ጠቅላይ ሚንስትር መለስ በትግርኛ መናገርን ለምን መረጡ?

ከአቶ አስገደ ገብረስላሴ
(የህወሓት መስራች የነበሩ ከመቀሌ)

ውድ አንባቢያን ከጥቂት ሳምንት በፊት ጠ/ሚንስትር መለስ ዜናዊ ከትግራይ ክልል ቴሌቪዥን ጋር በትግርኛ ቃለ-መጠይቅ ማድረጋቸው ይታወቃል፡፡እናም የቃለ-መጠይቁን አንድምታ ብናአያው ለጋራ ግንዛቤ ይረዳል፡፡ ስለዚህም የሚከተሉት አንኳር የመወያያ ነጥቦችን ተመልከቱና የራሳችሁን ትንታኔ ሰጥታችሁ ወደ ድምዳሜ የሚያመራ ማጠቃለያ በመያዝ በአእሞሯችሁ ሁኔታውን አሰላስሉ፡፡
በትግርኛ ቋንቋ ለትግራይ ህዝብ ብቻ በተለይ ቃለ ምልልስ ለማድረግ ለምን መረጡ?
- ትግራይ በልማትና በሃብት በመበልፀጓ ሁኔታውን የኢትዮጵያ ህዝብ እንዳያውቀውና እንዳይቆጣ ሰግተው ይሆን?
- የትግራይ ህዝብ የአማርኛ ቋንቋ መግለጫዎችን ስለማይሰማ በቋንቋው ቢነገረው ነገሮች በቀላሉ እንዲገቡት በማሰብ ይሆን?
- ለመሆኑ የሀገር መሪ ሆነው ሁሉም ኢትዮጵያዊ በብሄራዊ ቋንቋ እንዲሰማው መግለጫ እንደማድረግ ፈንታ ለምን ለትግራይ ህዝብ ብቻ የጓዳ መግለጫ እንዲሰጡ ተገደዱ? ምን መልእክት ሊያስተላልፉ ስለፈለጉ ነው?
- የትግራይን ህዝብ መልካም ነገር (ችግር) አማራው፣ ኦሮሞው፣ አፋሩ፣ጉራጋው ወዘተ መሰማት የለበትም? የትግራይ ህዝብ የሌሎችም ችግር (ብልፅግና) ማወቅ የለበትም? ታድያ ጠ/ሚንስትር በየክልሉ እየሄዱ የጓዳ መግለጫዎች ለመስጠት ይችላሉ?
የትግራይ ህዝብ ተቀይሞናልና ለብቻው ማብራሪያ ብንሰጠው ይሻላል ብለው በማሰብ ለመታረቅ? ወይስ የተስፋ እንጀራ በመስጠት እንደ ልማዳቸው ከጎናቸው በማሰለፍ መቺ ሃይል ለማድረግ ነው?
- ቃለ መጠይቃቸው የሚያብራራው በአይን የማይታይ፣ የማይዳሰስ፤ የማይቀመስ፤ የማይሰማ የህልም እንጀራ እናመጣልሃለን በሚል ዲስኩር የተሞላ ስልነበር የተቀረው ክልል ብሄሮች ህዝብ እንዳይንቁዋቸው ሰግተው ይሆን?
- የትግራይ ህዝብ ኑሮው ከድህነት በታች በመሆኑ ህዝቡ ፍትህ፣ መልካም አስተዳደር፣ ነፃነት፣ ልማት አጣን ብሎ ወደ ስደት እየፈለሰ ስላለ ለብቻው ለመስበክና ለማረጋጋት አስበው ይሆን? ከሆነስ በባዶ ሆዱ እንዴት ይሰበካል?
- ለትግራይ ህዝብ መለስ ከሌለ የትግራይ ህዝብ አይኖርም የሚል መልእክት ለማስተላለፍ አስበው ይሆን?
