ኢትዮጵያዊ ዋጋው ስንት ነው?
ኢትዮጵያዊ ዋጋው ስንት ነው?
ደራሲና ሀያሲ አለማየሁ ገላጋይ
የፍትሕ ተጋባዥ ፀሐፊ
አርብ ህዳር 2004ዓ.ም
ኢትዮጵያዊ ዋጋው ስንት ነው? ብለን ስንጠይቅ ..አንድ ሰው ዋጋው ስንት ነው?.. ከሚለው ፍፁም ይለያል፡፡ ይሄ ዘመን አመጣሽ የኢትዮጵያዊ ዋጋ ግሽበት የተቀረውን የሰው ልጅ ሳይነካ እኛን ብቻ ያሸመደመደን ይመስላል፡፡ ኢትዮጵያውያን ለግርድና ሔደው ሬሳቸው ይመጣል- ጠያቂ የለም፤ ኢትዮጵያውያን ሞት ሸሽተው ሄደው ሞት አፍ ውስጥ ይወድቃሉ- ተቆርቋሪ የለም፤ ኢትዮጵያውያን የችግር ባህርን ሸሽተው የውሃ-ባህር ይውጣቸዋል- ሃይ ባይ የለም፤ ኢትዮጵያውያን የድህነትን ሀሩር ሸሽተው አሸዋማው በርሃ ላይ ይቀራሉ-ቅር የሚለው የለም...
ለመሆኑ ኢትዮጵያዊ ዋጋው ስንት ነው?
ኢትዮጵያዊው አረብ አገር ይሞታል፣ ሱዳን፣ ሱማሌ፣ ጅቡቲ፣ ሊቢያ... ይሞታል፣ ኬንያ ይሞታል፣ ደቡብ አፍሪካ ይሞታል፣ ግብፅ ይሞታል... ሌላው ቀርቶ የነፃነት ምድር የተባለችው አሜሪካ ውስጥ እንኳን ይሞታል... ሰው፣ ዜጋ እንዲህ የረከሰበት አገር ከወዴት ይገኛል?
ኢትዮጵያዊዎች ሞት በሚያስመርጥ ባርነት የሚማቅቁበት፣ ለወሲብ ግርድና የሚፈነገሉበት፣ በገንዘብ መያዣነት የሚታገቱበት... አገር ብዙ ነው፡፡ የሚጣላና የሚያስጠነቅቅ ቀርቶ ጥያቄነኳ የሚያቀርብ አካል የለም፡፡
ኢትዮጵያዊው ከፎቅ ይወረወራል፣ ወደ ባህር ይጣላል፣ በረሃ ላይ ይገደላል፣ ለፈላ ውሃ ይዳረጋል... ሌላው ቀርቶ ከአየር ላይ እንደ አሞራ ከነአውሮፕላኑ ተቀልቦ ይጣላል፡፡ ለእነዚህ ሁሉ መንግስታችን ለዘብተኛ ነው፡፡ ህዝባችን ድምፅ አልባ ነው፡፡ ኢምባሲያችን ዱዳ ነው፡፡ ቆንሲሎቻችን እውሮች ናቸው፡፡ በዚህም በዓለም ፊት ያለን ዋጋ እጅግ አሽቆልቁሏል፡፡ ሌላው አለም ቀርቶ እኛው ለራሳችን ያለን ግምት ወርዶ-ወርዶ ..ከመሬት በታች.. እየተባለ ከመቆጠር ደርሷል፡፡
ይሄንን ሁሉ ብሶት እንዳምሰለስል ያደረገኝ የሰሞኑ የሶማሌ ፑንትላንድ ዜና ነው፡፡ ኢትዮጵያዊው በነፍስ ማጥፋት ተወንጅሎ 700ሺህ ብር ስለመጠየቁ ቤተሰቦቹ የተማፅኖ ድምፅ አሰምተው ነበር፡፡ አስመሮም ኃ/ስላሴ የተሰኘው ይሄው ኢትዮጵያዊ ህይወቱ በክር ጫፍ ተንጠልጥላ በነፍስ ግቢ-ነፍስ ውጪ እንዳለ ነበር ዜናው የተነገረው፡፡ የቦሳሶ ከተማ የጎሳ አባላት