ሐተታ አድዋ
የአድዋ ድልን ከድንበር ሉአላዊነት ጋር አያይዞ መተንተን የተለመደ ነው፡፡ ድሉ አነሠ በዛ የሚለው ጭቅጭቅ ከዚህ መሠረት ይፈልቃል፡፡ በኔ ግምት የአድዋ ድል ትልቅ ጭብጥ ‹‹የሰውነት ክብር›› ይሰኛል፡፡ ቀደምቶቻችን ወደ አድዋ የጋለቡት በግፍ የተነጠቁትን የሰውነት መታወቂያ ለማስመለስ ነው፡፡ እንዲያውም ሰው መሆናቸውን በማያዳግም መንገድ ያረጋገጡት አድዋ ላይ ነው ማለት ይቻላል፡፡
ወገኖቼ!! ሰው መሆንን ማረጋገጥ ቀላል ነገር አይምሰላችሁ፡፡
አባቶቻችን ከአውሮፓውያን ጋር የሚጋሩትን ግን ደግሞ ከአውሮፓውያን ቀድመው የሚያውቁትን ቅዱስ መጽሐፍ ጠቅሰው ሁላችንም ያዳም ልጆች ነነ ይሉ ነበር፡፡ እና ያዳም ልጆች ነነ ብለው የሚያምኑ ፈረንጆች ቢቸገሩ የሚደርሱላቸው፣ ቢጠቁ የሚታደጓቸው ወንድሞቻቸው እንደሆኑ ያስቡ ነበር፡፡ በርግጥም የሃይማኖት አንድነት የቀለም ልዩነትን ደምስሶ አዳማዊ ወንድማማችነትን ያስገኘበት የዘመን ምዕራፍ ነበር፡፡ ክርስቶፈር ደጋማ የተባለ የፖርቹጋል ነፍጠኛ ለኢትዮጵያ ደሙን ያፈሰሰው የማተብ አንድነት ስለገፋፋው ነው፡፡
ይሁን እንጂ ባንድ ወቅት የሚያገለግል የኑሮ ዋስትና በሌላው ዘመን አያገለግልም፡፡ ሁላችንም ያዳም ልጆ ነነ የሚለው የዝምድና ውል ከእለታት አንድ ቀን ያገልግሎት ዘመኑ አለቀ፡፡ በ1548 ተወልዶ በ1600 እንደጧፍ የተቃጠለው ዦርዳኖ ቡርኖ የተባለ የጣልያን መናፍቅ ‹‹ኢትዮጵያውያን ያዳም ልጆች አይደሉም፤ ቅድመ-አዳማዊያን ናቸው እንጂ›› ብሎ ፃፈ፡፡ በቡርኖ ዘመን ኢትዮጵያ የጥቁር ዘር ሁሉ የወል ስሙ ነው፡፡ ቅድመ አዳማዊ ማለት ደሞ በአዳምነት ማዕረግ ያልደረሠ ጅምር ፍጡር ማለት ነው፡፡ ይህ አስተሳሰብ ጥቁሮች በእግዜር አምሳል የተፈጠሩ አይደሉም የሚል ድምዳሜ ላይ ያደርሳል፡፡ ያለማለዘቢያ ለመግለፅ፣ ጥቁሮች ከእንሥሣትና ከእፅዋት ይመደባሉ ማለት ነው፡፡ ነገሩ ይበልጥ የሚያስገርመን ይህንን አመለካከት ከጥንታዊያን ግሪኮች ነባይ አመለካከት ጋር ስናመዛዝነው ነው፡፡ ጥንታውያኑ ግሪኮች ጥቁሮችን ከአማልክት ጋር ያወዳድሯቸው እንደነበር ለመገንዘብ የሆመርን ውዳሴ መስማት ይበቃል፡፡ ሆመር እንዲህ ይዘምራል፡፡
እናንት ኢትዮጵያውያን ከሰው ዘሮች ሁሉ እንከን የሌላችሁ
ከተንኮል ከክፋት ከሰው ድክመት ሁሉ ነፃ የሆናችሁ ከቶ ከምን ይሆን የተፈጠራችሁ? ምንድነው ባህሪያችሁ?
እግዜሮች ትሆኑ ወይስ ሰዎች ናችሁ? (ከሀዲስ አለማየሁ ትርጉም የተጠቀሰ)
ታዲያ በጥንታዊ ግሪኮች ሰው ናቸው አማልክት? ተብለው የተጠረጠሩ ጥቁሮች፣ በአስራ ሰባተኛው ክፍለ ዘመን ሰው ናቸው እንስሳ? ተብለው ለምን ተጠረጠሩ? የጥቁሮችን ሰውነት መካድ ለምን አስፈለገ?