ከላይ የተቀመጡት መወያያ ነጥቦችን ላነሳ የፈለኩት ሰሞኑን ከህዳር8 እስከ 9/3/2004ዓ.ም የሀገራችን ጠ/ሚንስትር መለስ ዜናዊ ለትግራይ ህዝብ ብቻ የሚሰማ በትግርኛ ቋንቋ በአቶ ገዘኢ የድምፅ ወያኔ ጋዜጠኛ መጀመሪያ ለሁለት ቀን በተከታታይ መግለጫ ሰጡ ሁለተኛ ይደገም ተብሎ ለሁለት ቀን በየቀኑ ለ30 ደቂቃ ያህል የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን ትግርኛ ፕሮግራም ተቆጣጥረውት ሰንብተዋል፡፡
ቃለ መጠይቁ ያተኮረበት አጀንዳ ቢኖር በመጭው 3 እና 4 ዓመታት የትግራይን ህዝብ ፍፁም ከድህነት እናወጣዋለን፣ መልካም አስተዳደርና ፍትህን እናነግሳለን በሚል ዙሪያ የሚያጠነጥን ነበሩ፡፡ እኔም የጠ/ሚንስትሩ ዲስኩር ሊተገበር የማይችልና ጥናት የጐደለው መሆኑን ምክንያት ጠቅሼ ለመተቸት እሞክራለሁ፡፡ ጠ/ሚንስትሩ በመጭው አምስትና አራት አመታት በትግራይ ክልል የሚታረሰው መሬት ከ1/3 በላይ ስፋት በመስኖ ይለማል ብለው አፋቸውን ሞልተው ተናግረዋል፡፡ እዚህ ላይ የጠ/ሚንስትሩ ምኞት የሚሆን ከሆነ በበኩሌ አልቃወምም፤ ነገር ግን ይሄ ሁኔታ አቶ መለስ ከአሁን በፊት እንደተናገሩት ከሰጡን ተስፋ በኃላ ሳይሳካላቸው እንደቀረው ከንቱ ዲስኩር ሆኖ እንዳይቀር ስጋት አለኝ፡፡ እንደሚታወቀው ከሁለት አስርት አመታት በፊት በአንድ ጋዜጠኛ ..ከአስር ዓመት በኋላ የኢትዮጵያ ህዝብ ምን ላይ ይደርሳል.. ተብለው ሲጠየቁ መልስ ከመስጠታቸው በፊት ረዘም ላለ ደቂቃ ከአሰቡ በኋላ ..የኢትዮጵያ ህዝብ ከአስር አመት በኋላ በቀን 3 ጊዜ እስከሚጠግብ ይበላል፡፡ ጥሩ ልብስና መጠለያ ይኖረዋል.. ብለው በእርግጠኝነት ተናገሩ፡፡
በመሬት ላይ ያለው ደረቁ ሃቅ ግን የተባለው አስር አመትም አልቆ በ21 አመት ውስጥ ሶስት ጊዜ ሊባላ ቀርቶ አንድ ጊዜም ለመብላት አቅቶት ወጣቱ ሁሉ ወደ ስደት እየፈለሰ በሰሃራ በረሃ፤ በቀይ ባህር እየሞተ በሁሉም አገር እየተበታተነ የጨለማና የእንግልት ኑሮ እየገፋ ነው፡፡ በአገር ውስጥም እሚበዛው የኢትዮጵያ ህዝብ ከድህነት ወለል በታች ነው፡፡ በተለይ የትግራይ ህዝብ ደግሞ በባሰ ከድህነት ወለል በታች ነው ያለው፡፡
የተከበሩ ጠ/ሚንስትራችን በዚህ 3 አመት ውስጥ 1/3ኛው በላይ የትግራይ የሚታረስ መሬት በመስኖ እናለማዋለን እንከብበዋለን ሲሉ ምን አይነት ዝግጅት አድርገው እንደሆነ ይንገሩን? ሌላው ቢቀር የአካባቢው ዋነኛ ችግር ውሃ ነው፡፡ እናም ይሄ እንዴት ተፈታ? 400ሺ እና ከዛ በላይ ሄክታር መስኖ ለማልማት ይቅርና በአሁኑ ጊዜ በትግራይ ዞኖች ወረዳዎች ዋና ከተማዋ መቀሌ ሳይቀር ለሰው ለኮንስትራክሽን፤ ለእንዲስትሪዎች የሚሆን ውሃ የለም የሚሉን አስተዳዳሪዎች 1/3ኛውን የሚታረስ መሬት በየትኛው ውሃ ነው የሚለማው? ስንት ግድቦች አሉን? ከሌለስ መቼ ሊገደቡ (ይቆፈሩ) ይሆን የተነናገሩት በጤና ነው?
