ከማይሸነፈው ጋር መታገል
ደሳለኝ በዛብህ
desalew@yahoo.com
የማይሸነፈው ማን ነው የሚል ጥያቄ ቢቀርብልን ብዙዎቻችን የማይሸነፈውማ ሞት ነው ማለታችን አይቀርም፡፡ ሞትማ ተሸንፎ ይሄውና የአለም ህዝብ ከሚሊዮን ወደ ቢሊዮን ተሸጋግሯል፡፡ አንዳንዶች በተለይም የጥቅም ተጋሪዎች በኢትዮጵያችን የማይሸነፈው ኢህአዴግ ብቻ ነው ብለው ትንሽ ፈገግ ያደርጉን ይሆናል፡፡ ይሄም ቢሆን ምኞት እንጂ እውነት ሊሆን አይችልም፡፡ ኢህአዴግን የመሳሰሉ እንዲያውም ከኢህአደግ የተሻለ ጥንካሬ እና ተቀባይነት ያላቸው ብዙ ድርጅቶችና ስርዓቶች ተሸንፈው የከሰሙና የጠፉ በመሆኑ ኢህአዴግን ከታሪክ ውጪ የሚያደርግ እውነታ ሊኖር አይችልም፡፡
በአንድ ወቅት ታዋቂ ደራሲና ፀሐፊ ለነበረው አቤ ጎበኛ በወቅቱ በነበሩ የገዥው መደብ አባላት አንድ ጥያቄ ቀርቦለት ነበር ይባላል፡፡ ለአቤ ጎበኛ ቀረበለት የተባለው ጥያቄ ..ሰፊው ህዝብ በማለት የምትጽፈው ምን ለማለት ፈልገህ ነው.. የሚል ነበር፡፡ አቤ ጎበኛም ..ሰፊው ህዝብ ማለት ብትገድለው ብትገድለው የማትጨርሰው ነው በማለት መልስ ሰጠ.. ይባላል፡፡
አቤ ጎበኛ ተናገረ የተባለው ተባለም አልተባለም አባባሉ ህዝብን ትገድለዋለህ እንጂ አታሸንፈውም የሚለውን ዘላለማዊ እውነታ በትክክል የሚያስተላልፍ ነው፡፡
እውነታው ይሄ ሆኖ ሳለ አሁንም ድረስ የህዝብን አሸናፊነት ባለመረዳት ህዝብን እናሸንፋለን በማለት ህዝቡን ራሱንና የህዝቡን ሃብት የሚጨርሱ ጨቋኝ አምባገነኖች አሉ፡፡ የማይሸነፈውን እናሸንፍ በማለት የሚችሉትን ያክል የህዝቡን ህይወትና ሃብት ጨርሰው በቅርብ ጊዜ ራሳቸው ያበቃላቸውን አምባገነን ገዥዎችን እናስታውሳለን፡፡ የቱኒዚያ፣ የግብፅና የሊቢያ አምባገነኖች ከማይሸነፈው ህዝብ ጋር በከንቱ ታግለው ተሸንፈዋል፡፡ በየመንና በሶሪያም የህዝብን አይሸነፌነት ያልተረዱ አምባገነኖች የህዝብን ህይወትና ሀብት በከንቱ በማጥፋት ላይ ይገኛሉ፡፡ ሌሎች ተረኛ አምባገነኖችም የማይሸነፈው ሃይል ጡንቻውን አስከሚያሳርፍባቸው ድረስ አሸናፊ የሆኑ መስሏቸው በለመዱት የጭቆና መንገዳቸው ቀጥለውበት ይገኛሉ፡፡ እነዚህ አሁን በስልጣን ላይ ያሉ አምባገነኖች በህዝብ ተሸንፈው ከተባረሩት አምባገነኖች የተለየ ተአምር ስለሌላቸው የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ መሸነፋቸውና መባረራቸው አይቀርም፡፡
ከግድያ መልስ በፕሮፓጋንዳ
ገዥዎች ህዝብን በመግደልና በማስፈራራት ለማንበርከክ ከመንቀሳቀሳቸው በተጨማሪ ልዩ ልዩ የፕሮፓጋንዳ ስራዎችን ያከናውናሉ፡፡ ለምሳሌ በኢትዮጵያ አጼ ኃ/ስላሴ ..