በኢትዮጵያዊው ላይ የሞት ፍርድ አስተላልፈው የነፍስ ዋጋ ያሉትን ብር ከከፈለ ብቻ ከመገደል እንደሚተርፍ ይነግሩታል፡፡ እናም ቤተሰቦቹ መንግስት በጉዳዩ ጣልቃ ገብቶ አስመሮምን ከሞት እንዲታደግላቸው ሲወተውቱና በማመልከቻ ሲማፀኑ የተቀጠበው ጊዜ ገደብ ተገባደደ፤ ሁለት ቀናት፤ 48 ሰዓታት ብቻ ቀሩት፡፡ አስር ቀናት የተሰጠው አስመሮም ሰማኒያ ከመቶ ጊዜው የጠፋው ..መንግስት ምን እንደሚወስን አልታወቀም.. እየተባለ ነው፡፡
እንዴት? ሲሆን መንግስት ከቤተሰቦቹ ቀድሞ ዜጋው በምን ሁኔታ ውስጥ እንዳለ ማወቅ አይገባውም? እሺ ይሁን በቤተሰቦቹ ማመልከቻ እንዲያውቅ ከተደረገ በኋላ አፋጣኝ ንግግር መጀመር የለበትም? እንዴት ከአስር ቀናት ውስጥ ስምንቱ ከጠፋ በኋላ ምን እንደሚወስን አልታወቀም ይባላል? ይሄ ምንን ያመላክታል? የመንግስት ቢሮክራሲያዊ አሰራር ቀርፋፋ መሆኑን? ከዚያ ይልቅ ለዜጐቹ ያለውን ቸልተኝነት የሚያሳብቅ ነው፡፡
እንዴት? መንግስት ማንን ሊጠብቅ በዜጐቹ ላይ ቸልተኛ ይሆናል? ዜጐች ጉልበታቸውና ድምፃቸው ሁሉ የት ተጠራቅሞ በመንግስት በኩል ያላቸው አማራጭ ቸል ይባላል? የዋጋ ማጣታችን ምንጭ የገዛ መንግስታችን ነው ማለት አይቻልም? አንዳንድ አገራት በመንግስት የፖለቲካ ጉዳይ ላይ ጣልቃ ሲገቡ የሚያሳየውን መንጨርጨርና ግትርነት ስለምን ለዜጐቹ መጠቃት አይጠቀምበትም? እስከመቼ በእንባ፣ በቁጭትና በገንዘብ ብቻ እየተረዳዳን ያለ መንግስት ጣልቃ ገብነት እንዘልቃለን?
መንግስት አስመሮም ከነበረው ጊዜ ከአምስት እጅ አራቱን ቢያቃጥለውም ድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) በቀረው የሰዓታት እድሜ ተጠቅሞ ታሪኩ በሞት ከመደምደም ታድጐታል፡፡ ዜናውን ከሪፖርተር ጋዜጣ ላይ ያነበበው ድምጻዊ ምንም እንኳ በወቅቱ እጁ ላይ ገንዘብ ባይኖርም ከወዲያ ወዲህ ተሯሩጦ በመበደር የ700 መቶ ብር ቼኩን ለአስምሮም እህት አስረክቧል፡፡ ይሄኔ ነው እንግዲህ ነገሮች ሁሉ የሚገለባበጡብን፡፡ ከመንግስት ኃላፊነት፣ ተቆርቋሪነትና ተሰሚነት... በላይ እንዴት አንድ ግለሰብ ገንኖ ይታያል? ከአገሮች ጋር ለሚኖረን ግንኙነት፣ ለሚደርስብን በደል አቻ ለአቻ ከምንነጋገርበት መንግስታዊ አግባብ ይልቅ፤ እንባ፣ ቁጭትና ግለሰብን ተማምነን እስከ መቼ?