እነዚህ ችግሮች ቢወገዱ እንኳ 1/3ኛውን የሚታረስ መሬት በመስኖ ለማልማት በ3 አመት ውስጥ የትኛው መዋቅር የተኛው ባለሙያ ነው የሚያሳካው? ለመሆኑ ጠ/ሚንስትር መለስ በትግራይ ያለው መዋቅራቸውን ያውቁታል፡፡ የክልሉ መሪዎች እኮ በክልሉ ያሉ ሙያተኞችና ምሁራኖችን የማያሳትፍ በመሆኑ ምሁሩኖች እና ሙያተኞች ክልሉን እየለቀቁ እንዲሄዱ በማድረጋቸው የማስፈፀም አቅማቸው ተሟጥጦ ያለቀ መሆኑን አያውቁም? ማን ሊያስፈፅመው አስበው ነው? እስቲ ለማስረጃ ያህል፡-
የክልሉ የ2003ዓ.ም አመታዊ ባጀት 3.1 ቢሊዮን 3.1ኀ (930) ሚሊዮን ብር ወደ ማዕከላዊ መንግስትዎ ተመላሽ እንደተደረገ ያስታውሳሉ?
የትግራይ ውሃ ሃብትና የትግራይ ውሃ ኢንተርፕራይዝድ በእቃ ግዥና በውሃ ቁፋሮ ያባከኑት ገንዘብ ጥራት የሌለው ኪዝንግ መግዣ 164 ጥልቅ ጉድጓድ ቁፋሮ ብዙ መቶ ሚሊዮኖች ገንዘብ የባከነ ሳይፈቱሹ የማስፈፀም አቅም አለኝ ብለው ሳያጠኑ ይህን ሁሉ የህልም ተስፋ መናገርዎ የትግራይ ህዝብና ትግርኛ ቋንቋ የሚሰማን ሁሉ አስገርሟል፡፡ እንደ አደንዛዥ አፅ ሆኖ ተሰምቶታል፡፡
ጠ/ሚንስትሩ በቃለ-ምልልሱ ላይ ..በአሁኑ ወቅት 70ኀ የሚሆነው የትግራይ አርሶ አደር በየቤቱ የውሃ ባንክ አለው፤ 30ኀ በመጭው 3 ዓመት ይኖረዋል፡፡ ስለሆነም ሁሉም ህብረተሰብ በመስኖ እንዲያለማ ሊደረግ ነው.. ብለውናል፡፡
- አቶ መለስ አሁንም ለነገሮን ሁሉ እየተጠራጠርኩ ነው፡፡ በነፍስ ወከፍ ገበሬው በየቤቱ የውሃ ባንክ ይኖረዋል ሲሉ፤ ምን ማለትዎ ነው? 70ኀ ገበሬወ የውሃ ባንክ አለው ያሉት የት ነው ያለው? እኛ ትግራይ ነው ያለነው፡፡ የውሃ ባንክ የሚባል ግን አላየንም፡፡ በየወንዙ ዳር ጥቂት ጉድጓዶች ተቆፍረው ካልሆነ በቀር፡፡
- የውሃ ባንክ ሲሉን ሆረዩ (ውሃ ማቆር) ማለቶት ነው? ሆረዩ (ውሃ ማቆር) ከሆነ 1996 እና 1997ዓ.ም ከዛም በኋላ በሚሌዮኖች የሚቆጠሩ ገበሬውን በማስገደድ ጥናት በጐደለውና በሙያተኞች ያልታመነበት የሰው ጉልበት፤ በገንዘብ ሲታሰብ በቢሊዮን የሚገመት ሆኖ፤ በተጨማሪ ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ የተገዛ ጥቁር ላስቲክ ከህንድ ተገዝቶ፤ ገበሬው በደደቢት ብድርና ቁጠባ በብድር ተመዝግቦ ወስዶ፤ የላሲቲክ ውሃ ሳይዝ ቀርቶ በከንቱ ቀረ፡፡ ገበሬውም ይጠቅምሃል ተብሎ በስብሰባ፣ በኮንፍረንስ፣ በጉባኤዎች እንዲያምን በማድረግ ተገዶ እንዲቆፈር ሲደረግ ያለማመን መንፈሱ ይበልጥ ነበር፡፡ የመንግስት የፓርቲዎች ብዙሃን መገናኛም ስለውሃ ማቆር (ሆረዩ) ቀንና ለሊት በመደስኮር ጆሮዎቻችንን አደነቆሩን 2000 ዓ.ም፡፡ በኋላ ውሃ ማቆር ምንም ልማት ሳያመጣ ቀርቶ፤ የትግራይ ገበሬ እዳ በእዳ ሆኖ ቀረ ከሰረ አለቀሰ ሰሚ ጆሮ ግን አላገኝም፡፡ ከ3 አመት በኋላ ብዙሃን መገናኛ ዝምታ መረጡ፡፡ የማፈር ምልክትም ይታይ ነበር፡፡ ሃገራችንና የክልላችን መሪዎች ካድሬዎች ምላሳቸውን አኝከው ቀሩ፡፡