ሞዓ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ ቀዳማዊ ኃ/ስላሴ ስዩመ እግዚአብሔር ንጉሰ ነገስት ዘኢትዮጵያ.. በማለት ራሳቸውን በእግዚአብሔር የተሰየሙ ንጉስ በማድረግ በህዝብ ላይ ኃያልና ዘላለማዊ መስለው ታይተዋል፡፡ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ በልጅነት እድሜው ቤተክርስቲያን ለመጀመሪያ ጊዜ በሄደበት እለት ለፀሐዩ ንጉሳችን እድሜ እንፀልይ ንጉሳችን ከሌሉ ፀሐይ አትወጣም እየተባለ በቄሶች ሲሰበክ፣ ህዝቡም መሬት ላይ ወድቆ ለንጉሱ እድሜ ሲለምን እንደነበር ዛሬም ድረስ በደንብ ያስታውሳል፡፡ በኋላም ብዙም ሳይቆይ ንጉሱ ከዙፋን ወረዱ ሲባል ሰምቶ ፀሐይ ከእንግዲህ የማትወጣ መስሎት በእለቱ የወጣችውን ፀሐይ ለመጨረሻ ጊዜ መሰናበቱን ያስታውሳል፡፡ በሚቀጥለው ጠዋት ግን ፀሐይ ተመልሳ ስትወጣ እና የተለመደው ሁኔታ ሲቀጥል ፀሐይ ዛሬ ቢሳካላት ነገ አይሳካላትም አለ እንጂ በጭራሽ የቄሶቹ ስብከት ከንቱ ሆኖ ይቀራል ብሎ አላሰበም ነበር፡፡ እውነታው ግን አሁንም ድረስ ፀሐይ ትወጣለች ትገባለች፡፡
አሁን ባለንበት ወቅት የዚሁ ስብከት ምትክና ተመጣጣኝ ደግሞ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ነው፡፡ ለኢትዮጵያ አብዮታዊ ዴሞክራሲ የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው እየተባለ ነው፡፡ መጠኑ እና ሃሳቡ ያው ንጉሱ ከሌለ ፀሐይ አትወጣም እንደማለት ነው፡፡
የደርግ ስርዓትም የኢትዮጵያንና የጀግኖች አባቶቻችንን ታሪክ ከፍ አድርጎ በማጉላት የኢትዮጵያዊያንን አንድነትና የማይደፈር ዳርድንበር እንዲሁም አለማቀፋዊ ወዛደራዊነትን፣ ሶሻሊምንና ኮሚኒዝምን የመሳሰሉ ስሜት ቀስቃሽና መልካም ሃሳቦችንም በማቀንቀን ኢትዮጵያዊያንን ከጎኑ ለማሰለፍና ድጋፍ ለማግኘት ተንቀሳቅሷል፡፡ በተለይም በአረቡ አለም ለሚገኙ አንዳንድ ኃይሎች ተላላኪ በመሆን ለአገራችን የግዛት አንድነትና የመጪ ው ትውልድ ጠንቆች ናቸው ያላቸውን ክፍሎች ወንበዴ እና ገንጣይ በማለት ይህ ቀረሽ የማይባል የፖለቲካ እና የማቴሪያል ድጋፍ አሰባስቧል፡፡
ኢህአዴግም ዴሞክራሲንና ሰላማዊ የስልጣን ሽግግርን ይዞ ይመጣል ተብሎ የተጠበቀ ቢሆንም ለአገዛዙ የማይመቹትን ገድሏል ወይም አስገድሏል፤ ብዙዎቹን አገር ጥለው እንዲሰደዱ አድርጓል፡፡ እንደማንኛውም አምባገነን ገዥ የፕሮፓጋንዳ ስራዎችንም አካሂዷል፡፡ አሁንም በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ የኢህአ ዴግን የፕሮፓጋንዳ ስልት ከሌሎች በኢትዮጵያ ውስጥ ከተፈጠሩት ጨቋኞች ሁሉ የተለየ እና አሳፋሪ የሚያደርገው ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያን ታሪክ በማዋረድ መጀመሩ ነው፡፡ ኢህአዴግ የኢትዮጵያን ታሪክ የ100 ዓመት ታሪክ ነው ማለቱ ባንዲራን ጨርቅ ነው በማለት የጥሬ መቋጠሪያ ማድርጉ፣ ህዝቡን እንደሰው ሳይሆን እንደ እንሰሳ በዘር ማደራጀቱ የህዝቡን ኢትዮጵያዊ ማንነት የገደለ ነበር፡፡ ኢህአዴግ ይሄን ያደረገው በትንሹ በ3 ምክንያቶች ነው፡፡ የመጀመሪያው ኢህአዴግ ኢትዮጵያዊያንንና የኢትዮጵያን ታሪክ የሚመጥን