ፕ/ር ገብሩ ከኢትዮጵያ ህዝብ ራቁ ወይስ ከህወሓት ታረቁ? (በተወልደ በየነ)

በቅድሚያ ያለሙያችን ገብተን እንድንፅፍ የተገደድንበት ምክንያት ሙያተኞቻችን ሙያቸውን እንደረሱና አስታዋሽ እንደሚያስፈልጋቸው ስላሳወቁን መሆኑን በትህትና እገልፃለው፡፡ አሁንም በድጋሜ ..አስቀድሜ.. ልበልና አስቀድሜ አንድ ነገር ልናገር፡- የታሪክ ምሁር ማለት እንደጦረኛ ያልተመቸውን የሰውን ሀሳብ ለማጥቃት እና ለመውጋት (ለማሸነፍ) የሚነሳ ባህሪ የለውም፡፡ እውቀቱም በጨለማው (ባለፈው) ዘመን ላይ ብርሃን የሚፈነጥቅባት እንጂ በስሜት እና በወገንተኝነት ለፍልሚያ የሚሰደር እንደማይሆን ከእኔ በእጅጉ የበለጠ እውቁ የታሪክ ምሁር ፕ/ር ገብሩ ታረቀ ያውቁታል ብዬ አስባለው፡፡ የእኔ ድርሻ ማስታወስ ብቻ ነው፡፡ (አስታዋሽ እንደሚፈልጉ ስለነገሩን ነው ይህንን ያልኩት፡፡)
አሁን ወደ ርዕስ ጉዳዬ ልለፍ፤ አርብ ነሐሴ 20ቀን 2003ዓ.ም በወጣችው ፍትህ ጋዜጣ ላይ ፕ/ር ገብሩ ..ለፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም.. በሚል ርዕስ ያቀረቡት ትችት አከፋፍዬ በማንበብ Distortion ላይ የተመሰረተ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ ለምሳሌ ፕ/ር መስፍን የአቶ ስብሃት ነጋን ..የቢሆን ኖሮ.. የታሪክ ትንተና ሲተቹ እንዲህ ብለው ፅፈዋል .....ቢሆን ኖሮ በማለት ክርክሩን መለወጥ ይቻላል፤ ለምሳሌ በኤርትራና በትግራይ ይኖሩ የነበሩ የኤርትራና የትግራይ ዜጐች ተግተው ኢጣሊያን ቢወጉ ኖሮ ከሐረር፣ ከሲዳማ፣ ከሸዋ ወደ ሰሜን መዝመት አያስፈልጋቸውም ነበር፡፡ ዛሬ ሌሎች ያልሞቱትን ሞት በመሞታቸው አይወቀሱም ነበር፡፡ ከኋላዬ ሁለት ተጨማሪ አይኖች ቢኖሩኝ ቁመቴ አስር ሜትር ቢሆን እያሉ መከራከር የትም አያደርስም፡፡ ለልቦለድ ስራ እንጂ ለታሪክ አይበጅም፡፡.. (ፍትሕ ነሐሴ 6ቀን 2003) ፕ/ር ገብሩ ለዚህ አንቀፅ የሰጡት ምላሽ ደግሞ እንዲህ ይነበባል ..የአድዋ ጦርነትን በተመለከተ የኤርትራና የትግራይ ዜጐች ተግተው ኢጣሊያንን ቢወጉ ኖሮ (መስመር የኔ ነው) የመሐል ሀገር ወገኖቻቸው ወደ ሰሜን መዝመት ባላስፈለገ ነበር.. ይሉናል፡፡
ፕ/ር ገብሩ ለክስ እንዲያመቻቸው ከጥቅሱ ውስጥ የወሰዱት ያሰመርኩበትን ኃይለ ቃል ነው፡፡ .....እያሉ መከራከር የትም አያደርስም.. የሚለውን የፕ/ር መስፍንን መደምደሚያ ሆን ብለው ዘለውታል፡፡ ይህ ምሁራዊ ስነ ምግባር የጎደለው ተግባር ይመስለኛል፡፡