ጠ/ሚንስትር ያለፈው ኪሳራ አይበቃምና ነው የትግራይ ገበሬ በነፍስ ወከፍ በየቤቱ የውሃ ባንክ ከሰራ በቃ አለፈለት እያሉን ያለው? የካድሬዎች የውሸት ወሬ እየሰሙ መድርክ እየወጡ የማይሆነውን ነገር ከሚነግሩን ከአገራችን ሙሁራኖች ጋር ቢማከሩ አይሻልም? በአለፉት አመታት የስኳር ኢንዱስትሪን እናስፋፋለን፤ ከሁለት አመት በኋላ የስኳር ችግር ይፈታል ተብሎ የስኳር ኢንዱስትሪዎች በሚንሴቴር ደረጃ እንዲመራ ተደርጐ፤ ሚንስትር አባይ ፀሃዬ በመሾም ብዙ ተብሎ ነበር፡፡ በቂ ገንዘብ የሰው ሃይል አለን እየተባለ ተቆይቶ በዚህ ሳምንት ደግሞ አንድ መርዶ ተነገረን፡፡ እሱም የስኳር ኢንዱስትሪን ለማሰፋፋት የፋይናንስ እጥረት ስለአጋጠመን ተጓትቷል አሉ፤ ሚንስትር አባይ ፀሃዬ፡፡
ጠ/ሚኒስትር እዚህ ላይም ልክ እንደ በፊቱ ስራዎች ያለጥናት ህዝባችን በቀን 3 ጊዜ ይበላል፤ ትግራይ በሆረዩ ልማት ተቀየረች ብለውን እንደከሸፈው ሁሉ የሚሉን መክሸፉ አይቀሬ ነው፡፡ ምክንያቱም በ3 አመት እናመጣዋለን ያሉን ልማት ጥናት የጐደለውና ባለሙያዎችን ያላሳተፈ ስለሆነ ነው፡፡
ስለመስኖና ውሃ ማቆር (ሀረዩ) ሳስታውስ የህወሓት ማ/ኮሚቴ በሁለት ተሰንጥቆ ከመውጣቱ በፊት በትግራይ በመስኖ ልማት ስትራቴጂክ ለውጥ ሊያመጣ ነው ተብሎ በ15 አመት ግድብ እያንዳንዳቸው ከ100-200 ሄክታር ሊያለሙ የሚችሉ 500 አነስትኛና መካከለኛ ግድቦች መገደብ የሚል በሙያተኞች ተጠንቶ ስራ ከጀመረ በኋላ፤ ከህወሃት መሰንጠቅ ጋር ተያይዞ የገብሩ አስራት የተሳሳተና ጥናት የጐደለው ተብሎ በመኮነን ወደ አልተጠና ውሃ ማቆር እንደተቀየረ አስታወሰኝ፡፡
ያ ጥናት ግን በሞሮኮና ቱኒዚያ የተሞከረ፤ እነዚህ ሁለት ሀገሮች እያንዳንዳቸው 1500 ግድቦች እንዳላቸውና በአሁኑ ወቅት ከራሳቸው አለፎ ለአውሮፓና መካከለኛ ምስራቅ አገሮች ሰብል፣ አትክልትና ፍራፍሬ በመላክ የታወቁና ተጠቃሚዎች መሆናቸው ነው፡፡ የትግራይ ግድቦች ያጠኑ ኤክስፐርቶች እንደተሞክሮ ወስደው ያጠኑት ነበር፡፡ በዛን ጊዜ የተገደቡ በመቀሌና አካባቢዋ በሃውዜን አክሱም በሽሬ ዓዲሮዕሮ ውጤታማ በሆነ መንገድ እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ ታዲያ ክቡር ጠ/ሚንስትር ይህ ስትራቴጂክ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል በተግባር ተፈትኖ የተረጋገጠውን ከመጠቀም ይልቅ ለምን ሙያ በሌላቸው ካድሬዎች ተመርተው ሃቅነት የጐደለው ተስፋ ከሚሰጡን ከተመራማሪዎች ጋር አይመካከሩም?