መልሱ ብዙም የተወሳሰበ አይደለም፡፡
የቅኝ ግዛት ዳርዳርታው ለቅኝ የታጩ ህዝቦችን የሰውነት መታወቂያ መንጠቅ ነው፡፡
ሰው በድንግል ተፈጥሮው መሠሉን ለማጥፋት ልቡና እጁ በቀላሉ አይታዘዙለትም፡፡ ይህንን ለማድረግ ባፍራሽ ንድፈ ሀሳብ መታገዝ ይኖርብታል፡፡ ሰው፣ በጎች ነፍስ የላቸውም ብሎ ራሱን ካሳመነ ጀምሮ በጎችን ወደ ቀይወጥ ለመለወጥ የህሊና ወቀሳ የለበትም፡፡ አውሮፓዊውም ጥቁሮችን ጨፍጭፎ አገራቸውን ለመቀማት ከሰው ተራ አውጥቶ ከዋርካና በጥድ ተራ ማሰለፍ አስፈላጊ ሆኖ አግኝቶታል፡፡ ባድዋ ድባቅ የተመታው የጣልያን ቅኝ ወራሪ ኃይል ኢትዮጵያውያኑን ከማይገባቸው ማሣ ላይ የተሰማሩ ገመሬዎች አድርጎ ሳይቆጥራቸው አልቀረም፡፡ የጣልያኑ ጄኔራል (ባሪያቴሪ መሰለኝ) በጦርነቱ ዋዜማ ‹‹…ምኒልክን በቀፎ አስገብቼ አበረክትላችኋለሁ›› ብሎ ለሮማውያን ወንድሞቹ መጐረሩ በአእምሮው ውስጥ የነበረው ምስል ምን እንደነበር ፍንጭ ይሰጠናል፡፡
‹‹መትረየስ ጠመዱ
አሉ በርከክ በርከክ
አውሬ መስያቸው
ከሰው መወለዴን ማን በነገራቸው?›› አለ አቅራሪ፡፡
ታዲያ አባቶቻችን እንዲህ በአደባባይ የተነጠቁትን የሰውነት ክብር ለማስመለስ ከፍልሚያ ውጭ ምን አማራጭ ነበራቸው?? ፓትሪክ ሄነሪ የተባለው የአሜሪካ አርበኛ ‹‹ነፃነቴን ወይም ሞቴን ወዲህ በሉ!›› ብሎ በአሜሪካ ተራራዎች ላይ ከመጮኹ አንድ መቶ አመት አስቀድሞ ኢትዮጵያውያን ‹‹…ይኄይስ መዊት በክብር እምሐይው በኃሣር (በውርደት ከመኖር በክብር መሞት ይሻላል) የሚለውን መፈክር ያውቁት ነበር፡፡ (የሰርፀ ድንግልን ዜና መዋዕል ተመልከት)
አባቶቻችን አይን ያጠፋውን አይኑን በለው የሚለው ኦሪታዊ ሕግ ለአድዋ ዋዜማ ተስማሚ ሆኖ አግኝተውታል፡፡ እንደ ሰው ያልቆጠራቸውን ጠላት እንደ ሰው ሊቆጥሩት አልፈለጉም፡፡ አፄ ምኒልክ በጦርነት አዋጃቸው ‹‹…እኔም ያገሬን ከብት ማለቅ፣ የሰውን መድከም አይቼ ዝም ብለው ደግሞ እያለፈ እንደፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር›› አሉ፡፡ በዚህ ንግግር ውስጥ ያለው ትልቅ ነገር ጣልያኑ እንደ ፍልፈል መታየቱ ነው፡፡ አጤ ምኒልክ ያገራቸው ወታደር ለወራሪው ሰብዓዊ ዝምድና ተሰምቶት እንዲሳሳለት አልፈለጉም፡፡ በጦርነቱ ወቅት በተመሳሳይ መልኩ ወራሪን ወደ አውሬ የመለወጥ የስነ ልቦና ቅኝት የነበረ ይመስለኛል፡፡ ለምሳሌ በመቀሌ ጦርነት ዋዜማ ራስ አሉላ በተገኙበት ጉባኤ ቀኛዝማች በሻህ ጣልያኑን በዜግነት ስሙ መጥራት ሳያስፈልጋቸው ‹‹…በሾተል እየቀነጠሰን በግንቡ ውስጥ እንደ አይጥ እንፈጀዋለን›› ሲሉ መስማቱን በጅሮንድ ተክለሐዋርያት በግለ-ታሪኩ ይዘግባል፡፡
ታሪክ በሠፈሩት ቁና ይሠፍራል፡፡ ጣልያኖች ከሰው ተራ ወጥተው በፍልፈልና በአይጥ ሰልፍ ውስጥ ገብተው ለእልቂት ተመቻቹ፡፡ አዎ፣ ውርደት እንደ ተስቦ ነው፡፡ ወደ አዋራጁም ይጋባል፡፡
ወታደር ባለመሆኔ የጦርነቱን ውሎ ማተት አያምርብኝም፡፡ ያም ሆኖ የአድዋ ድል ዛሬ ብርቅ በሆኑብን ሁለት እሴቶች ረድኤት የተገኜ ይመስለኛል፡፡እኒህ ሁለት እሴቶች መተባበርና መደማመጥ ናቸው፡፡ ጣልያኖቹ በጊዜው ወደ ጦርነት ሲገቡ ተስፋቸውን የጣሉት በመድፍና በጠመንጃቸው ሳይሆን ኢትዮጵያውያን ዝነኛ በነበሩበት የውስጥ መቆራቆስ ላይ ነው፡፡ የትግራይ ቅልጥም ሲመታ ሸዋ ያነክሳል ብለው አላሰቡም፡፡ በርግጥም በክፍለ ሀገሮች ውስጥ የተለያዩ ሽኩቻዎች ነበሩ፡፡ እኒህን ሽኩቻዎች አስረስቶ ኢትዮጵያውያንን ሁሉ ለአንድ አላማ ማሠለፍ ምኒልክነትን ይጠይቃል፡፡