መንግስት ለዜጐቹ የሚሰጠውን ዋጋ አርክሶ ውጭ ባሉ ኢትዮጵያውያን ጣጣ ላለመግባት ከወሰነ ሰነባብቷል፡፡ በተለይ አረብ አገር ላሉ ዜጐች ሰከንድ ማጥፋት የሚፈልግ አይመስልም፡፡ ከአራት አመት በፊት ነው፡፡ ጣይቱ ሆቴል ውስጥ የምሰማው ነገር ሁሉ ክፉኛ እረብሾኝ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ አንዲት ወጣት ኑሮዋን ለማሻሻል ወደ አቡዳቢ ተጉዛለች፡፡ ይሁንና ..ሙስጠፋህ.. የሚባል አካባቢ ባልታወቀ ሁኔታ ተገድላ አስከሬኗ ይገኛል፡፡ ይሄ መረጃ የደረሰው ..በአረብ አገሮች የኢትዮጵያውያን መረዳጃ ማህበር.. ጉዳዩን ዱባይ ለሚገኘው ቆንስላ ጽ/ቤት ያሳውቃል፡፡ ቆንስላ ጽ/ቤቱ ሁኔታውን ከመከታተል ይልቅ ዝምታን ስለመረጠ አስከሬኑ ጠያቂ አጥቶ በረዶ ቤት ለአራት ወር ለመቆየት ተገድዷል፡፡
ወገንተኝነት፣ ኃላፊነት፣ ተቆርቋሪነት... ይቅር እንዴት ሰብዓዊነት ይጠፋል? የሟቿ የወይዘሪት ሄለን አስማረ ቤተሰቦች በወቅቱ ይሉ የነበረው አስከሬኗ ብቻ ይላክልን ነው፡፡ አፈር ትቅመስ፣ ተላቅሰን እንቅበራት፣ እርማችንን እናውጣ፡፡ ይሄን የጠየቀ ዜጋ እንዴት ከመንግስት ምላሽ ይነፈገዋል? የ24 ዓመት ወጣት የነበረችው የወይዘሪት ሄለን ገዳይ የአገሩ ተወላጅ እንደነበር ተደርሶበታል፡፡ በቁጥጥር ስር ውሎ የነበረ ቢሆንም ጠያቂ ሲጠፋ ተለቋል የሚል ምክንያት ፖሊስ ሰጥቶ እንዲድበሰበስ አድርጓል፡፡
ግድ የለም፤ ደሟ አንዴ ደመ-ከልብ ሆኖ ቀርቷል፡፡ የቤተሰቧ ሰቀቀን የሆነው ግን በባዕድ አገር፣ በማቀዝቀዣ ቤት ውስጥ እንዴት ይሄን ያህል ጊዜ አስከሬኗ ይጉላላል? ነው፡፡ ከተጨማሪ አንድ ወር በኋላ የወጣቷ አስከሬን ወደዚህ ሊላክ ችሏል፡፡ አምስት ወር ማለት ነው፡፡ አስከሬኗ የመጣው አብዛኛው የሰውነት ክፍሏ ተወስዶ (ተሰርቆ) በሚቆጭ ሁናቴ ነው፡፡
አልታደልንም እንጂ ተቆርቋሪ መንግስት ቢኖር አገሪቷ ያላት ዲፕሎማሲያዊ ተፅዕኖ ነገሮችን ከዚህ በላይ ለማስተካከል የሚያንስ አልነበረም፡፡ ግን ሳይሆን ቀርቶ ኢትዮጵያውያን በመናኛ ምክንያት በየተገኙበት የሚጐሳቆሉ እና የሚገደሉ እርካሾች ተደርገው ተቆጠሩ፡፡
ሌሎች መንግስታት ስለዜጐቻቸው ህይወት ቀርቶ ክብር ምን ያህል-እንደሚጓዙ እየተመለከትን ነው፡፡ በቅርቡ እስራኤል ከመመሪያ ውጭ ተጉዛ አንድ ዜጋዋን ለማዳን የከፈለችውን ዋጋ እዚህ ላይ መጥቀሱ በቂ ነው፡፡