-የተካኑ ኤክስፐርቶች እንዳረጋገጡት ለትግራይ ህዝብ ብሎም ለመላው ኢትዮጵያ በድርቅ ለሚጠቁ ድህነትን ለማጥፋት ከመሬት በላይና ተፋሰሶች ወንዞችን በመገደብ 1ኛ ወጭው ቀላል መሆኑ 2ኛ ሰፊ የመስኖ መሬት የሚያጠጣ መሆኑ፡፡ የጥልቅ ጉድጓድ መስኖ ግን 1ኛ ወጭው ብዙ ነው 2ኛ. እንደ ግድብ አገልግሎት አይሰጥም ይላሉ፡፡ ለዚህ እንደ አብነት ሲያስቀምጡ በእስራኤል በአመት 2.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ዝናብ ይዘንባል፡፡ ያን ውሃ ተጠቅመው እስራኤል ከመመግብ አልፈው ወደ ውጭ ኤክስፖርት ያደርጋሉ ይላሉ፡፡
በአገራችን ግን በትግራይ ብቻ ድርቅ ባልሆነበት ወቅት 12 ቢሊዮን ሜትር ኩብ በድርቅ ጊዜ 9 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ዝናብ ይዘንባል፡፡ ስለዚህ በትግራይ ግድብ ከተሰራ ከትግራይም ተርፎ ኤክስፖርት ለማድረግ ይቻላል ይላሉ ሙያተኞች፡፡ የኛ መሪዎች ግን ተመራማሪዎች የሚሰጡዋቸውን ጥናት ምን ያህል ሳይንሳዊነት ይኖረዋል ብለው ከመፈተሽ ይልቅ ያጠናው ሰው ምን አይነት ፖለቲካዊ አመለካከት አለው? አስተሳሰቡ ወዘተ በማለት አቃቂር ያወጡበታል፡፡ ያገሉታልም፡፡
- ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ቀጥለው የነገሩን በትግራይ ክልል ተራራማ ቦታዎች ደናቸው የተራቆቱ 4 ሚሊዮን ሄክታር መሬትን በ3 እና 4 አመት በደን እንሸፍናቸዋአለን ብዙ ስራ አጥ ወጣቶች ስራ ይፈጠርለታል ብለዋል፡፡
- ጠ/ሚንስትር አሁንም አልተቀበልኩዎትም፡፡ ምክንያቱም በትግራይ ክልል ከ1984ዓ.ም ጀምሮ 20 አመት ሙሉ የተለያዩ የሀገርና የውጭ ዝርያ ያላቸው ዛፎችን በማፍላት በየአመቱ በብዙ ቢሊዪኖች የሚቆጠሩ ተተክለዋል ተብለዋል፡፡ እስካሁን እንደምናየው ከሆነ አልፎ አልፎ በአድዋ አክሱም ሽሬ ደጋማ ተራራዎች በዛው በነበሩ እፅዋቶች ጥበቃ ተደርጐላቸው የተፈጥሮ ዛፎች አሉ በተረፈ በሌሎች ቦታዎች ሰፋፊ በረሃማ ቦታዎች የነበሩትም ጠፍተዋል አዲስ የተተከሉትም የሉም፡፡ ለምን ለሚል ጥያቄ?