መደማመጥ ያልሁትን ላሳይ፡፡ አባ ዳኘው ከዛሬው የይስሙላ ፓርላማችን በተሻለ ሁኔታ ለልዩነቶች ቦታ የሚሰጥ ተንቀሳቃሽ ምክር ቤት በጦርነቱ ወቅት መፍጠር ችለዋል፡፡ ፀሐፌ ትእዛዝ ገብረሥላሴ በውጊያው ዋዜማ የነበረውን ሁኔታ እንዲህ ይገልፁታል
‹‹…አፄ ሚኒልክም በበነጋው ሰራዊቱን የቀኙን በቀኝ፣ የግራውን በግራ አሰልፈው ነጋሪትዋን እያስመቱ ወደሱ ተጓዙ፡፡ ኢጣሊያኖችም ዘበኛው ሲመጣ ባዩ ጊዜ ተመልሰው ወደ እርዳቸው ገብተው ተኙ፡፡
ከዚህ በኋላ ሰራዊቱም እንደ ኤሊ ስንመጣበት ከድንጋይ ይገባል፤ ስንመለስ ይወጣል፤ እንዲህ አርጐ ሊጫወትብን ነውን? ብሎ እጅግ አጥብቆ ተናደደ፡፡ መኳንንቶቹም ተሰብስበው ከዚህ ሰፍረን አድረን በማለዳ እዚያው ካሉበት ከርዱ ድረስ ሄደን እንዋጋለን ብለው መከሩ፡፡ ንጉሠ ነገሥቱም እሺ ብለው ድንኳኑን ለማስመጣት አዘዙ፡፡
ይህ ምክር ካለቀ በኋላ የትግሬው ገዢ ራስ መንገሻ ተሰልፎ በፈረስ ሆኖ መጣ፡፡ እሱም ይህ ምክር እንዳለቀ ባዬ ጊዜ አንድ ነገር ልናገር ይፍቀዱልኝ ብሎ ወደ ንጉሠ ነገሥቱ ቀርቦ እንዲህ አለ፡፡ እንደ ተርታ ነገር ካልሆነ ስፍራ ሄደን ልናስፈጀው ነውን? አለ፡፡ ይህ ምክር የተስማማ ምክር ሆነ፡፡ አፄ ምኒልክም ተመልሰው ከድንኳንዋ ከገቡ በኋላ እንዲህ አሉ፡፡ እንግዲህ ከሰፈሬ ወጥቶ ተኩስ አልጀመረ ባይኔ ካላየሁት ተሰልፌ አልወጣም፡፡››
ፀሐፌ ትእዛዝ ያቀረቡትን ዘገባ ወደ ዘመናዊ አማርኛ አሳጥሬ ሳዛውረው የሚከተለውን ይመስላል፡፡
ርዕሰ-ብሔር ምኒልክ ሰራዊታቸውን እየመሩ ወደፊት ሲገሰግሱ የጣልያን ሰራዊት ስልታዊ ማፈግፈግ አድርጎ ወደ ምሽጉ ገባ፡፡ ምኒልክ በቀጣዩ ስትራቴጂ ላይ ለመወያየት አስቸኳይ ስብሰባ ጠሩ፡፡ በስብሰባው ላይ ወደ ጠላት ምሽግ ሄደን እንዋጋ የሚል ሐሳብ ቀርቦ ባብላጫ ድምፅ ፀደቀ፡፡ ምኒልክም በብዙሃኑ ተሰብሳቢ የቀረበውን ሐሳብ ለማስፈፀም ተዘጋጁ፡፡ ይሁን እንጂ ጄኔራል መንገሻ ዮሐንስ ዘግይቶ ስብሰባውን ከተቀላቀለ በኋላ ‹‹ምሽግ ድረስ ሄዶ መዋጋት በወገን ጦር ላይ ጉዳት ያስከትላል›› ብሎ መከራከር ጀመረ፡፡ ምኒልክም ‹‹እኔ አንዴ ወስኛለሁ፤ ውሳኔዬ ካልጣመህ በሊማሊሞ በኩል ማቋረጥ ትችላለህ›› ብለው ሳያሸማቅቁት ሐሳቡ እንዲጤን አደረጉለት፡፡ ሐሳቡ በድምፅ ብልጫ ፀደቀ፡፡ በድምፅ ብልጫ ያልሁት ‹‹ይህ ምክር የተስማማ ምክር ሆነ›› የሚለውን የፅሐፌ ትዕዛዙን አማርኛ ተርጉሜ ነው፡፡
እንደተመለከተው አጤ ምኒልክ ልዩ ልዩ ሐሳቦችን ለማዳመጥና አወዳድረው የነጠረውን ሐሳብ ለማስፈፀም ዝግጁ ነበሩ፡፡ በአራት ነጥብ የታጠረ ግትርነት አልነበረባቸውም፡፡
ሾፐናወር የተባለ የጀርመን አገር ፈላስፋ ከአድዋ ሠላሳ አምስት አመት አስቀድሞ ‹‹ከጥንት ግብፃውያንና ከህንዶች ውጭ ያለው ታላቅ የስልጣኔ ፍሬ ሁሉ በነጮች ጥረት ውጤት ነው፡፡ ከጥቁር ህዝቦች መካከል እንኳ የገዢነትን ስልጣን የሚይዙት በቀለም ፈካ ያሉት ናቸው›› ብሎ ነበር፡፡ ያጤ ምኒልክ ፊት ይህንን ንድፈ ሐሳብ በይፋ ለማስተባበል የተፈጠረ አይመስልም?

Comments
Kinfe (not verified)
Sun, 03/04/2012 - 11:30
Permalink
Excellent
Excellent
Tulu Forssa, (not verified)
Sun, 03/04/2012 - 15:14
Permalink
Spot on Beweketu, as always.