በዚህ ከላይ በጠቀስኩት የፕ/ር መስፍን አንቀጽ ላይ የውዝግብ መነሻ የሆነው .....የኤርትራና የትግራይ ዜጐች.. የሚለው አባባል ነው፡፡ እኔ እንደገባኝ ፕ/ር መስፍን ..የትግራይ ዜጋ.. ያሉት የትግራይ ባላገር፣ የትግራይ ጭሰኛ የሚለውን ሀሳብ ለመግለፅ ነው፡፡ ምክንያቱም ..ዜጋ.. የሚለውን ቃል አለቃ ኪዳነወልድ ክፍሉ ሲፈቱት .....ዜጋ፡- በቁሙ ተገዥ፣ ባላገር፣ ገባር፣ ጭሰኛ ማለት ነው.. (መጽሐፈ ሰዋሰው ገፅ 418)
ይህ ሆኖ ሳለ ፕ/ር ገብሩ፣ ፕ/ር መስፍንን .....ደግሞ ኢትዮጵያዊ ዜግነትን በትግራይ ዜግነት መተካትዎ ምን ቢያስቡ ነው?.. ብለው ጠይቀዋቸዋል፡፡ በፕ/ር መስፍን አባባል ውስጥ የኢትዮጵያዊ ዜግነትን በትግራይ ዜግነት መተካትን የሚገልፅ ንባብ የለም፡፡ እኔም እርሶን ልጠይቅና፤ እርሶስ ከየት አመጡት?
...ወደ ሌላው እንለፍ "እንነጋገር ማለት እውነትን በማስረጃ አስደግፎ ነው" ሲሉ ፕ/ር መስፍን የጠቀሱትን ጠቅሰው "የታሪክ ባለሙያነቴን ነውና ያስታውሱኝ አመሰግኖታለሁ" የሚል ምስጋና አቅርበዋል፡፡ ምስጋና አይከፋም ይሁን፡፡ ሆኖም ግን ፕ/ር ገብሩ የኢትዮጵያ ታሪክ (አሁንም በስልጣን ላይ ባሉ መሪዎቻችን) ከ3000 አመት በግሽበት ወደ 100 አመት ሲያሽቆለቁል ምነው የታሪክ ባለሙያነቶት ትዝ አላሎትም? በ1988 የአድዋ 100ኛ አመት አከባበር ዝግጅት ላይ በተካሄደ የፓናል ውይይት እነ ፕ/ር እንድርያስ እሸቴ "አፄ ሚኒልክ ከአድዋ ጦርነት መሸሽ ጀምረው ነበር፤ የትግራይ ህዝብ ይዞ ባያስቀራቸው ኖሮ" የሚል የታሪክ ክህደት ሲነግሩንስ እንዴት የታሪክ ምሁርነቶት ትዝ አልሎት አለ?
እሺ ክቡር ፕሮፌሰር.. ..አፄ ሚኒሊክ የእነዚያን 400 የሚያህሉ ኤርትራውያን እጅና እግር አስቆርጠው የህይወት ሽባዎች ያደረጉዋቸው?.. ሲሉ የፃፉት እውነት ግን ምን ለማለት ፈልገው ነው? እዚሁ ጋር ያነሱት አወዛጋቢ ጥያቄ ነው፡፡ የኤርትራን በሻባዙቆች በዚህ መንገድ እንዲቀጡ ሃሳቡን ያቀረበው ማን ነው?
ሀ/ ራስ መንገሻ ዮሐንስ ናቸው (አፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ እንደ ፃፉት ከሆነ)
ለ/ በሰራዊቱ ድምፅ ብልጫ ግብፃዊው ጳጳስ አቡነ ማቲዎስ የወሰኑት ፍርድ ነው፡፡
በወቅቱ የአይን ምስክር የነበረው የታሪክ ፀሐፊ ሌዎንቲፍ የኤርትራውያን ምርኮኞችን ቅጣት አስመልክቶ የፃፈውን አያውቁትም ብዬ ሳይሆን ለማስታወስ ያህል ልጥቀስሎት Leontiev N. Provinces Equatorials or Abyssinia (Paris 1900)… ..ኤርትራውያን በምኒሊክ ፊት ተሰልፈው ሲያልፉ አፄ ሚኒልክ እንደተለመደው ውሳኔ አልሰጡም፡፡ ወደ አቡነ ማቲዎስ ዞረው ተመለከቱ፡፡ ሰራዊቱ ሁሉ ፣ቆራርጧቸው፣ ብለው ጮኹ፡፡ ጳጳሱም ይህንን ፈረዱ፤ በሀገር ክህደት ተወንጅለው ቀኝ እጃቸው እና እግራቸው እንዲቆረጥ ተወሰነ.. ይላል፡፡ እኔ ወይም ፕ/ር መስፍን ሳይሆን ይሄንን ያልነው ፈረንሳዊው ታሪክ ፀሐፊ ነው፡፡