1. በምስራቅ ትግራይ በእንዳርታ በሁለት ዓውላዕሎ ደጋዎችና ቆላማ ቦታዎች ልኡል ራስ መንገሻ በጥብቅ የሚጠብቁት የነበሩ ጥድ ወይራ እና ሌሎች እፅዋት እሳት ገብቶ ከአላቃጠለው በቀር ያልቃል ተብሎ የማይገመት የነበረ በአሁኑ ጊዜ በተለይ ጠ/ሚ ስልጣን ከያዙ በኋላ ለሙዚየም የሚሆን ጥድና ወይራ የሚባል ነገር የለም፡፡
ሌላው በተንቤ፣ አክሱም፣ ዓድዋ፣ ሽሬ፣ ወልቃይት፣ ፀገደ አሰገደ፤ አድያቦ የተፈጥሮ እፅዋት ተሸፍነው ነበር በተለይ ጠ/ሚ መለስ እና እኔ እምናውቀውን እንደማስረጃ ላቅርብ፤ ከሽሬ ከተማ 5 ኪሎ ሜትር ወጣ ብለን ወደ ምዕራብ ደደቢት አልፈን ተከዜን ተሻግረን ወልቃይት ዓዲረመፅ ከ230 ኪሎ ሜትር በላይ ርቀት በተለያዩ እፅዋቶች ተሸፍኖ አንድ ሰው ከጓደኛው ተነጥሎ ከ20 ሜትር በላይ ከራቀ ጫካው ውስጥ ገብቶ ተደናግሮ የሚጠፉበት ሁኔታ እንደነበረ ነው፡፡ መቼም እርስዎም ቢሆኑ ይሄን ይረሱታል ብዬ አላስብም፡፡
ከሽሬ በዓዱሃገራይ፤ ሽራሮ ሕሞራም ወደ 300 ኪሎ ሜትር ጫካ ነበር መኪና መንገድም በግራና ቀኝ ዛፎች ተሸፍኖ ነበር፡፡ እነዚህ ቦታዎችም በአሁኑ ጊዜ ለሙዚየም የሚሆን ዛፍ እንኳን የላቸውም፡፡ እነዚህ ዛፎች በሁለት ምክንያት ጠፍተዋል፡፡
1ኛ. የክልሉ መንግስት ምንም ጥበቃና መከላከል ባለማድረግ፤
2ኛ. የሰፈራ እንቅስቃሴ ጥናት በጎደለው ፖሊስ ከተከዜ ሁመራ ከዛም አልፎ በሕሞራ ሜዳማ በረሃዎች ጥርጊያ መንገድ ተከትሎ ከ220 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ግራና ቀኝ ጥርጊያ 30 (60) ኪሎ ሜትር ህዝቡ በመስፈሩ እፅዋቶች ስለወደሙ በበረሃው የነበሩ እንሰሳ ዘገዳም ዝሆን፣ አጋዘን፣ ጐሽ፣ አንበሳና ነብር፣ ድኩላ፣ ጉሬዛ፣ ከርከሮ ወዘተ ሸሽተው ሱዳን ገብተዋል፡፡