Spot on Beweketu, as always. I am proud to be your compatriot.
ephrem (not verified)
Mon, 03/05/2012 - 06:34
Permalink
pill to racist
it is a very wonderful humor. if our leader are willing to see the other perspective of Adwa this is a nice looking. i like the way beweketu put the significance of Adwa in teadresrms of Humanity. i recommend this article to our EPRDF cadres this is a good pill to recovered from painful racist mentality.
Ethiopia (not verified)
Mon, 03/05/2012 - 15:51
Permalink
"I wish I wrote 'ሐተታ አድዋ'!"
Long live በዕውቀቱ በዕውቀቱ!
You are a born great analyst,you gave the history a human face!
I would like to borrow a line from a blurb:"I wish I wrote ሐተታ አድዋ!"
dada (not verified)
Tue, 03/06/2012 - 12:59
Permalink
WOW!!!
WOW!!!
Anonymous (not verified)
Tue, 03/06/2012 - 20:18
Permalink
If some boday has to write,
If some boday has to write, it should be like this. It does not need racial or religious similarity to be convinced by the article. I recommend this article to be read by the present leaders to consider the role of common understanding and cooperation. This article summerizes everything, the current problems of ethiopia. Bravo Bewketu!!! I urge the government to increase freedom of speech, perhaps the government it self will benefit from it.
Mesfin (not verified)
Wed, 03/07/2012 - 11:32
Permalink
Comment
Simply great!!
Thank You Bewketu for sharing such an exciting perspective.
derso2012@yahoo.com (not verified)
Wed, 03/07/2012 - 16:14
Permalink
admire
fantastic
Sol (not verified)
Sat, 03/10/2012 - 09:00
Permalink
Tebarek
Ewnet ejih yibarek! At'erechibign libel?
joc (not verified)
Tue, 03/13/2012 - 14:59
Permalink
እንደተመለከተው አጤ ምኒልክ ልዩ ልዩ ሐሳቦችን ለማዳመጥና አወዳድረው የነጠረውን ሐሳብ ለማስፈፀም ዝግ
እንደተመለከተው አጤ ምኒልክ ልዩ ልዩ ሐሳቦችን ለማዳመጥና አወዳድረው የነጠረውን ሐሳብ ለማስፈፀም ዝግጁ ነበሩ፡፡ በአራት ነጥብ የታጠረ ግትርነት አልነበረባቸውም፡፡
Add new comment