ኢትዮጵያውያኖች ደግሞ ሩህሩህ እና ፍትህ አዋቂ ለሆኑት ንጉስ እንዲ ብለው በዜማ ያወድሷቸዋል፡-
..ደግነትክን ሳላይ በዋልክበት ውዬ
ደርሶ እንደ ሚኒልክ አልልኽም እምዬ..
እናም ምኒልክ ማለት እኚህ ናቸው፡፡ በእኔ እድሜ ሁለት መሪዎችን አይቻለሁ (አቶ መለስን ጨምሮ..፡፡ ነገር ግን ህዝባቸውን ..እዬዬ.. ሲያስብሉ እንጂ ..እምዬ..... ሲባሉ ሰምቼ አላውቅም፡፡
ክቡርነቶ.. ሌላው ያልገባኝ ጉዳይ ስለውጫሌ ውል የአነሱት ነው፡፡ የውጫሌ ውልን ለምን እንዲ ነክሰው እንደያዙት አልገባኝም፡፡ መቼም እኛ ኢትዮጵያውያኖችን የጎዳን የውጫሌ ውል ሳይሆን፤ የአልጀርሱ ስምምነት እንደሆነ ለአንድ የተከበረ የታሪክ ፕ/ር ይጠፋዋል ብዬ አላስብም፡፡
በመጨረሻም ያልገባኝን አንድ ተጨማሪ ጥያቄ ላንሳና በአንድ ኢትዮጵያዊ ተረት ልሰናበቶት፡፡ እርሶ በሀገር አቀፍ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በአለም አቀፍ ደረጃ ምሁር እና ተመራማሪ ሆነው ሳለ ..እኔም እንደ አስግደ ገ/ስላሴ ፣የወዲያው ማዶ፣ ልጅ ነኝ..ን ምን አመጣው? ከቻሉ ይመልሱልኝ፡፡ ከላይ ፅሁፌን እደመድምበታለሁ ያልኩትን ተረት አሁን ደግሞ ልንገሮት .....ከእለታት አንድ ቀን አንድ ዛፍ ስር ተቀምጣ የነበረች ጦጣ፤ ከፊት ለፊቷ ባለጎፈሩ አንበሳ እየመጣ መሆኑን ታይና፤ በፈጣን ዝላይ ተደግፋው በነበረው ዛፍ ላይ ትወጣለች፡፡ አያ አንበሶም በጦጣው ፍጥነት ተደንቆ የሆዱን በሆዱ በማድረግ ..ጦጢት ነይ ውረጂ፤ አልበላሽም.. ሲል ያግባባታል፡፡ ጦጢት ሆዬም ..አልበላሽምን ምን አመጣው.. አለችው አሉ፡፡... የዚያ ማዶ ሰው ነኝን ምን አመጣው ክቡር ፕሮፌሰር?

Comments

it is amazing

Add new comment

Filtered HTML

  • Web page addresses and e-mail addresses turn into links automatically.
  • Allowed HTML tags: <a> <em> <strong> <cite> <blockquote> <code> <ul> <ol> <li> <dl> <dt> <dd>
  • Lines and paragraphs break automatically.

Plain text

  • No HTML tags allowed.
  • Web page addresses and e-mail addresses turn into links automatically.
  • Lines and paragraphs break automatically.