- በአጠቃላይ በትግራይ ያገር ውስጥ እፅዋት አልቀዋል፡፡ በ20 አመት የስልጣን ዘመንዎ የደን ማጥፋት እንጂ የደን የማልማት ስራ አልታየም የቀሩትም ዘመንዎ አሁንም ህዝቡ የኑሮ ችግር ስላለው አልፎ አልፎ የሚገኙ ዛፎች ከስራቸው በመቆፈር ወደከተማ እያወጣ በመሸጥ የለት ጉርሱን ለማግኘት ኑሮውን እየገፋ ነው፡፡ ጠ/ሚ በመቀሌ ከተማ ብቻ ቅዳሜ እና ሰኞ በ6 አቅጣጫ እንጨት ተጭነው የሚገቡ አህያና በቅሎች እጅጉን ብዙ ናቸው፡፡ እንግዲህ ሁኔታው እስካሁን የገለፅኩት ነው፡፡ ጠ/ሚንስትራችን ደግሞ 4ሚሊዮን ሄክታር በ4 አመት አረንጓዴ እናደርጋለን ብለዋል፡፡ በበኩሌ ከሆነ አሁንም ደስታውን አልችለውም፡፡ ግን ደግሞ በየትኛው መዋቅር? ምክንያቱም በአሁኑ ጊዜ በትግራይ ያለዎት መዋቅር፤ ልድገምልዎትና ምሁራኖችና ባለሙያዎችን የማያሳትፍ፤ በሙስና የላሸቀ ሳለሰራ ልብላ የሚል በመሆኑ፤ ከክልል እስከ ቀበሌ ያለው የካድሬ መዋቅር ስለራሱ እንጅ ስልሀገር ልማት ደንታ የሌለው፤ በአካባቢው የሚገኙ ምሁራኖችን እያሳተፈ የማይሰራ ከመሆኑም ሌላ 4 ሚሊዮን ሄክታር በ21 ዓመት ያላለማ በ3 አመት ሊያለማ አይችልም፡፡ ጠ/ሚኒስትር እዚህ ላይ እኔ ብቻ ሳልሆን የራስዎ ካድሬዎችም ሳይቀሩ አይቀበሎዎትም፡፡
ጠ/ሚንስትር ሌላው አስግራሚ ነገር በትግራይ በ4 አመት ውስጥ ከእርሻ የሚገኘውን ገቢ ከዛሬ 12 አመት በፊት በመላው ኢትዮጵያ ከሚታረስ መሬት ይገባ የነበረውን ምርት ያህል በአንድ ዓመት ውስጥ በትግራይ ከእርሻ ብቻ እንዲገኝ እናደርጋለን ብለውናል፡፡
ጠ/ሚንስትር ይህ ህልም የመሰለ መግለጫ 80 ሚሊዮን የአገራችን ህዝብ ቢሰማው አያስገምትዎትም? በበኩሌ አሰበውበት ነው የተናገሩት ብዬ አልቀበለውም፡፡ ከ12 አመት በፊት የኢትዮጵያ ህዝብ ከ70 ሚሊዮን በላይ ነበር፡፡ በወቅቱም ይገባ የነበረ የእርሻ ሰብል ምንጭ እንኳን ተጨባጭ ማስረጃ ባይኖረኝ በመቶ ሚሊዮን ኩንታል የሚቆጠር የእርሻ ሰብል ነበር፡፡ ታዲያ ጠ/ሚንስትር መለስ እያሉን ያሉት ከ3 አመት በኋላ ትግራይ ከ100 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ሰብል ያፍሳል ነው? አሁንም ያስተዛዝባልና ያስቡበት፡፡ የእርስዎ መስተዋት እኮ የኢትዮጵያ ህዝብ ነው፤ የክልሉ ጥናት እንደሚጠቁመው የትግራይ የሚታረስ መሬት 1.3 ሚሊዮን ሄክታር ነው የመላው ኢትዮጵያ የሚታረስ መሬት ስንት ሚሊዮን ሄክታር ነው?