ፕሮፓጋንዳ ለማዘጋጀት አቅም እና እቅድ ያልነበረው በመሆኑ ነው፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ኢህአዴግ መሰረቱ እና ታሪካዊ ትስስሩ ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር ስለነበረ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊያንን በማዋረድ የስንቅ እና ትጥቅ አቀባዮቹን ፍላጎት ለሟሟላት እና ትእዛዛቸውን ለመፈፀም ሊሆን ይችላል፡፡ ሶስተኛው ምክንያት ደግሞ ለኢህአዴግ የሚመጥኑ የወረዱ ደጋፊዎችን በአገር ውስጥና በውጭ ለማሰባሰብ ሊሆን ይችላል፡፡
ኢህአዴግ ደርግን ከስልጣን ካስወገደ በኋላ ትልቁ ፈተናው ደጋፊዎችን ማግኘት አለመቻሉ ነበር፡፡ በወቅቱ በህብረተሰቡ ውስጥ ተቀባይነትና ቦታ ያልነበራቸውን ስራ አጦችን፣ ግድየለሾችንና ሰነፎችን ተጠቅሟል፡፡ በመቀጠልም ..የአባትህ ቤት ሲዘረፍ አብረህ ዝረፍ.. የሚሉ ተቀላቅለውታል፡፡ ከዚያም አንዳንድ መልካም ስምና ስብዕና ያላቸውን ሰዎች በጥቅም በመሳብ ደጋፊዎቹና አባሎቹ ለማድረግ ችሏል፡፡ በዚህ መልክ ኢህአዴግ አሁን 6 ሚሊዮን የሚጠጉ አባሎች አሉኝ ቢልም የአብዛኞቹ ምንጭ አገራዊ ራዕይና የመጪ ው ትውልድ ተስፋ ሳይሆን የወረደ ጥቅም ፍለጋ በመሆኑ ሁሉም አባል እና ደጋፊ ግዙፍ የሙስና ሃይል ሆኗል፡፡
ኢህአዴግ በዚህ አገር ከአሁን በፊት ያልታዬ ወደፊትም ሊታይ የማይችል ግዙፍ የሙስና ሰራዊት ገንብቷል፡፡ የሙስና ሰራዊቱ የተፈለፈለው ከኢህአዴግ ቁሳዊ፣ መንፈሳዊና አገራዊ አመለካከት ነው፡፡
የኢህአዴግ የሙስና ሰራዊት አሁን አገሩንና ህዝቡን ረስቷል፡፡ ራሱን ከምንጊዜውም በበለጠ ከህብረተሰቡ አርቆ፣ ለህብረተሰቡ ምንም አይነት የልማት አስተዋጽኦ ሳያደርግ ህዝቡ ያመረተውን እና በህዝቡ ስም በእርዳታ የተገኘውን ሁሉ በመቀለብ ላይ ይገኛል፡፡ ይህች አገር ነገ ከአንዳች ችግር ሊያወጣት የሚችል የልማት መሰረት ሊጣል አልቻለም፡፡ አገራዊ መግባባትም አልፈጠረም፡፡
በመቱበት ልክ ይመቱበት
ታዋቂው ሳይንቲስት Sir Isaac Newton 3ኛው የኒውተን ህግ በሚባለው ህጉ ላይ for every action there is an equal reaction የሚል ቀመር አውጥቷል፡፡ ትርጉመ አንድን ግድግዳ በራስህ ብትገጨው ግድግዳውም የዚያኑን ያክል መልሶ ይገጭሃል የሚል ይመስለኛል፡፡
በጨቋኞችና በህዝብ መካከል ይሄን የመሰለ ግንኙነት አለ፡፡ ጨቋኞች በህዝብ ላይ በሚያሳርፉት በእያንዳንዱ ብትር ልክ ህዝብም የመልስ ምቱን በጨቋኞች ላይ ያሳርፋል፡፡ ጨቋኞች በእያንዳንዱ ዜጋ ላይ ያሳረፉት ግፍና በደል ተከማችቶ ይጠብቃቸዋል፡፡ በቱኒዚያው ቤን አሊ ላይ የተላለፈው የረጅም አመት የእስራት ፍርድ፣ የግብፁ ሆስኒ ሙባረክ በአልጋ ላይ ተጋድመው ለፍርድ መቅረብ፣ የሊቢያው ጋዳፊ በቤተ መንግስት ሳይሆን በገቡበት ጉድጓድ እየታደኑ መገኘታቸው ህዝብ ተመጣጣኝ የመልስ ምት እየሰጠ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡
ቀሪዎቹ አምባገነኖችም ጊዜውን ጠብቆ በእነሱ ላይ የሚያርፈውን የምት መጠን መወሰን ይችላሉ፡፡ በህዝቡ ህይወት፣ ሀብትና የልማት ጊዜ ከባድ ምት ካሳረፉ ጊዜውን ጠብቆ ከባድ የመልስ ምት ያርፍባቸዋል፡፡ ለምሳሌ በጋዳፊና በሆስኒ ሙባረክ ላይ የሚያርፈው የመልስ ምት መጠኑ የተለየ ነው የህዝቡን የለውጥ ፍላጎትና አይቀሬነት ተገንዝበው ለለውጥ ከተንቀሳቀሱ ለራሳቸው፣ ለቤተሰባቸውና ለአገራቸው የሚቀር ስም ትተው ለማለፍ ይችላሉ፡፡ ይሄን የማያደርጉ ከሆነ ግን በአሳፋሪ የታሪክ መዝገብ ውስጥ ስማቸው ተጽፎ ለዘላለም የውርደት ምሳሌ ተደርገው ይጠቀሳሉ፡፡
የማይቀረውን መቀበል
ዴል ካርኒጌ How to stop worry and start living በሚለው መጽሐፋቸው ውስጥ ራስን ከጭንቀት ለማዳን የማይቀረውን እንቀበል /Accept the inevitable/ የሚል ምክር ይሰጣሉ፡፡ በምሳሌ ሲያስረዱም ያጋጠመን ችግር የልብ ህመም ከሆነ ከችግሩ ለመፈወስ በመጀመሪያ የልብ ታማሚ መሆናችን ሊያመጣ የሚችለው የመጨረሻ አደጋ ሞት ነው ብለን እንቀበለው ማለታቸው ነው፡፡ በአገራችንም እንደ ካርኒጌ በተደራጀ መልኩ ለችግር መፍቺያ አናውለው እንጂ ..ምን ይመጣል.. ግፋ ቢል ሞት ነው.. የሚል አባባል አለን፡፡ እኛ ምን አልባት እንዲህ አይነቱን አባባል ተስፋ ቆርጠን እንል ይሆናል፡፡ ካርኒጌ ግን እንዲህ ማለታችን ከችግሩ ለመውጣትና ከአደጋው ለመትረፍ ያስችለናል ባይ ናቸው፡፡ የችግሩን የመጨረሻ አደጋ ማወቃችን እንዳንደነበርና ችግሩን ባልተጨበጡ ፍርሃቶች ሁሉ አግዝፈን አእምሮአችንን ከሚለው በላይ እንዳናስጨንቀው ይረዳናል ባይ ናቸው፡፡ ለአእምሯችን ተረጋግተን የመጨረሻውን ተጨባጭ አደጋ ካሳወቅነው አእምሮአችን ከአደጋ የመውጣት አቅም አለው፡፡ ሊደርስ የሚችለውን የመጨረሻውን አደጋ ለአእምሮአችን ካላሳወቅነው ግን አእምሮአችን ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት በሌላቸው ጉዳዮች ሁሉ ተጨናንቆ ውድቀታችንን ያፋጥነዋል ባይ ናቸው፡፡
ለዚህ የጋዳፊን ሁኔታ መመልከት ጥሩ ምሳሌ ይሆናል፡፡ ጋዳፊ ስልጣን እንዲለቁ ሲጠየቁ ስልጣናቸውን መልቀቅ የሚያመጣውን የመጨረሻ አደጋ ለመቀበል ቢችሉ ኖሮ ስልጣን ለቀው እንደማንኛውም ሰው በመላው አለም ተዘዋውረው መኖር የሚችሉና ለአገራቸውም አቅሙ ካላቸው ለአለምም ተጨማሪ አስተዋጽኦ ማበርከት የሚችሉበት እድል ነበራቸው፡፡ ይሁን እንጂ ስልጣን ልቀቁ መባላቸው ስላስደነበራቸው እና ስላስጨነቃቸው የመጣውን ቀርቶ የማይመጣውን ችግር ሁሉ እንዲመጣ በማድረግ የእርሳቸውን ብሎም የማንንም ሰው ልጅ ክብር በሚነካ ውርደት ውስጥ ወደቁ፡፡ ከ1997 ምርጫ በኋላ በዜጎቻችን ላይ የተደረገው ጭፍጨፋም የመጨረሻውን ካለመቀበልና ከመደንበር የመነጨ ችግር ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እንደሚለው ከሆነ በአፍሪካ ተወዳዳሪ የሌለው አምባገነን ስርዓት በኢትዮጵያ ውስጥ ይገኛል፡፡ ይሄን ሁላችንም የምንጋራቸውና የምናውቀው ሁኔታ ነው፡፡ አሁን ማንኛውም አምባገነን ስርዓት የህዝብን አሸናፊነት የሚቀበልበት ወቅት ነው፡፡ አምባገነኖች ከማያሸንፉት የህዝብ ሃይል ጋር በመታገል ህዝቡን ራሱንና ሃብቱን መጨረስ የለባቸውም፡፡ አምባገነኖች ራሳቸውን የሂደቱ አካል በማድረግ የኢትዮጵያ ህዝብ የስልጣን ባለቤት መሆኑን መቀበልና ህዝቡ ያመነበትን የፖለቲካ ስርዓት እንዲዘረጋ እና መሪዎቹን በነፃና በዴሞክራሲያዊ ሁኔታ እንዲመርጥ እንዲሁም መጪ እድሉን ህዝቡ ራሱ እንዲወስን እድል መስጠት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህ የማይሆን ከሆነ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የአፈና ስርዓትም ፍፃሜው ከሌሎች አገሮች የተለየ አይሆንም፡፡ ትርፉ ግን የሃብት ማለቅና የጊዜ መጥፋት ብቻ ይሆናል፡፡
እራት መመገብ የወቅቱ አንገብጋቢ ጥያቄ
ጽድቁ ቀርቶ በቅጡ በኮነነኝ እንደተባለው ለኢትዮጵያ ህዝብ አሁን ሌላው ሌላው ሁሉ ቀርቶበት እንደ ህዝብ ራት ተመግቦ ለማደር አልቻለም፡፡ ከችግሩ ብዛት የተነሳም እህቶቻችን በህዝብ ደረጃ ማለት ይቻላል ወደ አረብ አገሮች ወደ ገረድነት በመውረድ ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህ ህዝብ፣ አፈር፣ መሬትና ውሃ ላለው ሉዓላዊ አገር የሞት ሞት ነው፡፡ አፈር ውሃ እና መሬት እያለን ፆም ከማደር እንዲሁም እህቶቻችንን፣ ልጆቻችንን፣ ሚስቶቻችንን በግርድና ከመሸጥ የበለጠ አሳፋሪ ውርደት ከቶ ሊኖር አይችልም፡፡ አዎ ለም መሬት፣ አፈርና ውሃ የሌለው ህዝብ ይሄን ቢያደርግ ተወቃሹ ፈጣሪ ይሆናል፡፡
በተፈጥሮ የተሰጠንን ለም ሀብት ወደ ምርት ለመለወጥ የሚያስችል የፖለቲካ ስርዓት መገንባት አቅቶን ስንራብና ስንሰደድ ግን የሚያዝንልን ሳይሆን የሚሳለቅብን ይበልጣል፡፡ የሚገርመው እህቶቻችን ወደ አረብ አገሮች በግርድና ሲጎርፉ በአረብ አገሮች የሚገኙ ባለሀብቶች ደግሞ የእኛን ለም መሬት ፍለጋ ወደ አገራችን በመጉረፍ ላይ ይገኛሉ፡፡
አሁን የገባንበት ችግር በአንድ ሌሊት ወይም ባልተጠበቀ የተፈጥሮ አደጋ የተፈጠረ ሳይሆን ኢህአዴግ ላለፉት 37 አመታት በፈፀማቸው ስህተቶች የተፈጠረ ነው፡፡ መፍትሄው የችግሩን ምንጭ ከማድረቅ ጋር የተያያዘ ነው፡፡

Comments
ayal (not verified)
Sun, 09/11/2011 - 05:00
Permalink
"....እህቶቻችንን፣ ልጆቻችንን፣ ሚስቶቻችንን በግርድና ከመሸጥ ...."
አዎ...ለአንድ ሰብአዊ ፍጡር እናቱን፣ ሚስቱን፣ ልጁን፣ እህቱን እና ወገኑን ለግርድና ከመሸጥ በላይ ምን ውርደት፣ ጸጸት፣ የሞራል ውድቀትና አሳፋሪ ነገር አለ?!
Add new comment