these gorillas can cheat some people for some time but not all the people all the time.

ፕሮፌሰር ትንታኔዎን አደንቃለሁ። ስለ ሬሳ ማቃጠል የተናገሩትን የሰይጣን ጆሮ አይስማው። በባህላችን ሰው በሕይወት ካለው ይልቅ የሞተን ያከብራል። ሬሳ ካየ ፊቱን በሁለት እጁ አብሶ ቆሞ ያሳልፋል። ለምን እንደሚያብስ አላውቅም። ተስፋ የቆረጠ ደሃም <ብሞትም ያቺን ሦስት ክንድ መሬት እንደሆን የሚከለክለኝ የለም> ነው የሚለው። ስለዚህ እሷን አይጣ።መጽሐፍም <ኦ አዳም መሬት አንተ ወትገብእ ውስተ መሬት> አለ እንጂ የሳት እራት ነህ በእሳት ትቃጠላለህ አላለም።

ቦጋለ ዳኜ

የመሬቱ መሸጥ የሚጎዳው በኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ ተከታታይ ትውልዶችን ነው፤ ገንዘባቸውን ይዘው ወደሌላ አገር የሚንሸራተቱትን አይደለም፡፡

God please keep Ethiopia
I am so sorry due to all activities done by this Narrow and racist government

hi prof you are the father of us
thank you

thank u very much prof. and long live for u

Add new comment

Filtered HTML

  • Web page addresses and e-mail addresses turn into links automatically.
  • Allowed HTML tags: <a> <em> <strong> <cite> <blockquote> <code> <ul> <ol> <li> <dl> <dt> <dd>
  • Lines and paragraphs break automatically.

Plain text

  • No HTML tags allowed.
  • Web page addresses and e-mail addresses turn into links automatically.
  • Lines and paragraphs break automatically.