እንደ የክልላችን መሪዎች አባባል ባለፈው ወር አቶ ኪሮስ ቢተው እንዳሉት በ2004ዓ.ም የትግራይ የሚታረስ መሬት 25ኀ በመስኖ ይለማል፡፡ ይህ ማለት 425..000 ሄክታር ይለማል ማለት ነው፡፡ ባለፈው 2002ዓ.ም በዘመነ ስልጣን ፕሬዘዳንት አለቃ ፀጋዬ በርሄ 170000-እስከ 200..000 ሄክታር መስኖ አልምተን በአመት 3 ጊዜ ምርት በማስገባት የትግራይን ረሃብና ድህነት ታሪክ እናደርገዋለን ሲሉ ሰምተናል፡፡ በዚህ ሰሞን ደግሞ (በ2004 ዓም) በመስኖ 28 ሚሊዮን ኩንታል እናስገባለን ብለውናል፡፡ ይህ ማለት ለጠቅላላው የትግራይ ህዝብ (የተወለዱ ሕፃናትንም ጨምረን) ብናካፍለው እንኳ ለአንድ ሰው ከ6-እስከ7 ኩንታል በአመት ይደርሰዋል፡፡ ዋ... ው... እንዴት ያለ የውሸት ፕሮፓጋንዳ ነው፡፡ (ማደንዘዣ እጽ ነው) እዚህ ላይ የጠ/ሚኒስነር የመግለጫ መነሻ ነጥብ ይህ ይሆናል፡፡ ቢሆንም በባለሙያ አረጋግጠው ነው መናገር የነበረብዎት፡፡ ስለዚህ አሁንም ትልቅ ስህተት ፈፅመዋልና መግለጫዎን ደግመው ይፈትሹት፡፡

Comments

አቶ አስገደ ገ/ ስላሴ ትግሪኛውን ወደ አማርኛ ተርጉመው ላቀረቡልን ጥልቅ ማብራሪያ በጣም እናመሰግናለን::
የውሃ ማቆር ታሪክና የደረግ የመንደር ምስረታ ታሪክ ተመሳሳይ ሆነብኝ:: ደርግ ብዙ ገበረዎችን በአንድ ላይ ሰብስቦ መንደር መስርቱ ሲል
1. ገበሬው ለከብቶቹ ማገጃ በቂ መሬት ሳይሰጠው::
2. አርሶ አደሩ ከብቶችቹ የሚቆሙበት ልጆቹ የሚጫወቱበት በቂ ቀዬ( ደጃፍ)ተመጥኖ ሳይሰጠው
3.ከብቶቹን የሚያሰማራበት የመውችጫ ወይንም የመሄጃ መንገድ ሳይበጅለት ሌላም እጅግ ብዙ ነገር ሳይጤን:በካድሬዎች አስገዳጅነት ብቻ የስንቱ ቤት እንደፈረሰ ሁላችንም የምናስታውሰው ነው::

አሁንም ከሁለት አስርት አመት በህዋላ በውሃ ማቆሩ የታየው ትያትር ያው ተመሳሳይ ነው:: እኔ እራሴ በብዙ ቦታዎች ማለትም በመላው ኢትዮጵያ ማለት ይቻላል:: ከተራሮች ስር በሚፈልቁት ግዙፍና ትናንሽ ወንዝች ላይ ምንም አይነት የመስኖም ሆነ የመገደብ ሙከራ ሳይደረግ ምንም ዉሃ በማይገኝበት ተራሮችና ጉብታዎች ላይ ዉሃን ለማቆር የተቆፈረውን ጉድጉዋዶች አይቼ በጣም አዘንኩኝ::
በዓይናችን እያየን የሚፈሰውን ውሃ ሳንጠቀም ገና ወደፊት ክረምት ሲመጣ ምናልባት የሚዘንበውን ውሃ ለማቆር ምን ጉድዱዋድ አስቆፈረን? ለምንስ ላስቲክ በብድር አስገዛን? ህንዶች ላስቲካቸውን ሸጠው አተረፉብን የኛስ ትርፍ ምንድነው?
1. የጊዜ መባከ
2. የገዘብ መባከን
3.የጉልበት መባከን:: ለነዚህ ሁሉ ብክነቶችስ ተጠያቂው ማነው?

ቱሉ ነገዎ

Ato Asgede, Thanks for summarizing the interview and compare with the actual.I was an Expert in woreda Agriculture office, but currently at Addis.The reason why I left the woreda is like you said.The Cadres in the office couldn't listen to the ideas of the expert unless he is a member.

Add new comment

Filtered HTML

  • Web page addresses and e-mail addresses turn into links automatically.
  • Allowed HTML tags: <a> <em> <strong> <cite> <blockquote> <code> <ul> <ol> <li> <dl> <dt> <dd>
  • Lines and paragraphs break automatically.

Plain text

  • No HTML tags allowed.
  • Web page addresses and e-mail addresses turn into links automatically.
  • Lines and paragraphs break automatically.