እ.ኤ.አ በ2006ዓ.ም ነው፡፡ የፍልስጤሙ ሐማስ ተዋጊዎች አንድ ትልቅ ወታደራዊ ተልዕኮ ለመፈፀም ተዘጋጅተዋል፡፡ ተልዕኮው ከጋዛ እስከ እስራኤል ድንበር በተዘረጋ የመሬት ውስጥ ለውጥ መተላለፊያ ቱቦ ተሽሎክሉኮ ጥቃት ማድረስ ነው፡፡ እንግዲህ በተቃራኒው የ20 ዓመቱ እስራኤላዊ ሃምሳ አለቃ ገለድ ሻሊድ ደግሞ ከሁለት ታንከኛ ባልደረቦቹ ጋር ሆኖ ግዳጁን በመወጣት ላይ ነው፡፡ በዚህ መካከል ድንገተኛ የሐማሱ ማጥቃት ተሰንዝሮ ሁለቱ ወታደሮች ሲገደሉ ሃምሳ አለቃ ሻሊድ እጃቸው ላይ ይወድቃል፡፡
ስለዜጐቹ ዋዛ-ፈዛዛ የማያውቀው የእስራኤል መንግስት አምስት አመት የሞላ ፍለጋና ድርድር ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ እነሆ ድርድሩ አሁን በቅርብ ውጤት አስገኝቷል፡፡ ሐማስ ሃምሳ አለቃ ሻሊድን ለመልቀቅ በአፀፋው የእስራኤል መንግስት እጅ ላይ የሚገኙ 1ሺህ 27 እስረኞች ነፃ እንዲወጡ ጠይቋል፡፡ ጥያቄው እስራኤል ለዜጐቿ የምትሰጠውን ትኩረት መሰረት ያደረገ እንደሆነ ልብ ማለት ያሻል፡፡ ያም ሆነ ይህ የሐማስ ጥያቄ ምላሽ አግኝቶ ስምምነቱ ተግባራዊ ሆኗል፡፡ ከስምምነቱ በኋላ ጠ/ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔቲኒያሁ እንዲህ ብለዋል፡-
..በምትሳሱላቸው ወዳጅ ዘመዶቻችሁ ላይ የሳጥናኤል ተግባር የፈፀሙ ወንጀለኞች ለስራቸው የሚገባቸውን ዋጋ ሳይከፍሉ እንዲለቀቁ የሚያደርግ ስምምነት መቀበል ምን ያህል አስቸጋሪ ጉዳይ እንደሆነ እረዳለሁ፡፡..
አስቸጋሪ ቢሆንም የዜጐችን ደህንነትና ህይወት ለመጠበቅ ሲባል በእስራኤል መንግስት በኩል ተደርጓል፡፡ ድርጊቱ መልሶ የዜጐችን የደህንነት ዋስትና እንደሚያዳብር ግልፅ ነው፡፡
ወደተነሳንበት ርዕስ እንመለስ...
...ኢትዮጵያዊ በመንግስት የተተመነለት የዜግነት ዋጋው ስንት ነው? ከእስራኤላዊው፣ ከአሜሪካዊው፣ ከአውሮፓዊው፣ ከአረቡ፣ ከህንዱ፣ ከቻይናው... አንልም፡፡ ከውሻው፣ ከዶሮው፣ ከበሬው፣ ከበጉ... ሲነፃፀር ምን ያህል ነው? ውሻነኮ ከንቱ ሞት አይሞትም፡፡ ዶሮነኮ ሳይታረድ በፍል ውሃ አይቀቀልም፡፡ በሬና በግ ከከፍታ ተገፍትሮ አይገደልም፡፡ እናስ? ኢትዮጵያዊው ዋጋው ስንት ነው?

Comments
Girma (not verified)
Fri, 11/18/2011 - 21:56
Permalink
Adding comment
Teddy have to get his money back
GSM
Add new comment